Wednesday, September 4, 2013

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የተፈፀመውን ድርጊት አወገዙ


በዘሪሁን ሙሉጌታ

ባለፈው ቅዳሜ (ነሐሴ 25 ቀን 2005 ዓ.ም) በሰማያዊ ፓርቲ አመራርና አባላቱ ላይ የታጠቁ ፖሊሶች አድርሰውታል የተባለውን ሕገወጥ ተግባር እናወግዛለን ሲሉ ዋና ዋና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አስታወቁ።
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉአላዊነት (አረና) ፓርቲዎች ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የደረሰው ህገ-ወጥ ተግባር ነው ብለዋል።
አንድነት ነሐሴ 27 ቀን 2005 ዓ.ም ‘‘በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የተወሰደውን ህገ-ወጥ እርምጃ አጥብቀን እናወግዛለን’’ በሚል ርዕስ በወጣው መግለጫ በፓርቲው ላይ የደረሰው ህገ-ወጥ ተግባር የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ምህዳሩን የመዝጋትና የማናለብኝነት አንዱ መገለጫ ነው ብሏል።
አንድነት ቅዳሜ ምሽት በሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ የተፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት በሰላማዊ ትግሉ ላይ እየተፈፀመ ያለ እርምጃ መሆኑንና የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት የማገት፣ የማፈንና የመደብደብ እርምጃ አሳፋሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ሲል በመግለጫው አመልክቷል።
‘‘ፀጥታ አስከብራለሁ የሚለው ፖሊስ አካል መብትን በድብደባ ለማስቆም የሄደበት መንገድ ህገ-ወጥ ነው’’ ያለው የአንድነት መግለጫ መንግስት እያካሄደ ያለውን የአፈናና የጉልበት አቅጣጫ እንዲያቆም ሲል ጠይቋል።
የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት ፓርቲ (አረና) ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት እንኳን ፓርቲ ግለሰቦችም በማንኛውም ጉዳይ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብት ሕገ-መንግስታዊ መብት እስከሆነ ድረስ ይህንን ህገ-መንግስታዊ መብት በኃይል እርምጃ መቀልበስ የለበትም ብለዋል። በመሆኑም በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የተፈፀመውን የኃይል እርምጃ እንቃወማለን ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል።
የመላው ኢትዮጵያ ድርጅት አንድነት ሊቀመንበር አቶ አበባው መሐሪ በበኩላቸው ጉዳዩን በማስመልከት ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የደረሰው ህገ-ወጥ ተግባር እንቃወማለን ብለዋል። ምንም እንኳ ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የትግል አጋርነት ፍላጎቱ ባይኖረውም በፓርቲው ላይ የደረሰው ችግር በእኛም ላይ የሚደርስ ስለሆነ በጉዳዩ ላይ ተወያይተን መግለጫ የምንሰጥበት ይሆናል ብለዋል።
ሰማያዊ ፓርቲ ነሐሴ 25 ቀን 2005 ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ የፖሊስ ልብስ በለበሱና ቢሲቪል የታጠቁ ኃይሎች ቢሮው ተሰብሮ አባሎቹ ታስረው መደብደባቸውን ከትናት በስቲያ አመራሮቹ በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ መግለፃቸው አይዘነጋም።
በጉዳዩ ላይ የመንግስትን አካላት ለማነጋገር ጥረት ያደረግን ሲሆን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳይ ጽ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ስብሰባ ላይ በመሆናቸው በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ልናገኛቸው አልቻልንም። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃናን ለማናገር ያደረግነው ጥረት ስብሰባ ላይ በመሆናቸው አልተሳካም።
ያም ሆኖ አቶ ሽመልስ ከማል ከትናንት በስቲያ ጉዳዩን በተመለከተ ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ ፖሊስ የፓርቲውን ጽ/ቤት ሰብሮ በመግባት ወከባ አልፈፀመም ብለዋል። የሰማያዊ ፓርቲ ያልተፈቀደ ሰልፍ ለማድረግ ሙከራ ማድረጉንም አያይዘው ገልፀዋል።
ሰማያዊ ፓርቲ በቅርቡ የተመሰረተ ሲሆን በወጣቶችና ምሁራን ቀዳሚ ሚና ለመወጣት መመስረቱን የሚገልፅ ፓርቲ ሲሆን በመጪው ቅዳሜ ጳጉሜ 2 ቀን የተከለከለውን ሰላማዊ ሰልፍ በድጋሚ ለማካሄድ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment