Thursday, September 5, 2013

ዜና በጨዋታ፤ አየር መንገዴ ሆነ እንዴ… መደዴ…!? (አቤ ቶኪቻው)

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ተደጋጋሚ ጉዳቶችን ሰምተንበት ደንግጠናል፡፡ ባለፈው ጊዜ በመላው ድሪም ላይነሮች ላይ የደረሰው የባትሪ መጋል የእኛንም አንድ ለእናቱ ድሪም ላይነር ስጋት ላይ የጣለ ነበር፡፡ ቀጠለ በለንደን ከተማ አንዱ አውሮፕላናችን ሲጨስ ታየ ተብሎ ትልቅ ወሬ ሆኖ እኛም ኤድያ…. አሁንስ አየር መንገዴ ቁጣ መጣበት እንዴ… ብለን አድነነ ከመዓቱ ብለን ፀሎት አደረግን፡፡ አሁን ደግሞ ከወደ ደቡብ አፍሪካ አንድ ወሬ ሰማን እቃ ጫኙ ካርጎ አየር መንገዳችን ሸክሙ ከብዶት እንደ ሮኬት ከአፍንጫው ወደላይ ተቀስሮ አየነው… አሁን ማንጎራጎር ጀመርን…Abe Tokichaw (Abebe Tolla) the Popular Ethiopian Political Satirist
ጥሩም አላወራም ሰው ሁሉ ባገሩ
ውድ አየር መንገዴ ምንድነው ነገሩ
መንሸራተት በዛ ቀረ እና መብረሩ
ካዋዋሉ ይሆን ወይ ካስተዳደሩ…
ብለን ሳናበቃ ከወደ አስተዳደሩ አንድ ዜና ሰማን፤ ይሄማ ካለ አዲስ መስመር አይሞከርም ይከተሉኝማ…

ከ9 ወር በፊት ወደ 1000 የሚጠጉ ሰራተኞች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ተባረው ነበር፡፡ ሰራተኞቹን ለአየር መንገድ ያስቀጠራቸው ስባኮ (ስልጡን ባለሞያ ኩባንያ) የሚባል ድርጅት ነበር፡፡ ሰራተኞቹ የመባረራቸውን ምክንያት ሲጠይቁ ”ይሄ ”ስባኮ” የተባለ አስቀጣሪ ድርጅት ከአየር መንገድ ጋር ኮንትራቱን አቁሟል” ተባሉ፤ ጥቂት ምግባረ ሰናይ ተብለው ያልተባረሩ ሰራተኞችም በተባረሩት 1000 ሰራተኞች ምትክ አስቀጣሪ የሆነው “ማሊፎ” (ማህበራዊ ሊግ ፎረም) በተባለው ድርጅት እንዲታቀፉ ተደረገ፡፡ እነዚህ ያልተባረሩ ሰራተኞችም አዲስ ገቢዎቹን የማሊፎ ልጆች በቅጡ ስራውን እንዲያለምዷቸው ተመከሩ፡፡ በጄ… አሉ፡፡
በመሃል ላይ የቀድሞው “ስባኮ” ድርጅት ያስቀጠራቸው እና ያልተባረሩ ሰራተኞች አንድ ቅፅ ተላከላቸው ቅፁ “ከሊግ እና ከፎረም አባልነት እየመረጣችሁ ሙሉ” የሚል ነበር፡፡ እነርሱም “ስለ ሊግም ሆነ ስለ ፎረም በቂ እውቀት የለንም እኛ ስራችንን ብቻ ነው የምንሰራው… አትቁሙ… ” ብለው ሁለቱንም ቅጾች ሳይሞሉ መለሷቸው፡፡
ግዜው ሄደ ሄደ …አሁንም ሄደ…. “ማሊፎ” (ማህበራዊ ሊግ ፎረም) ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ከየቀበሌው የተሰባሰቡ የኢህአዴግ አባል ወጣቶችን ቀድሞ “ስልጡን ባለሞያ ኩባንያ” የተበላው ድርጅት ባስቀጠራቸው አንድ ሺህ ሰራተኞች ምትክ ካስቀጠረ 9 ወራት ተቆጠሩ፡፡ አሁን የማሊፎ ወጣቶች በስልጡን ባለሞያ ኩባንያ ልጆች በተሰጣቸው ስልጠና ስራውን ተላምደውታል፡፡ ”እሰይ እንኳን ተለመዱ” ይበሉና ይከተሉኝማ…
አሁንም ከትላንት በስትያ ወደ ሰባ አምስት የሚጠጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች በፌደራል ፖሊስ እና በአየር መንገዱ ጥበቃ ሰራተኞች ከስራቸው ተባረዋል፡፡ እነዚህ ሰራተኞች ከቀበሌ የተላኩ አንድ ሺህ ሰራተኞችን ስራ እንዲያስለምዱ ከጓደኞቻቸው ተነጥለው “መልካም ስነምግባር አላችሁ” ተብለው ቀርተው የነበሩ ቢሆኑም፤ ”ከሊግ ከፎረም…” ምረጡ ሲባሉ “መልሱ የለም” ብለው ሁለቱንም አንሞላም ያሉ ናቸው፡፡
ማስታወሻ፤ ሊግም ፎረምም የኢህአዴግ መንትያ ልጆች ናቸው፡፡
የስራ መታወቂያቸውን ተቀምተው የተባረሩት እነዚህ ሰራተኞች ከስራ ሲሰናበቱ፤ ደሞዝ አልተሰጣቸውም፣ ደብዳቤ አልተሰጣቸውም፣ ማስጠንቀቂያ አልተሰጣቸውም፣ ትራንስፖርት እንኳን አልተሰጣቸውም፡፡ ስናጋንንም፤ ”ሰላም ወደቤታችሁ ግቡ” እንኳ አልተባሉም!
“ምን አጠፋን እና ከስራችን እንባረራለን” ብለው ቢጠይቁም “ድርጅቱ ጀርባቹን ሲያጠና ቆይቷል እናም አትሆኑንም” ብለዋቸዋል፡፡ ይሄንን የሚገልፅ ደብዳቤ ስጡን ብለው ጠይቀው ነበር…የሚሰማ አላገኙም፡፡
እናም አየር መንገዳችንን ትልቅ ቦታ ሰጥተነው የነበርን ሁላ… አየር መንገዴ ሆነ እንዴ… መደዴ….! ብለን እየተከዝን እንገኛለን! ገና ዛሬ… ብሎ የሽሙጥ ጥቄ መጠየቅ ይቻላል…!

No comments:

Post a Comment