Wednesday, September 4, 2013

አቶ ገብሩ አስራት ከፓርቲ ሊቀመንበርነታቸው ሊነሱ ነው አረና ጳጉሜ 1 እና 2 ጉባኤ ይቀመጣል

በዘሪሁን ሙሉጌታ

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት (አረና) ፓርቲን ከአራት አመታት በላይ ሲመሩ የነበሩት የቀድሞው የህወሓት አባልና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት ከፓርቲ ሊቀመንበርነታቸው ሊነሱ ነው።
በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት አንድ የፓርቲው ሊቀመንበር ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥን ስለማይፈቅድ አቶ ገብሩ በደንቡ መሠረት ስልጣናቸውን ለሌላ ተመራጭ ለማስረከብ ይገደዳሉ። ፓርቲው በመቐሌ ከተማ በመጪው ቅዳሜ እና እሁድ (ጳጉሜ 1 እና 2) ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያካሂድም ፓርቲው ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቋል።
አረና በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ፓርቲው በመድረክ ውስጥ ስለሚኖረው የአሰላለፍ ሚና እና የሊቀመንበር ምርጫ ላይ ወሳኝ አቋም እንደሚወሰድም ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልፀዋል።
ከሊቀመንበር ምርጫ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል በእነ አቶ ገብሩ አስራትና በአቶ አስገደ ገ/ስላሴ መካከል የነበረው ልዩነት መፍትሄ የሚያገኝበት እንደሆነም ምንጮች ጠቁመዋል። በተሰናባቹ ሊቀመንበርና በአቶ አስገደ ገ/ስላሴ መካከል የነበረው ልዩነት እነ አስገደ ወጣቶችን ወደ ፓርቲው የአመራር እርከን መምጣት አለባቸው የሚል ሲሆን በአንፃሩ በእነ አቶ ገብሩ በኩል ቀደም ሲል በትግሉ ተሳትፎ የነበራቸው፤ ከ1993 የህወሓት ክፍፍል በፊት ከህወሓት የወጡትን በአሁኑ ወቅት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ብርሃኑ በርኸ እንዲመረጡ ይፈልጋሉ።
የእነ አቶ አስገደ ቡድን ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር የጀመሩት አቶ አስራት አብርሃምና ሌሎች ጠንካራ ወጣቶች የአመራር ቦታውን እንዲይዙ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት መድረክ ውስጥ ከተፈጠረው የፖለቲካ ትኩሳት ጋር በተያያዘ አቶ አስራት በራሳቸው ፈቃድ ከፓርቲው በመልቀቃቸው የኃይል ሚዛኑ ወደ አቶ ብርሃኑ እንደሚያመዝንም እየተገለፀ ነው።
አቶ ብርሃኑ በጥብቅና ሙያ የሚተዳደሩ ከሀገር ውስጥ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲና ከህንድ ሀገር በህግ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን ቋሚ መኖሪያቸውም መቀሌ ከተማ በመሆኑ ፓርቲውን ይበልጥ ያንቀሳቅሳሉ ተብሎ ይገመታል። አቶ ብርሃኑ በአረና ፓርቲ ካሉ በሳል አመራሮች የሚጠቀሱ ሲሆን የህግ እውቀታቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይነገርላቸዋል።

No comments:

Post a Comment