በአሸናፊ ደምሴ
ለመንገድ ግንባታ የሚያገለግል ዶዘር መኪና በተጭበረበረ ቼክ ወስደዋል የተባሉት የአልጌ ኮንስትራክሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ሃይማኖት ኤሊያስ፤ በ447 ሺህ 500 ብር የቼክ ማጭበርበር ወንጀል ተከሰው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ በመባላቸው በትናንትና ውሎው በ3 ዓመት ከ7ወር ፅኑ እስራትና በ1‚000 ብር ተቀጡ።
የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ ዞን ውስጥ እየተከናወነ ላለው የመንገድ ግንባታ የመንገድ ጥርጊያ አገልግሎት የሚውል አንድ ዶዘር መኪና ከግል ተበዳይ የትምጌታ ማሞ በተለያዩ ቀናት የ371 ሺ ብር እና የ76 ሺ 500 ብር በድምሩ የ447 ሺ 500 ብር ቼክ በመፃፍ በህዳር 5 ቀን 2005 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲወጣ ቢፈቅድም ተከሳሹ በተባለው ባንክ ምንም አይነት ተቀማጭ ገንዘብ ሳይኖረው ቼክ ፅፏል ሲል፤ በቼክ ማጭበርበር ወንጀል ክስ መስርቶበታል።
የዐቃቤ ሕግን ክስ ሳይቃወሙ የተከራከሩት ተከሳሹ ቼኩን መፃፋቸውን አምነው ነገር ግን የግል ተበዳይን ለመጉዳትና የባንኩን የቼክ አሰራር ለማስተጓጐል አስበው ያደረጉት ሳይሆን፤ መንግስት ለመንገድ ግንባታው ሊከፍላቸው የሚገባውን ገንዘብ በጊዜው ባለመስጠቱ የተከሰተ ችግር መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቼኩ የተቆረጠው መኪናው አገልግሎት ባልሰጠበት ወቅት በቅድሚያ መሆኑንም ጭምር የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ አስረድተዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ቼኩ እንዲከፈል በታዘዘበት ወቅት ምንም ዓይነት ተቀማጭ ገንዘብ አለመኖሩን ሁለት ምስክሮችን፣ ሁለት ተከሳሹ ያዘዙባቸውን ቼኮችና ባንኩ በተከሳሽ አካውንት ውስጥ ተቀማጭ ገንዘብ አለመኖሩን የገለፁበትን ደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
የግራ ቀኙን ሀሳብ ያደመጠው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎትም ተከሳሹን ጥፋተኛ ካለ በኋላ፤ በነሐሴ 28 ቀን 2005 ዓ.ም ውሎው የተከሳሽን ያለፈ ባህሪ መልካምነትና የቤተሰብ አስተዳዳሪነት ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ቅጣቱን በማቅለል በ3 ዓመት ከ7 ወር ፅኑ እስራትና በ1ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
No comments:
Post a Comment