በመስከረም አያሌው
የኢትዮጵያ ራእይ ፓርቲ (ኢራፓ) በመጪው ጳጉሜ 3 ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በደብዳቤ ቢያሳውቅም እስከ አሁን ድረስ ምላሽ አለማግኘቱን ገለፀ።
የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ተሻለ ስብሮ ትናንት ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ፓርቲው ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ነሐሴ 8 ቀን 2005 ዓ.ም በፅሁፍ ለአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እውቅና ሰጪ ክፍል ካሳወቀ 20 ቀናት ያለፉት ቢሆንም እስከ ትናንት ድረስ መልስ አለማግኘቱን ተናግረዋል። ሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ ፓርቲው የመረጠው ቀን በማንም ያልተያዘ በመሆኑ እውቅና እንዲሰጣቸው ተደጋጋሚ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል። ፓርቲው በነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም እና በመስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም ሰልፍ ለማረግ አስቦ የነበረ ቢሆንም ቀኖቹ በሌሎች ተቃዋሚዎች ቀደም ብሎ በመያዛቸው ሰልፉን በመካከል ጳጉሜ 3 ለማድረግ መወሰናቸውን የገለፁት አቶ ተሻለ፤ ብሔራዊ ግብረሃይል ተቋቁሞ ለሰላማዊ ሰልፉ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ እውቅና እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።
በየቀኑ እየተመላለሱ ከሚመለከተው አካል ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ተሻለ ነገር ግን ምንም አይነት ትብብር እንዳልተደረገላቸው፤ ይልቁንም ተልካሻ ምክንያቶች እየተሰጧቸው እንደሆነ ገልፀዋል። የጳጉሜ 3ቱ ሰላማዊ ሰልፍ ፓርቲው በዓመት አራት ጊዜ ሊጠራ ያሰባቸው ሰላማዊ ሰልፍ አካል እንደሆነ የገለፁት አቶ ተሻለ፣ የሰልፉ አላማም መንግስትን በማስጠንቀቅ እና ህዝቡን በማንቃት ለብሔራዊ መግባባት ዝግጁ ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።
የሰልፉን መነሻ እና መድረሻ በተመለከተ ፓርቲው ለእውቅና ሰጪው አካል ሁለት አማራጮችን እንዳስቀመጠም ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልፀዋል። በአንደኛ ደረጃ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ጀርባ ከሚገኘው የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤቱ ተነስቶ በፍል ውሃ፣ ቤተ መንግስት እና ሂልተን ሆቴል አድርጎ መዳረሻውን አራት ኪሎ ትምህርት ሚኒስቴር አደባባይ ለማድረግ ነው። ይሄኛው የማይሳካ ከሆነ ደግሞ ከዋና ጽህፈት ቤት ተነስቶ በቸርቸል ጎዳና መሀል ፒያሳ አድርጎ መጨረሻው አራት ኪሎ ትምህርት ሚኒስቴር አደባባይ እንዲሆን መጠየቃቸውን የገለፁት አቶ ተሻለ፤ የሚሰጠው መልስ ከነዚህ ከሁለቱ በአንዱ ቢሆን እንደሚመረጥ፤ ካልሆነ ግን እንደመስቀል አደባባይ ያሉት ቦታዎች ናቸው የሚገቧችሁ ከተባሉ ለመደራደር ፈቃደኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
“እኛ የስብሰባ ፈቃድ አልጠየቅንም፣ የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድም አልጠየቅንም። ህገ-መንግስቱ አሳወቁ ከሚለው ተነስተን ነው ያሳወቅነው” ያሉት አቶ ተሻለ፤ የፀጥታ እና የደህንነት ጥበቃ የሌለው ሰላማዊ ሰልፍ ላለማድረግ በማሰብ ማሳወቃቸውን ገልፀዋል። ለሰላማዊ ሰልፉ የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል። ፓርቲው በህገ መንግስቱ ማእቀፍ ውስጥ ሆኖ የተለያዩ መፈክሮችን እና ቀስቃሽ ጽሁፎችን ማዘጋጀቱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ሰላማዊ ሰልፉም እንደሚፈቀድ እና በእለቱ እንደሚካሄድ ፓርቲው ተስፋ እንዳለው ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment