የፌደራል ጉዳዮች ሚ/ር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ከሰሞኑ መንግስት በአዲስ አበባ በጠራው ጽንፈኝነትን እና አክራሪነትን የሚኮንን ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር በስደተኛው ሲኖዶስና በማህበረ ቅዱሳን ውስጥ መሽገዋል ያሏቸውን ምእመናን የግንቦት 7 ከበሮ መቺ ሲሉ መናገራቸውን ሐራ ተዋሕዶ ዘገበ። ከዚህ ቀደም በሕይወት የሌሎት ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ማህበረ ቅዱሳንን አክራሪ ሲሉ በፓርላማ መናገራቸውን ያስታወሱ ምእመናን የሚ/ሩ ንግግር እንዳስቆጣቸው ለመረዳት ተችሏል። የሐራ ተዋሕዶ ዘገባ እንደወረደ ይኸው፦
‹‹በስደተኛው ሲኖዶስ የተሸፈኑና በማኅበረ ቅዱሳን የመሸጉ የትምክህት ኀይሎች የግንቦት ሰባትን ከበሮ ሲመቱ ከርመዋል››
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባዘጋጁትና ከነሐሴ ፳፩ – ፳፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በተካሄደው ‹‹አገር አቀፍ የሰላም እሴት ማጎልበቻ ጉባኤ›› ውይይት ከተካሄደባቸው ጽሑፎች መካከል የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ‹‹የአክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎችና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርእስ ያቀረቡት ጽሑፍ ይገኝበታል፡፡
በሰባት ንኡሳን አርእስት ተከፋፍሎ በስፋት የቀረበው ጽሑፋቸው÷ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ከሕገ መንግሥት አንጻር እንዴት እንደሚታይ፣ በአገራችን ይታያሉ ያሏቸውን የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዝንባሌዎች፣ አክራሪነትን/ጽንፈኝነትን የማስፋፊያ ስልቶችን፣ የአክራሪ/ጽንፈኛ ኃይሎች መነሻና መድረሻ ምስጢር፣ ሃይማኖትን ሽፋን ስላደረጉ የአክራሪነት አደጋዎች እና አክራሪነትን/ጽንፈኝነትን በአስተማማኝ ደረጃ ለማሸነፍ መሠራት ይገባቸዋል ያሏቸው ስድስት የመፍትሔ ሐሳቦች የተካተቱበት ነው፡፡
በሚኒስትሩ ጽሑፍ አክራሪነት/ጽንፈኝነት የሚለው ቃል የተበየነው በሦስት መንገዶች ነው፡፡ ይኸውም አክራሪነት/ጽንፈኝነት÷ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፳፯ ንኡስ አንቀጽ ፫ ዜጎች የፈለጉትን እምነት የመከተል መብት እንዳላቸው የተደነገገውን በመተላለፍ የሃይማኖትና እምነት ነጻነትን በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፳፭ ስለ እኩልነት መብት በሚደነግጋቸው ንኡሳን አንቀጾች በሃይማኖቶች መካከል የማበላለጥ ጉዳይ እንደማይኖር የተቀመጠውን ድንጋጌ በመጣስ የሃይማኖት እኩልነትን በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ ነው፤ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፲፩ ስለ መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት በግልጽ የተቀመጠውን ድንጋጌ በመፃረር መንግሥታዊ ሃይማኖት ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት ለመመሥረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው፡፡
አክራሪው/ጽንፈኛው ኃይል ደረጃው ይለያይ እንጂ በሁሉም ሃይማኖቶች ሽፋን እንደሚንቀሳቀስ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ዓለም አቀፋዊና ከባቢያዊ ገጽታም ያለውና የሚመጋገብ እንደኾነ ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ እኔን የሚመለከተኝ አይደለም የሚል ሃይማኖትና አገር ይኖራል ተብሎ እንደማይታሰብ፣ እንደየአገሩ የሕዝቦች በሰላም አብሮ የመኖር ታሪክ፣ ከድህነትና ኋላቀርነት ተጋላጭነት የመላቀቅ፣ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዐት የብዝሃነት አያያዝ ጥበቃ ዋስትና ሊለያይ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
በአገራችን በሁሉም ሃይማኖቶች (በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሽፋን፣ በእስልምና ሃይማኖት ሽፋንና በፕሮቴስታንት ሃይማኖት ሽፋን) የአክራሪነትና ጽንፈኝነት አስተሳሰብና ተግባር አራማጆች ከሃይማኖቱ መሪዎች ያልተላኩና መነሻቸውም መድረሻቸውም ሃይማኖታዊ ሳይኾን ፖሊቲካዊ መኾኑን ይጠቁማሉ፡፡
ከዚህ በታች ሚኒስትሩ ‹‹በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሽፋን›› ይታያል ለሚሉት ‹‹የአክራሪነት እና ጽንፈኝነት አስተሳሰብና ተግባር›› በማብራሪያነት የሰጡት ገለጻ ለሐራውያን ቀጥተኛ መረጃና ማገናዘቢያ ይኾን ዘንድ በጽሑፋቸው በሰፈረበት ይዘቱ ቀርቧል፡፡
* * *
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በንጉሡ ዘመን የመንግሥት ሃይማኖት እንደኾነች በ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት የተደነገገና እስከ ንጉሡ ሥርዐት መውደቅ ድረስ የቀጠለ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ በዚያን ዘመን ንጉሡና የገዥ መደቡ አካላት ለሥልጣን ማራዘሚያ፣ የጥቅም ማካበቻና የሌሎች እምነት ተከታዮችን በማሸማቀቅ አንድ አገርና አንድ ሃይማኖት ፍልስፍና ለማራመድ ተጠቅመዋል፡፡
በሌላ በኩል ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ሃይማኖት ገጽታ የተላበሰች ብትኾንም የውስጥ ነጻነት አልነበራትም፡፡ የጳጳሳትና የዲያቆናት ሹመት ሳይቀር በመንግሥት የሚወሰንና የሚጸድቅ ስለነበር መንፈሳዊም ይኹን አስተዳደራዊ ነጻነት ያልነበራት ነበረች፡፡ በሌላ በኩል የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ከገዥዎች አስተሳሰብ በተለየ ኹኔታ ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጋራ አብሮ በሰላም በመኖር የሺሕ ዓመታት ታሪክ የነበረው እንደኾነ ደጋግመን አውስተናል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ኾኖ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተረጋገጠው የሃይማኖት/እምነት ነጻነት፣ የሃይማኖቶች እኩልነት እና መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለው መርሕ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ክብርና ሞገስ፣ ታሪክና ጥቅም የነፈገ አድርገው የሚያስተጋቡ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች የሃይማኖት/እምነት ነጻነትን፣ የሃይማኖት እኩልነትን፣ መንግሥታዊ ሃይማኖትም ይኹን ሃይማኖታዊ መንግሥት እንደማይኖር የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ይጥሳሉ፡፡
ከሃይማኖት/እምነት ነጻነት አኳያ ሲታይ የሌላውን እምነት ትክክል ነው ብሎ ለመውሰድ ማንም እንደማይገደድ ቢታወቅም የሌላውን ሃይማኖት የተለያዩ ስያሜዎችን እየሰጡ የማብጠልጠልና የማሳነስ አመለካከትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ይታያሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ከሌሎች ሃይማኖት ጋራ እኩል ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፤ ይኽም ክብሯንና ታሪኳን የሚጎዳ ነው በሚል ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እንደማሳያም የአማኝ ቁጥራችን ብዙ ነው፤ ታሪካችን ረዥም ነው በሚል ለመከራከር ይሞክራሉ፡፡
ሃይማኖቶች እኩል ናቸው በሚል የተቀመጠው ድንጋጌ የአማኝ ቁጥርንና የሃይማኖቶችን ታሪክ የሚደፈጥጥ ሳይኾን የአገራችን ሕዝቦች እንደ ዜጋ በነጻ ፍላጎታቸውና ምርጫቸው የያዙት አመለካከት – ሃይማኖትና እምነት ከሌላኛው እንደማይበልጥና እንደማያንስ ብሎም ሁሉም ዜጎች የዴሞክራሲያዊ መብት ተጠቃሚ መኾናቸውን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ይህን ሕገ መንግሥታዊ መርሕ ዐውቀው በመጣስ በዙሪያው የትምክህት ኀይሎች የሚሰበሰቡበት ገጽታም የሚታይበት ኹኔታ አለ፡፡
በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሽፋን ከሚካሄዱት ቅስቀሳዎች ‹‹የበላይነትን አጥተናል፤ ይህንኑ መመለስ ይገባናል›› የሚል ሕገ መንግሥታችን የሻረውን አስተሳሰብ የሚደግፍ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ነች››፤ ‹‹አንድ አገር አንድ ሃይማኖት›› ወዘተ. . . ጉዳዮችን በማቅረብ በአንድ በኩል የአገራችንን የሃይማኖት ብዝሃነት የሚፃረር በሌላ በኩል ደግሞ አገራችን የሃይማኖቶች ብዝሃነት ነባራዊ መገለጫዋ መኾኗን የሚቃወም አካሄድ ነው፡፡
በሃይማኖት ሽፋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መንግሥታዊ ሃይማኖት መኾን ይገባዋል በሚል አቋራጭ የፖሊቲካ መሣርያ ለማድረግም የሚንቀሳቀሱ አካላት ይታያሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ የአክራሪነትና ጽንፈኝነት እንቅስቃሴ በዋናነት የሚታየው በተለያዩ የማኅበራት አደረጃጀት ውስጥ ራሳቸውን ደብቀው በሚሠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ነው፡፡ በእነዚህ ማኅበራት ውስጥ የመሸጉ አክራሪ ግለሰቦችና ቡድኖች በሚያሰራጭዋቸው የተለያዩ የኅትመት፣ የኤሌክትሮኒክስና የድረ ገጽ ውጤቶች በተከታታይ ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ሕዝብንና መንግሥትን የሚያጋጩ ዘገባዎችን በማስተጋባት የኢፌዴሪ መንግሥት የኦርቶዶክስ ክርስትናን ያሳነሰና ተገቢውን ክብርና ጥቅም የነፈጋት አድርገው ለምእመናን ያቀርባሉ፡፡
መንግሥት የሚያካሂዳቸው የልማት ሥራዎች መንግሥት የሚያሳያቸውን የገለልተኝነት ሚና. . .ወዘተ መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል በሚል ገሃድ ፍላጎትና ድብቅ አሠራር ካላቸው የውጭ ቡድኖች ጋራ በማበር ሰላምን አደጋ ውስጥ የማስገባትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱን በሃይማኖት ሽፋን ለመናድ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በቅርቡ በነበረው የፓትርያርክ ምርጫና በዋልድባ ገዳም ዙሪያ የተፈጠረው ዝንባሌ የነዚህ ፍላጎቶች ጉልሕ ማሳያ ነው፡፡
* * *
የአክራሪው/ጽንፈኛው ኃይል የማስፋፋት ስልቶች
የሃይማኖት ተቋማቱን የአመራር ዕርከኖች መቆጣጠር
አክራሪነትና ጽንፈኝነትን ለማስፋፋት ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አንዱ በሃይማኖት ተቋማትም ይኹን በመንግሥት መዋቅር ሰርጎ በመግባትና ደጋፊ በመምሰል በድብቅ መሠረቱንና መረቡን ማስፋፋት ነው፡፡ ይህን መሠረት የማስፋፋትና መረብ የመዘርጋት ተግባር ውጤታማ በኾነና በአጭር ጊዜ ማከናወን የሚቻለው የመንግሥትንም ይኹን የሃይማኖቶች አደረጃጀቶችን በበቂ ደረጃ መቆጣጠር ከተቻለ ነው፡፡
አክራሪነትና ጽንፈኝነትን ለማስፋፋት ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አንዱ በሃይማኖት ተቋማትም ይኹን በመንግሥት መዋቅር ሰርጎ በመግባትና ደጋፊ በመምሰል በድብቅ መሠረቱንና መረቡን ማስፋፋት ነው፡፡ ይህን መሠረት የማስፋፋትና መረብ የመዘርጋት ተግባር ውጤታማ በኾነና በአጭር ጊዜ ማከናወን የሚቻለው የመንግሥትንም ይኹን የሃይማኖቶች አደረጃጀቶችን በበቂ ደረጃ መቆጣጠር ከተቻለ ነው፡፡
በእስልምናም ይኹን በክርስትና ሃይማኖቶች ሽፋን የሚካሄደው የአክራሪነት/ጽንፈኝነት እንቅስቃሴ በዋናነት እያነጣጠረ የሚገኘው የተቋማቱን የበላይ አመራር ዕርከኖች መቆጣጠር ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚኾነው በቅርቡ በተካሄደው የእስልምና ምክር ቤቶች ምርጫ ወቅት ለአክራሪው ኀይል ለራሱ በሚበጅ መንገድ ካልኾነ ምርጫው ትክክለኛ አይደለም በሚል የዑላማ ምክር ቤት ፋትዋ ጭምር በመቃወም ያደረገው ሙከራ ነው፡፡
ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራዊ ኾኖ ከ8 ሚልዮን በላይ ሕዝበ ሙስሊም ወጥቶ የፈለገውን አመራር ከመረጠ በኋላ እስከ ፍርድ ቤት የሚሄድ ክሥ የመመሥረት፣ ሕዝበ ሙስሊሙ በራሱ ነጻ ፍላጎት መርጦ ያቋቋመውን መሪ ተቋም ማብጠልጠል የሚታይ የዘወትር ክሥተት አድርገዋል፡፡ አክራሪው ኀይል ‹‹የራሴ ብቻ ካልኾነ›› የሚለውን አመለካከት በግልጽ ያመላከተ ሂደት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ከምርጫ ሂደቱም በኋላ ከቀበሌ ጀምሮ የተመረጡ አመራሮችን በየዕርከኑ የራሱ ለማድረግ የሌት ተቀን ሥራውን በተለያዩ መደለያዎችና ማስፈራሪያዎች እየሠራ መኾኑ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡
በኦርቶዶክስ ሃይማኖት የ፮ኛው ፓትርያርክ ምርጫ ሲካሄድም በተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ተስተውለው እንደነበር ይታወቃል፡፡ የሚሾመው ፓትርያርክ ጉዳይ የራሱ የአማኙ መኾኑ እየታወቀና ራሱ ሲኖዶሱ አስመራጭ አካል ሠይሞ ከየሀገረ ስብከቱ በውክልና ከ800 በላይ መራጮች እንዲሳተፉ አድርጎ ያካሄደውን ሂደት በማብጠልጠል ‹‹መንግሥት ጣልቃ ገብቷል›› ስለዚህም የፍላጎታችንን መሾም አልቻልንም በሚል ለማስተጋባት ተሞክሯል፡፡
አክራሪው/ጽንፈኛው ኃይል የሃይማኖት ተቋማቱን የአመራር ዕርከኖች መቆጣጠር የሚፈልግበት ምክንያት ሕዝባችንን በተደራጀ መንገድ በበቂ ለማደናገርና ከዚያም ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዐታችንና ከሕገ መንግሥት ጋራ ፊት ለፊት ለማፋጠጥ ነው፡፡ ‹‹በሃይማኖትኽ መንግሥት ጣልቃ ገብቷል›› የሚለውን መፈክራቸውን የሁሉም ሕዝብ መፈክር በማድረግ በሕገ መንግሥታችንና በዴሞክራዊ ሥርዐታችን ላይ በተሳሳተ መንገድ ሕዝብን ለማዝመት ነው፡፡ ተቋማዊ ቁመናና ትስስር ተጠቅመው ገንዘቡንም ሕዝቡንም ለአክራሪነት ግባቸው ለማሰለፍ ስለሚመቻቸው ነው፡፡ የሃይማኖቱ ተቆርቋሪ መስለው አክራሪነቱን ለማስፋፋት ምርጥ ዕድል ስለሚኾን ነው፡፡
በተቃራኒው ግን ሕዝበ ሙስሊሙም ይኹን ሕዝበ ክርስቲያኑ ለአፍራሽ ፍላጎት ተገዥ እንዳልኾነ፣ ለሰላምና ልማት የቆመ ሕዝብ መኾኑን ደጋግሞ በተግባር አሳይቷቸዋል፡፡ በእነርሱ እኩይ ዓላማና ፍላጎት እንደማይገዛ፣ ሕገ መንግሥታችንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትን በኃይል ለመናድ ከሚንቀሳቀሰው ኃይል ጋራ እንደማይተባበር ፊት ለፊት በሰፋፊ ሰላማዊ ሰልፎች ጭምር ነግሯቸዋል፡፡
ስለዚህ አክራሪው ኃይል ቢቻል እነዚህን የአመራር ዕርከኖች ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ካልተቻለም ደረጃ በደረጃ እየሰረገና አቋሞቻቸውን እየሸረሸረ የራሱ ተቋም ለማድረግ ሰፊ ርብርብ ያደርጋል፡፡ ንጹሓን አማኞች ሁሌም ቢኾን ይህን አደጋ በንቃት በመጠበቅ ከመንግሥት ጋራ ተባብሮ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጉዳዩ ፀረ ሕገ መንግሥት አቋም እንደመኾኑ የሁሉም የሰላምና ልማት ኃይሎች ርብርብ የሚፈልግ ነው፡
No comments:
Post a Comment