Thursday, September 12, 2013

ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ለነፃነት መታገል ያስፈልጋል !!

እኔ እምለው ኢትዮጵያውያን አንድ  እንዳይሆኑ ተረግመዋል እንዴ?

ቃልኪዳን ካሳሁን
Ethnic Politics Split US Ethiopians  እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በመላው አለም በተለይ በአሜሪካ፣ እንደገና በተለይ በዋሽንግተን የሚኖሩ ብዙ ዜጎች አሏት፡፡ ከትግራይ ይሁን ከሶማሌ፤ ከኦሮሚያ ይሁን ከአማራ፣አፋር፣ደቡብ፣ቤኒ ሻንጉል፣ ድሬ፣ ሸገርብቻ ከየትም ይሂዱ ከየት የሁሉም ኢትዮጵያውያን የስደት መነሾ  በፖለቲካ አልያም የተሻለ ህይወት ፍለጋ ከመሆን አይዘልም፡፡
 (በሀገሩ መኖርማ ማን ይጠላል …)
ብዙ ጊዜ የማስበው ታዲያ ኢትዮጵያውያኑ በሰው ሀገር ሲኖሩ እንዳውም ከሀገር ውስጥ የበለጠ አንድነትና መግባባት ወይም አብሮ የመኖር ስሜት ይኖራቸዋል ብዬ ነው፡፡ በሰው ሀገር የመኖርን የህይወት ትግል ለመላመድና ለማሸነፍም ከሀገር ልጅ የበለጠ አለኝታ፣ አይዞህ/ ባይ እና አጋዥ የለምና፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች የምሰማው ግን ከዚህ በተቃራኒው የሆኑ እውነታዎችን ነው፡፡ በጥርጣሬ መተያየት፣ የብሔርና የፖለቲካ ክፍፍልሌላም ሌላም፡፡ እርግጥ ነው ሁላችንም አንድ አይነት አቋም ሊኖረን አይችልም፤ ከመሰረታዊ ጉዳዮች በስተቀር በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የግድ ተመሳሳይ ሀሳብ እንዲኖረንም አይጠበቅም፡፡ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ሊኖረን ይችላል፣ የተለያዩ ብሔሮች ልጆችም ልንሆን እንችላለን፤ ኢትዮጵያውያን በመሆናችን ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች በህልውናችን ላይ አንዳች ጥላ ማጥላት የለባቸውም፡፡ ደግሞም ከተቀራረብን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሊታረቁና ሁላችንንም የሚያስማሙ ሀሳቦችን ለመፍጠር ይቻላል የአፍሪካ የነፃነት ምሳሌ የሆንን ዜጎች ህብረ ብሔራዊ ውበታችንን በእያንዳንዳችን ፓስፖርት ላይ ካለው ኢትዮጵያዊነታችን ጋር የተጣበቁ የጋራ ተቀፅላዎቻችንን (stereotypes) በማጥፋት የትም ቦታ አንገታችንን ቀና አድረገን ለመኖር ምቹ ሁኔታዎችን ልንፈጥርበት ይገባል፡፡
ልዩነቶቻችንን በማቻቻል የትም ይሁን የት በአንድነት መስራቱ ለዜጎቿና ለኑሮ ምቹ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠርና ዳግም ኢትዮጵያን ታላቅ ለማድረግ ያስችለናል፡፡ ይሄም በቅርቡ እውን እንደሚሆን ተስፋ አለኝ!
ይኧዉ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስተዳድረዉ ወያኔ/ህውሃት የህዝብ መብት በመንቀፍ ፣ዘረኝነትን በማስፋፋት ፣ሃገርን በመከፋፈል ፣ጎሰኝነትን በማስተማር፣ አገር በመዝረፍ ፣አገርን በመሽጥ፣ ሰዉን ከሚኖርበት ቅዬ በማፈናቀል፣ በመቻቻል እንዳይኖር በማድረግ፣ ዘር ከዘር ጥላቻን ማስፈን፣ ቀጥሎበት ሃያ ሁለት ዓመታትን አስቆጠረ። እስከመቸ ይኧን ነገር ዝምብለን ማየት እንችላለን

እዚህ ጋር የሌሎች ሀገራት ዜጎችን በሚያስቀና መልኩ አብሮ የመኖርና የመተባበር ባህልና ማህበራዊ ህይወት ያላቸው ባህር ማዶ አደር ኢትዮጵያውያን እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይሁንና እነሱም ቢሆን እነዚህንና መሰል በኢትዮጵያውያን እህትና ወንድማማቾች መካከል እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡
ነጻነታችንን የቀሙን የወያኔ ዘረኞች ነጻነታችንን እንደቀሙን ለረጂም አመታት ለመግዛት እንዲመቻቸዉ በዘር፤ በቋንቋ፤ በክልልና በሐይማኖት ከፋፍለዉን ከሃያ አንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ዝብ ላይ ጀመሩትን እስራት፤ ስደት፤ ግድያና ዝርፍያ አሁንም እንደቀጠሉ ነዉ።  የወያኔ ዘረኞች ነጻነታችንን ቀምተዉ እየገዙን ቢሆንም ገዛናቸዉ ብለዉ እጃቸዉን አጣጥፈዉ አልተቀመጡም። ዜጎች ነጻነታቸዉንና መብታቸዉን እንዳይጠይቁ አፋቸዉን ያዘጋሉ፤ አንዱ ለሌላዉ አንዳይቆም አገር፤ ባንዲራና ኢትዮጵያዊነት የሚባሉ ትላልቹን የጋራ እሴቶቻችንን በየቀኑ ያፈርሳሉ። ይህ የሚያሳየን ዜጎች ትልቅ ተስፋ ይዘዉ ቤተሰብ መስርተዉ ለራሳቸዉና ለአገራቸዉ የሚኖሩበት ግዜ እየጠፋ ተስፋ መቁረጥ፤ ስደትና የመከራ ኑሮ ዘመን እየከበበን መምጣቱን ነዉ።  ይህ ከሆነ የነገዋን የነጻነት፣ የፍትህ፣ የዴሞክራሲ ባለጸጋ ኢትዮጵያን ለማየት እያንዳንዱ ዜጋ በቻለው አቅሙ ሁሉ ጠንክሮ በመታገል እና ከራሱ ባለፈ ሌላው ዜጋ  የነጻነት ትግሉን ጎራ እንዲቀላቀል ብሎም የዚህ ትግል ባለቤት እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡የሀገራችን ህዝብ የነጻነት ችቦ አቀጣጣይ የትግሉ አካል በመሆን መስራት እንጅ፣ ከቶ ሌላ አካል፣ ሌላ ሃይል መጦ ነጻ ያወጣኛል በሚል በባርነት እየተገዛ መጠበቅ የለበትም። ነጻነትና ዴሞክራሲ በችሮታ አሊያም ከሰማይ እንደሚወርድ መና የሚጠበቅ ስጦታ አይደለም። ነጻነት የራስን መሰዋእትነት ይጠይቃል።
 አለበለዚያ ላም አለኝ በሰማይ ወተትዋንም አላይ እንዳይሆን ያስፈልጋል።

ነጻነት እኛ ሰዎች በልደት ወደዚህ አለም ስንመጣ አብሮን የሚመጣ የተፈጥሮ ፀጋ ነዉ። ነጻነት ከሌሎች የምንጠብቀዉ ወይም ማንንም ስጠን ብለን የማንጠይቀዉ ፈጣሪ ለእያንዳንዳችን ያደለንን፤ በዚህ አለም ቆይታችን ለደቂቃም ቢሆን እንዲለየን መፍቀድ የሌለብን ኃብት ነዉ። ነጻነታችን እጃችን ላይ ሲኖር በግለሰብ ደረጃ የምንደሰትበት፤ እንዳንቀማ በጋራ የምንጠብቀዉና እንደወያኔ አይነቱ ፀረ ህዝብ ኃይል ሲቀማን ደግሞ በጋራ ታግለን ማስመለስ የሚገባን የግልና የጋራ ኃብት ነዉ። ዛሬ ከ22 የወያኔ አመታት በኋላ እኛ ኢትዮጵያዉያን በድህነትና በረሀብ የምንጠቃዉ፤ በዘረኝነት አለንጋ የምንገረፈዉ፤ የምንሰደደዉ፤ የምንታሰረዉና የምንገደለዉ  ይህንን ፈጣሪ ያደለንን ነጻነት የሚባል ኃብት ወያኔ አንድ፤ ሁለትና ሦስት እያለ ሲቀማን አፋችንን ዘግተንና እጃችንን አጥፈን ስለተመለከትን ነዉ።  መፈናቀላችን፤ ስደታችን፤ ዉርደታችንና በገዛ አገራችን ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ መኖራችን እንዲያበቃ ለማድረግ ያለን ብቸኛ አማራጭ ሌሎች መጥተዉ ነጻ ያወጡናል ከሚለዉ አመለካከት ተላቅቀን ነጻነታችንን ለማስመለስ ህዝባዊ ትግሉን መቀላቀል ብቻ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ የዘር በትር አለንጋ የሚደርስበት ግርፋት፣ ስቃይ፣ ርሃብ፣ ስደት፣ እንግልት በራሱ በህዝቡ ላይ ነው። ስለዚህ ህዝቡ ራሱ ለራሱ ነጻነት፣ በእምቢ አልገዛም ባይነት የሚነሳበት ጊዜው አሁን ነው። ነጻነትን ከነጻ አውጭዎች በመጠበቅ እስከመቼ የወያኔ የጥይት ሰለባዎች እንሆናለን?
ወገን ሁሉ ለራሱ ነጻነት፣ ህልውና ሲል የለውጡ እንቅስቃሴ ታጋይ የመሆን ኢትዮጵያዊ ግዴታውን እንዲፈጽም ጥሪ ማድረግ ይገባል ፡፡ ለአገሩ፣ለማንነነቱ መሰዋእትነት ለመሆን እንደሚኮራ ሁሉ አገሩም በሱ ትኮራለች ፡፡
ወያኔ 22 ዓመት ውስጥ የሰራው ወንጀል በወገናችን ላይ እንዲህ በቃላት ተዘርዘሮ አያልቅም።ይህ አልበቃ ብሎን።  ታዲያ ምንድን ነው አንድ ሆነን ከመታገል ፈንታ መለያየትን መረጥን!
 ኢትዮጵያውያን አንድ እንዳይሆኑ ተረግመዋል እንዴ?
ከቃልኪዳን ካሳሁን
kassahun.kalkidan@yahoo.no



No comments:

Post a Comment