ቁጥራቸው በቀላል የማይገመት ወገኖቼ ዘወትር ‘’ እኔ ፖለቲካ ውስጥ እኮ አልገባም፤ ፖለቲካ አልወድም፤ ፖለቲካን ለፖለቲከኞች ትተነዋል። ኤሌትሪክና ፖለቲካን በሩቁ ወዘተ…..” ሊሉ መስማት ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እንግዳ ነገር አይደለም። ይህንንም የሚሉት ስለሀገር ስለመንግስት አሰራር አንዳንድ ጨዋታ በሚነሳበት ጊዜ ነው። በርግጥም ታዲያ የለት ተለት ኑሮውን ከማሳደድ በቀር ሀገር እንዴት ዋለች እንዴት አደረች ህዝቡ ሰላም ነው ወይ መንግስት ምን እያለ ምን እያደረገ ነው? “ ብለው መጠየቅ የማይወዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ልክ የለውም።
ካንድ ወገኔ ጋር የግዚአብሄር ሰላምታ ከተለዋወጥን በሗላ “ ቤተሰብ እንዴት ነው? አገርቤት ሰላም ነው ወይ? ትደዋውላለህ ወይ? ‘’ እለዋለሁ።
“አዎ! ምን እባክህ ይሄ መንግስት ሰዉን ግራ እያገባው ነው፤ አሁን ደሞ አባይን እንገድባለን ደሞዛችሁን ልቀቁ ብሎ እያስጨነቀ ነው። በቀደም ለእናቴ ደውዬ ነበር። ምርር ብሏት ስትነግረኝ …. የኑሮ ውድነቱ እራሱ….”
ይህን የሚለው ሰው ዘወትር በተገናኘን ቁጥር ፖለቲካ አልወድም፤ አልከታተልም እያለ የሚነግረኝ ወገኔ ነው። እሱ ፖለቲካውን ቢሸሸውም ፖለቲካው ያለ እረፍት እየተከተለ ቤተሰቡን ሰላም ይነሳዋል። ያምሰዋል። በኑሮ ውድነት ይቀጣዋል። በደሞዙ ይቀጣዋል። ይህ ሰው ሸሽቶ አመለጠ? እውነታውን መጋፈጥ የተሻለ ቀን ሊያመጣ ይችላል። ሁሉም በራሱ ላይ ሲመጡበት ብቻ እንጂ የወገን ህመም የማያመው ከሆነ የሀገር ህመም የማያመው ከሆነ አብሮ ለመነሳት ጊዜ ይፈጃል። እርግጥ የወያኔ ገዢ ቡድን ያላቆሰለው ያላደማው የህብረተሰብ ክፍል የለም ብንልም፤ ያላሸበረው፤ ያላናደደው ክፍል የለም ብንልም፤ እነሱን ተለጥፎ ተጠቃሚ የሆነው ወገንና፤ እስካሁን በቀጥታ ዱላው ያላረፈበት ዱሮ የሚኖራትን ውሀ ልኳን የጠበቀች ህይወት በመኖር ላይ ያለ አንዳንድ ሰው ባያመልጥም ለስርዓቱ እድሜ መራዘም የቀጥታም ሆነ የእጅአዙር ድጋፍ ያደርጋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጦ እኔን አልደረሱብኝምና ምን አገባኝ የሚል ካለ ነገ ያገኘዋል። የሚያጣድፍ ነገር የለም። ያ ከመሆኑ በፊት ግን ለመቃወም መተባበር ምናልባትም አንባገነንነት በኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ተወግዶ የሕግና የሕዝብ ድምጽ የበላይነት ነግሶ የእውነቱን ዲሞክራሲ የምናይበትን ቀን ሊያቀርበው ይችላል። በተወሰኑ ሰዎች ጩኸትና ትግል ለውጥ ሊመጣ ጊዜ ይፈጃል። ዳር ሆኖ መመልከትና በጥቂቶች ብርቱ ጥረትና መስዋእትነት ድል የመጣ ቀን የድል አጥቢያ አርበኛ ሆኖ ብቅ ማለት ሊያስተዛዝብ ይችላል። ከ 66 ቱ አብዮት አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የሚደገፍ መንግስት፤ የሚታገሱት መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ኢትዮጵያን ሊያጠፋ ቆርጦ የተነሳ ህዝቡን በታትኖ መሬቷን ለባእዳን ሸጦ ሊያመልጥ የተዘጋጀ አደገኛ ቡድን በጦር ሀይል ህዝቡን ተቆጣጥሯል።
ለምሆኑ ፖለቲካ አያገባኝም የሚሉ ወገኖቼ ፖለቲካ የለትተለት ህይወታችን አካል መሆኑን አያውቁ ይሆን?…. ፖለቲካ ምንድነው?
ፍሪ ኦን ላይን ዲክሽነሪ ቃሉን እንዲህ ይፈታዋል።
ሀገርን ህዝብን የማስተዳደር ብልሀትና ዘዴ፤ የውስጥና የውጭ ጉዳዮችን የመምራት እውቀት፤የመንግስት ወይም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የሕዝብን ጉዳይ የሚያስተዳድሩበት አሰራር፤በፓለቲካ ቡድኖች መካከል የሚደረግ የስልጣን ፉክክር፤ ዜጎች ስለ መንግስት አሰራር ስለ ሀገር አስተዳደር ያላቸው እውቀት፤ አመለካከት፤
ይህንን ትርጉም መሰረት ስናደርግ፤ ፖለቲካ ፖለቲከኞች ወደ ግባቸው ሲያመሩ የሚነድፉት፤ የሚተገብሩት፤ የሚያከናውኑት፤ ማናቸውም ፡ ድርጊት ነው። ፖለቲካ በየሁላችንም ቤት አለ። ፖለቲካ የህዝብ አስተዳደር ስራ አፈጻጸሙ ነው ብለናል።
አንድ መንግስት በሀገር ውስጥ ከድሮ ጀምሮ የሚያመርተው የጨው ምርት አለ እንበል። በዚህ አመት አዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያወጣና በተወሰነ ደረጃ የሀገሪቱን የጨው ምርት የሚጨምር እርምጃ ይወስዳል። ማለትም ማምረቻ ጣቢያዎችን በማስፋፋት ይተገብርና ቀድሞ ከሚመረተው ተጨማሪ ጨው መመረቱን መሰረት በማድረግ፤ ከህዝቡ ብዛት ጋር ያለው ፍላጎት ከአቅርቦቱ ጋር መመጣጠኑን ለማወቅ በቂ ጥናት ሳያካሂድ፤ ቀድሞ ከውጭ ያስገባ የነበረውን ጨው ያስቆማል። በሀገር እየተመረተ ያለው በቂ ነው ብሎ በማመን። ከጥቂት ወራት በሗላ በሀገር ተመረተ የተባለው ጨው በፍጹም ህዝቡን የማያዳርስ ይሆንና ታይቶ ተሰምቶ ባልታወቀ ሁኔታ ጨው ከሀገር ይጠፋል። ሰዎች ያለጨው መመገብ የደረሱበት ደረጃ ይመጣል።
በዚህ ጊዜ እርሻ ውሎ፤ ወይም የቀን ስራውን ሲሰራ ውሎ ያገኛትን ለሚስት ሰቶ፤ የተሰራለትን በልቶ ወደ ተለመደ ተግባሩ ከመመለስ በቀር ምንም የማያውቀው አባወራ ከሚስት ጋር ጭቅጭቅ ይጀምራል።
“ አንቺ ሰው ምነው ያለጨው ታበይን ጀመር?”
“ ጨው ጠፍቷል።”
“ እንዴት ይጠፋል?’’
“ እንዴት አይጠፋም፤ እኔ ምናውቄ’’
“ ጨው ጠፍቷል።”
“ እንዴት ይጠፋል?’’
“ እንዴት አይጠፋም፤ እኔ ምናውቄ’’
ባልና ሚስት ሲጨቃጨቁ በመካከል ጎረቤት ይደርስና፤
“ መንግስት ከውጭ እንዳይገባ ከልክሎ ነው አሉ ’’ ይልና አቶ ባልን ያረጋጋል።
“ ለምንድነው የሚከለክለው? ”
“ ለምንድነው የሚከለክለው? ”
ይላል አቶ ባል። ፖለቲካ ኩሽና ገባች። ያ የሁሉም ጥያቄ ነው። ፖለቲካ።
በፖለቲካ እውቀት፤ ማለትም ባስተዳደር እውቀት የላቀ ችሎታ ያላቸው ሰዎችና ስኬታቸው የገነነ አሉ። ባንጻሩ የፖለቲካ ወይም የህዝብ አስተዳደር እውቀታቸው ድኩም የሆነና ውድቀታቸውን ያስከተለ ሰዎች አሉ። ወደ ታሪካዊው ምርጫ 97 እንመለስና በዚያን ጊዜ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ እውቀትና ችሎታ በማሳየታቸው መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማሳመን ለመማረክ በመቻላቸው በፖለቲካው ሰላማዊ ፉክክር የላቀ ተቀባይነት በማሳየታቸውም ሕዝቡ መረጣቸው። ባንጻሩ ወያኔዎች የፖለቲካ እውቀትድህነታቸውን፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎትና አመለካከት የማይወክል አስተሳሰባቸውን፤ ያስተዳደር ድንቁርናቸውን፤ ቀድሞ ህዝቡ ስለተረዳ ስላያቸው ችሎታውም ብቃቱም እንደሌላቸው በድርጊታቸውም በፕሮፓጋንዳቸውም ስላወቀው ሊማረክላቸው አልቻለም። ስለዚህ ድምጹን ነፈጋቸው፤ እንደማይፈልጋቸው አረጋገጠ፤ ወደቁ። ይህ ሁነት በፖለቲካ ስልጡን መሆን አለመሆንን የሚያሳይ አስረጅ ነው።
የፖለቲካ እውቀት ለማግኘት የግድ ትምህርት ቤት መሄድ አያስፈልግም። በለት ተለት ኑሮአችን ውስጥ መንግስት የተባለ ቡድን የሚያደርገውን የሚናገረውን መስማት ወሬ መለዋወጥ ማየት ነው። ያ ማለት ደሞ የቀበሌው አስተዳዳሪ የወረዳው የክፍለሀገሩ አስተዳዳሪ የዚያ የዚህ ቢሮ ሀላፊ ምናለ ምንአደረገ? እያሉ ዜና መለዋወጥ ነው። ሁሉም የመንግስትን ፖሊሲ፤ ህግ፤ ደንብ፤ መመሪያ ነው የሚያስፈጽሙት።
የፖለቲካ እውቀት የሌለው ወገን ማን እንደሚመራው እና እንደሚያስተዳድረው የማያውቅ ዝም ብሎ በእምነት የሚኖር ሕዝብ ማለት ነው። ይህ ባሕሪ ሰውን የዘለዓለም ተገዢ ያደርገዋል። አንባ ገነኖች የሚገዙት ህዝብ እነርሱ ከሚያቀርቡት ሰበካና የውሸት ዜና ውጭ አንዳይሰማ የሚፈልጉት ምን እያደረጉ አንዳለ እንዳያውቅና ጥያቄ አንዳያነሳ አንዳይቃወም ነው። የትግራይ ሕዝብ ከቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የበለጠ አፈና ውስጥ ያለ ነው። በወያኔ ፖለቲካ ያን ሕዝብ ከሌላው በከፋ ሁኔታ አፍኖ መያዙ ወደፊት በስልጣን ላይ የመዝለቅ ትልም ስላለ ከሌላው የሀገሪቱ ክፍል ሊነሳ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል የትግራይን ህዝብ በነመለስ ዜናዊ የፈጠራ ታሪክና ወሬ አውሮና አደንቁሮ ማስቀመጥ፤ በቁጣ ለማስነሳት እንዲመች ማድረግ የወያኔ ዘላቂ የፖለቲካ ግብ ነው።
የፖለቲካ ስራ ውስብስብና ሁለገብ ነው። ጥፋትና ልማቱን ማንም በአጭር ጊዜ ሊረዳ የማይችልበት ሁኔታም አለ። የቅኝ ዘመን ካከተመ በሗላ ባፍሪካ ውስጥ ለረጅም አመታት የተካሄዱ የርስበርስ ውጊያዎች መሰረታቸውን የጣሉት ቅኝ ገዚዎች ከፋፍሎ የመግዛቱን አማራጭ ለስልጣን ዘመናቸው መራዘም እንደ ፍቱን መድሀኒት በመያዛቸው ነው። ነጻነታቸውን ሲሰጧቸውም አንድ ሆነው እንዳይቀጥሉ የፖለቲካ ፈንጂ እየቀበሩ መሄዳቸው የተለመደ ነው፡ እንግሊዞች ጣሊያኖችን ተክተው ለአስር ዓመታት ኤርትራ ቆይተው ሲወጡ አንድ እንግሊዛዊ ኮሎኔል አቋቁሞት የሄደው የነጻነት ንቅናቄ ሲወድቅ ሲነሳ ሲቆረጥ ሲፈለጥ ሻእቢያ ላይ ደርሶ ሀገራችንን ለማፍረስ በቃ።
የማናቸውም ሀገር ማእከላዊ መንግስት ሲዳከም፤ ሐገር ራስን የመከላከል አቅም ሲጠፋው፤ ሀይልና ብርታት የሚያገኙ የጥፋት ድርጅቶች አሉ። እነዚህ ድርጅቶች በሳንባ ነቀርሳ ተውሳክ ይመሰላሉ። የሳንባ ነቀርሳ ተውሳክ ወደ ሰውነታችን ሲገባ፤ ስንለከፍ ከመቶ አስሩን ሰው ወዲያው ቢያጠቃ ነው። ሰውነቱ ራሱን ከበሽታ የመከላከል አቅሙ የተዳከመ ሰው በሽታው ይገንበትና ይሞታል። ሰውነት የመከላከል አቅሙ ጠንካራ ከሆነ ግን የሳንባ ነቀርሳ ተውሳክ ራሱን እንደበድን ያደርግና ሳይሞት ዝም ብሎ በሰውነታችን በደማችን ውስጥ አብሮን ለዘለአለም ይኖራል። አንድቀን ሰውነት ራሱን ከበሽታ መከላከል ሲያቅተው ያ ተውሳክ ካደፈጠበት አንገቱን ብቅ ያደርግና ይለመልምና ተስፋፍቶ መላ ሰውነታችንን ይወራል። በሽታው ይገናል። ሰው ይሞታል።
ለጥፋት የተፈጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶችም በሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች እንክብካቤና ኩትኮታ ከተፈጠሩ በሗላ ለረጅም ጊዜ ይኖራሉ።አንድቀን ሀገር ራስን የመከላከል አቅም ሲያንሰው ማእከላዊ መንግስት ሲዳከም እንደሳንባ ነቀርሳ ተውሳክ ባጭር ጊዜ ይገናሉ። ለዚህ ወያኔና ሻእቢያ በኢትዮጵያ አንጻር የተቀዳጁትን ድል ለዋቢ መጥቀስ በቂ ነው።
ፖለቲካ ያንድን ሀገር ህዝብ በነቂስ የሚነካ የለትተለት ኑሮ አካል ነው። ባስተዳደር ረገድ እንዴት እንደሚኖር ወዴት እንደሚኬድ ትልሙ የሚዘጋጀው በፖለቲከኞች ነው። ሕግና ስርዓት ይወጣል። ግለሰባዊ ደህንነታችንን ለመጠበቅ ሀገርና ሕዝብን ከወንጀለኞች ለመከላከል ፖሊስና ፍርድ ቤት ይደራጃል። ሀገርን ከጠላት ለመከላከል ጦርሰራዊት ይደራጃል። በሽታን ለመካላከል የጤና ተቋማት ይደራጃሉ። ወዘተ… ያስተዳደር ስራ ነው። የፖለቲካ ስራ ነው።
ፖለቲካ ያንድን ሀገር ህዝብ በነቂስ የሚነካ የለትተለት ኑሮ አካል ነው። ባስተዳደር ረገድ እንዴት እንደሚኖር ወዴት እንደሚኬድ ትልሙ የሚዘጋጀው በፖለቲከኞች ነው። ሕግና ስርዓት ይወጣል። ግለሰባዊ ደህንነታችንን ለመጠበቅ ሀገርና ሕዝብን ከወንጀለኞች ለመከላከል ፖሊስና ፍርድ ቤት ይደራጃል። ሀገርን ከጠላት ለመከላከል ጦርሰራዊት ይደራጃል። በሽታን ለመካላከል የጤና ተቋማት ይደራጃሉ። ወዘተ… ያስተዳደር ስራ ነው። የፖለቲካ ስራ ነው።
ፖለቲካ ማለት ለፓርላማ ለመወዳደር መሮጥ ንግግር ማድረግ ብቻ የሚመስላቸው አሉ። ፖለቲካ መንግስትን መተቸት ስለመንግስት መጥፎ ነገር መናገር ብቻ የሚመስላቸው አሉ። ያብቻ አ ይደለም። ከርእሰ ብሄር እስከ ቀበሌ ሊቀመንበር የሚሰራው ስራ ሁሉ የሚፈጸመው መመሪያ ሁሉ ፖለቲካ ነው። ስለ አስዳደር ንቅዘት፤ ስለ ፍትህ መጓደል፤ ስለ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የምንጠይቀው የምንናገረው ሁሉ ፖለቲካ ነው።ያስተዳደር ስራ ውጤት ነው።
ፖለቲካ አልወድም፤ ስለፖለቲካ አያገባኝም፤ ማለት ሀገርንም ህዝብም ማንም መንግስት ነኝ ያለ ሁሉ እንደፈለገ ያድርገን፤ ማንም አስተዳዳሪ ነኝ ያለሁሉ እንደፈለገ ያድርገን እንደበሬ ጠምዶ ይረስብን ልክ ነው ማለት ነው።
ወያኔ ዛሬ አይናችን እያየ የሀገራችንን ለም መሬት በሙሉ በባእዳን እያስያዘ ነው። ከሀምሳ ዓመት እስከ መቶ አመት በሚደርስ ኮንትራት ቶሎ ቶሎ እየሸጠነው። ዝምብለን ማየት ይዘናል። አልሸፈትንም። ጦርነት አላነሳንም። ከአርባ ዓመት በሗላ በኢትዮጵያ ውስጥ የህዝቡም የ እንስሳቱም ቁጥር መተናፈሻ እስኪጠበው ይበዛል። በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያን መሬት በሙሉ ከ አለም ላይ የተሰበሰቡ ባእዳን መንግስታት ተቆጣጥረውታል። ሀገሬ ብሎ ማንም ኢትዮጵያዊ የማንንም ይዞታ መርገጥ አይችልም። የዚያን ጊዜ የመሬቱ ባለቤት የሚሆነው ነጭ፤ አረብ እናም እስያዊ ነው። መቆሚያ መቀመጫ ለማግኘት ልጆቻችን ወደጦርነት መግባት ከአለም አቀፍ ወራሪ ጋር ለመዋጋት ሊገደዱ ነው። እኛ ዛሬ ወያኔን ለማቆም እንቅስቃሴ ብናነሳ ልጆቻችንን ከመከራ እናድናለን። እስካሁን ምንም እያደረግን አይደለም። ወያኔ አቅዶ የተነሳውን የጥፋት ተልኮ ሁሉ ያለምንም ሳንክ በዚች ሀገር ላይ ተግብሮ ካጠናቀቀ ኢትዮጵያውያን እንደምናወራው ጀግኖች አይደለንም። የመጨረሻ ፈሪዎች ነን።
ዊኪፒዲያ ኢንሳይክሎፒዲያ ፖለቲካን እንዲህ ይፈታዋል።
ሰዎች በጋራ ውሳኔ የሚያስተላልፉበት ሂደት ነው። መንግስት ስራውን የሚያከናውንበት ዘዴና ጥበብ ነው። የሕዝብ አስተዳደር ጥበብ ነው። የህዝብና የመንግስት የለት ተለት ግንኙነት ነው።
መንግስት በለት ተለት ከህዝብ ጋር የሚያገናኘው ያስተዳደር ስራው ነው። ሕዝብ ማለት ደግሞ እያንዳንዱ ሰው ተደምሮ አንድ አገር በሚባለው ምድራዊ ክልል ውስጥ የሚኖር ሁሉ ነው።ስለፖለቲካ አያገባኝም ከተባለ አሸባሪ ነህ ብሎ አንድ መንግስት ልጄን ከቤት ጎትቶ አውጥቶ ሲገለው አልናገርም፤ ይበለው ለራሱ ብሎ ነው፤ አልጠይቅም አልቃወምም ማለት ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሀያ ዓመታት እስከ 50 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ እርዳታ በ አይነትም በገንዘብም አግኝታለች። ወያኔ ይህን ገንዘብ ተረክቧል። ደርግ ስልጣን ላይ በቆየበት 17 ዓመታት ለጦርነት ይወጣ የነበረው የቀን ወጪ በአማካይ 30 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ነበር። ጦርነቱ አስራ ሰባቱንም ዓመታት ተካሂዷል። እንደዚያም ሆኖ ብዙ ነገር ተገንብቷል። ወያኔ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በሗላ ሀያ አመታት ተቆጠሩ። ከሻእቢያ ጋር የተደረገ አጭር ጦርነት በቀር የጦርነት ወጭ የለም። እንዲያውም ወያኔ ጦሩን ለጦርነት እየላከ ገቢ እያገኘበት ነው። ሐያውን አመት ከጦርነት ወጪ የዳነው ገንዘብ ከተገኘው እርዳታ ጋር ተደምሮ በተገቢው ሁኔታ ስራ ላይ ቢውል ባግባቡ ልማት ላይ ቢውል፤ ቢያንስ በያመቱ የሚመላለስብን ርሀብ አንድ ቦታ ላይ መቆም ነበረበት። ይህ ገንዘብ የት ሄደ? ለምንድነው ዛሬም የሚርበን ብሎ መመርመር የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሞራል ግዴታ ነው። ፖለቲካ አልወድም ካልን ደሞ ወያኔ መላ ሀገሪቱን ሸጦ ህዝቡንም በትኖ አስኪሄድ ተቀምጠን እንመልከት። ልጆቻችንም መከራ ይውረሱ። ልጆቻችን የሚያፍሩብን አባቶች እኛም ከሞትን በሗላ መቃብር ይደርመስብን ። ኢትዮጵያ ግን ለዘላለም ትኑር። አንድቀን እንዳባት እንዳያቶቻችን ጀግኖች ልጆች ዳግም ትወልድና ትንሳኤዋ ይሆናል።
No comments:
Post a Comment