Tuesday, September 10, 2013

‹‹አዲስ›› ዓመት!

ሳስበው ‹‹አዲስ›› ዓመቶች በተለይ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የዓመት ቁጥር ለውጥ እንጂ የግብር ለውጥ አይታከልባቸውም፡፡ የምናያቸው ምኞቶች ‹‹መመኘት ካልቀረ›› በሚል ፈሊጥ የሚቀርቡ ይመስለኛል፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የብልጽግና፣ የደስታ…. የሚሉ ምኞቶች ቃሎቹ እንጂ አብረውን ያሉት እሱን ተከትለው ተግባር የሚጠይቁት ነገሮች ላይ ምንም ነገር ለማድረግ ዝግጁ አይደለንም፡፡ ገዢዎቻችን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የዘመኑ ቱባ ሰዎች አዲሱ ዓመት የደስታ፣ የለውጥ፣ የብልጽግና ወዘተ እያሉ እየተመኙ ግብራቸው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ያለፉትን ስንት ዓመታት ታዘብናቸው፡፡ 
በአዲስ ዓመት ብልጽግና እየተመኙልን በተቃራኒው ሲያደኸዩን፣ አዲሱ ዓመት ደስታ እንዲያመጣ እየተመኙ ግን በሀዘን ቅርቃር ሲሰገስጉን፣ ጤና እንድናገኝ በተመኙበት አዲስ ዓመት አዲስ በሽታ ፈጥረው ከአልጋ ሲያውሉን አየናቸው፡፡ ምኞት ኪስ አይገባም፣ ሚጢጢ 'ሚስቃለ ዘረቲ' እንዲል መጽሐፉ ስራ ግን ኪስ እና ቀልብ ይገባል፡፡ ከምኞታችን በፊት ምኞታችንን እውን ለማድረግ ቁርጠኝነት በልባችን ቢሰፍን ብዙ ለውጥ በአንዲት ጀንበር እንቆጥራለን፡፡ ስለዚህ ከምኞት ጋጋታ የለውጥ መሻት በልባችን ይኑር፡፡ ምኞትና ፍላጎት ለየቅል እየሆኑ ተቸግረናል፡፡ 
እንደእኔ የተስፋ ጭላንጭል ከወዲያ ማዶ ለታያችሁ ሁሉ ተስፋችሁ ለምልሞ እውን ሆኖ የምታዩበት ሌላ ዓመት ይሁንላችሁ፡፡ 
ለማንኛውም መስከረም በሚጠባበት ወቅት መስክ ላይ የማናገኘው አደይ አበባ የአዲስ ዓመት ምልክት ሆኖ በመቀመጡ ለምልክትነት እነኾ በረከት፡፡

No comments:

Post a Comment