ይድነቃቸው ከበደ
የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ሃላፊ
የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ሃላፊ
ነሀሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሰማያዊ ፓርቲ ታላቅ የተቃውሞ ሠልፍ መጥራቱ የሚታወቅ ነው፤ ይሁን እንጂ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እንደሰፈር ጉልበታኛ ዱንኳን ሰባሪ ዘው ብሎ በሃይማኖት ስበብ ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ቀንና ሰዓት እንዲሁም ቦታ በህግ አግባብ ሣይሆን በጉልበት ሠልፍ መሰል ሠልፍ ማካሄዱ የሚታወቅ ነው፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም የተቃውሞ ሠልፍ በማድረግ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የተቃውሞ ሠልፈኞች እንዲሁም የአገር ውስጥና የውጪ የመገናኛ ብዙሃን በተገኙበት መንግስት ሊመልሳቸው የሚገባ ጥያቄዎችን የጠየቀ ሲሆን ለጥያቄዎቹም ምላሽ የሰጠው የጊዜ ገደብ ሦስት ወር መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
ይሁን እንጂ መንግስት በተሰጠው ጊዜ የተጠየቀውን ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ፓርቲውን በመወንጀል እና ስም የማጥፋት ዘመቻውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት ላሣየው ቸልተኝነት እርማታ እንዲያደርግ በመግላጫ የጠየቀ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ከ1 ወር በፊት በፓርቲው ጽ/ቤት በተሰጠ መግለጫ ነሀሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም ፓርቲው ቀድሞ ለጠየቃቸው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ በድጋሚ በተጠናከረ መልኩ የተቃውሞ ሠልፍ መጥራቱን ለመንግስትም ለህዝብም ተገልፃል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በሠላማዊና በህጋዊ መንገድ የሚታጋል እንደመሆኑ መጠን ለአ/አ መስተዳደር በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀፅ 30 ንዑሰ አንቀፅ 1 መሰረት በማድረግ ነሀሴ 13 ቀን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት የሰላማዊ ሰልፍ ስብሰባ ማሳወቂ ቢሮ ነሀሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም የተቃውሞ ሠልፍ አንደሚያካሂ ያሳወቀ ሲሆን፤ የከንቲባ ፅ/ቤት የሰላማዊ ሰልፍ ስብሰባ ማሳወቂ ቢሮ ነሀሴ 15 ቀን ለፓርቲው በላከው በአስቸኳይ የደብዳቤ መልዕክት ሦስት ጥያቄዎችን ለፓርቲው ሲጠይቅ ሰማያዊ ፓርቲ ነሀሴ 17 ቀን የተጠየቁትን ጥያቄ በመመለስ የማሰወቂያ ደብዳቤ አስገብቷል፡፡
ይሁን እንጂ የከንቲባ ፅ/ቤት የሰላማዊ ሰልፍ ስብሰባ ማሳወቂ ቢሮ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጠም፤ይህ ደግሞ የማሳወቂያ ደብዳቤ ከገባ በ48 ሰዓት ውስጥ ምንም ዓይነት ምላሽ ካልተሰጠ የተጠራው የተቃውሞ ሠልፍ እውቅና እንዳለው ይቆጠራል ተብሎ በአዋጅ ተደንግጎ ይገኛል፡፡በዚህም መሰረት ሰማያዊ ፓርቲ በ48 ሰዓት ውስጥ ምንም ዓይነት ምላሽ ስላልደረሰው የህጉን ስርዓት ጠብቆ ለተቃውሞ ሠልፉ ዝግጅቱን አጠናክሮ በመቀጠል ላይ እንዳል ነሀሴ 20 ቀን የሀይማኖት ጉባሄ የተባለ በመንግስት ድጋፋ የሚንቀሳቀስ አካል ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ቀንና ሰዓት እንዲሁም ቦታ ሠልፍ መጥራቱ ታወቀ፡፡
ይህ ደግሞ ተገቢ አለመሆኑ ምን አልባትም ከመረጃ እጥረት ከሆነ ወይም ሌላ ምክንያትም ቢኖርም ሰማያዊ ፓርቲ የህግ አግባብ ተከትሎ ቀድሞ የያዘው ፕሮግራም መሆኑ እና ለተፈጠረው የፕሮግራም መደራረብ መንግስት በአስቸኳይ ማስተካኪያ እንዲያደርግ፤ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለሚፈጠሩ ማናቸውም ችግሮች መንግስት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ሰማያዊ ፓርቲ በሰጠው መግለጫ አሳስቧል፡፡
ይህ በእንዲ እንዳለ ነሀሴ 24 ቀን 2005 ዓ.ም የአዲስ አበባ ፖሊሲ ኮሚሺን ሦስት የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችን የንወያይ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችም ጥሪውን በማክበር በቦታው ተገኝተዋል፡፡‹‹የአ/አ አስተዳደር ፓርቲያቹ ለጠራው የተቃውሞ ሠልፍ እውቅና አልሰጠም በዚህም መሰራት ሰልፉን ማካሄድ አትችሉም›› በማለት ፖሊስ መስጠንቀቂያ የሰጠ ቢሆንም ፤ የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ‹‹ ፖሊስ ይህን የማለት መብት የለውም፤ የአ/አ አስተዳደር ፓርቲያችን ላስገባው ደብዳቤ በ48 ሰዓት ውስጥ የሰጠው ምንም ዓይነት ምላሽ የለም ይህ ደግሞ የጠራነው የተቃውሞ ሠልፍ የህግ አግባብነት ያለው ነው፤በመሆኑም ምንም ዓይነት የህግ ስእተት ባለመፈጸማችን ሰልፉን እናካሂዳልን በዕለቱም ፖሊሲ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለበት››በማለት አሳባቸውን ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ሰማያዊ ፓርቲ ዝግጅቱን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ነሀሴ 25 ቀን 2005 ዓ.ም ከ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ የፓርቲው አመራሮችና አባላቶች እንዲሁም ደጋፊዎች በፓርቲው ጽ/ቤት ቅጥር ጊቢ በማግስቱ እሁድ ለሚደረገው የተቃውሞ ሠልፍ እጅና ጎንት በመሆን ከምንም በላይ በሚያስቀና ጎዳዊ ስሜት ሲንቀሳቀሱ ማየት ብርታትም ፍቅርም የሚሰጥ ነው፡፡ይሁንእንጂ በመንግስት ሚዲያ በዕለቱ ማለትም ቅዳሜ ከ 7 ሰዓት ጀምሮ በማከታተል ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው የተቃውሞ ሠልፍ ህገ-ወጥ መሆኑና ሠልፉ ቢካሄድ ፓርቲው ሃላፊነቱን እንደሚወስድ በፖሊስ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎ በአባላቶች መካከል ሠልፉ ይካሄዳል ወይስ ምን ይሆን በማለት የእርስ በእርስ ንግግር ሲያደርጉ ሞቅ ሞቅ ያለው እንቅስቃሲ ከዝናቡ ጋር ተዳምሮ በጊቢ ውስጥ ቀዝቃዛ ስሜትን ፈጠረ፡
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አስቸኳይ ስበሰባ በማድርግ ፖሊስ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግ ላይ እያሉ አባላቶች ከስብሰባው ምን አይነት ውሳኔ ይተላለፍ ይሆን በማለት በጉጉት ይጠብቁ ነበር፡፡የፓርቲው አመራሮች ስብሰባ እንደጨረሱ ከአበላት ጋር በመሰብሰብ አመራሩ የደረሰበትን ውሳኔ የተቃውሞ ሠልፉ እንደሚካሄድ መንግሰት አየተከተለ ያለው የህግ ጥሰት አገባብ እንዳልሆነ እና ይህን አስመልክቶ የተቃውሞ ሠልፉ አብይ መፈክር ‹‹ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ዘመቻ›› እንደተባለና አባላቶች አጠናክረው ስራቸውን እንዲቀጥሉ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ላይ መደረሱን ሲገልፁ በስብሰባው ላይ የተገኙ አባላቶች ጭብጨባና ደስታ እንዲሁም ያሳዩት የነበረው ቁርጠኝነት አመራሩ ያስተላለፈው ውሳኔ ትክክለኝነትን አጉልቶ የሚያሳይ ነበር፡፡
ዘመቻ ለህግ የበላይነት ከ10፡30 ጀምሮ በጊቢ ውስጥ እንደ ፍም እሳት ይፋጅ ጀመረ፤ አገራዊ ሙዚቃዎች ድምፃቸው ከፍ ብሎ ሲሰማ ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው እንደሚባለው ወጣትና አንጋፋ የፓርቲው አባላቶች የፓርቲውን ዓርማ በመያዝ ያሳዩት የነበረው እንቅስቃሴ እና ለአገራቸው ያላቸው ተቆርቋሪነት እንዴት ያለ የአገር ፍቅር ልክፍት ነው ? ያስብላል፡፡ወጪ ወራጁ መንገደኛ ሲጀምር የአግርሞትና አድናቆት እይታ ሲብስበት ተቀላቅሎ የድረጊቱ አንደ አካል ለመሆን ያሳይቱ የነበረው እንቅስቃሴ ሌላው አስደሳች ክስተት ነበር፡፡
ዘመቻ ለህግ የበላይነት በሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት ማምሻውን በድምቀት እየተካሄደ እንዳል በ4 የተለያዩ መኪናዎች ተጭነው የመጡ ሙሉ የጦር መሳሪያ ትጥቅ የታጠቁ የፌዴራል ፖሊሶች የፓርቲው መውጫና መግቢያ መንገዶችን በ50 ሜትር ዙሪያ በቅድሚያ ከበባ አካሄዱ፤ ቀጥሎም ቁጥራቸው ወደ 30 የሚጠጎ ሌሎች የፌዴራል ፖሊሶች የፓርቲው ጊቢ ጥሰው በመግባት መስኮትና በር በሃይል በመስበር ወደ ቤሮ በመግባት አባላትን በማገት በቤሮ ውስጥ የሚገኝ ንብረቶችን በማውደም የተቀሩትን በመኪና በመጫን ካሸሹ በኃላ የፓርቲው አመራርና አባላትን በመኪና ይዘው ሳይሆን ጭነው ወደ ጃንሜዳ ፖሊስ ጣቢያ ይዟቸው ሄዱ፡፡
ወጣትና አንጋፋ የፓርቲው አባላቶች በጃንሜዳ የጠበቃቸው ነገር መጀመሪያ ሁሉም የሞባይል ስልካቸውን እንዲያጠፉና እንዲያስረክቡ፤ቀጥሎም ጫማቸውን እንዲያወልቁና እንዲንበረከኩ ሲሆን ከዚህ በኃላ የሆነው ነገር ስሜትን የሚነካና የሚያስቆጭ ነው፡፡ በፖሊስ ጣቢያ ጊቢ ውስጥ በሚገኝ የሽንት መውረጃ ቆሻሻ ቦታ ላይ በጀርባ በማስተኛት በብረትና በዱላ ፍፁም ሰብአዊነት በገደለው ሁኔታ አህያ እንኳን የማይችለውን ዱላ በሰው ገላ ላይ ፖሊስ ድብደባ ፈጸመ በዚህም ምክንያት በአባላቶች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደረሰ፡፡
ይህ አይነቱ ኢሰብአዊ ድረጊት ከምሽቱ 3፡30 ፍፃሜ አገኘ ፤ወጣትና አንጋፋ የፓርቲው አባላቶች አብዛኞቹ ቆመው ለመሄድ በጣም ይቸገሩ ነበር ፤መኖሪያ ቤታቸው ቅርብ የሆኑ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ ራቅ የሚሉት ደግሞ በጉሩፕ በመሆን ሰብሰብ በማለት በተለያዩ የፓርቲ አባላት መኖሪያ ቤት ለማደር ችለዋል፡፡
ወጣትና አንጋፋ የሰማያዊ ፓርቲ አባላቶች ይህን ሁሉ የዱላ ውርጂብኝ በመቋቋም በድጋሚ እንዲ ሲሉ ዘመሩ፤
የትግል ጉዞው ታሪካዊ
ዓላመው ፍጹም ህዝባዊ
ራዕይችንም ኢትዮጵያዊ
ሰማያዊ ሰማያዊ
ፓርቲያችን ነው ሰላማዊ
No comments:
Post a Comment