Thursday, September 5, 2013

ሰልፉን የምቀላቀልባቸው ምክንያቶች

ጌታቸው ሺፈራው
ታይቶ ከጠፋው የ1997 ምርጫ በኋላ ለአለፉት 8 አመታት ከድጋፍ ሰልፍ ይልቅ የህዝብ ሮሮ የሚሰማባቸው ሰላማዊ ሰልፎች በግልጽም ሆነ በተዘዋዋሪ ታግደው ቆይተዋል፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ እንደገና ብቅ ያለው በኢህአዴግ ጉባኤ ምክንያት የፓርቲው አመራሮችና ካድሬዎች ባህርዳር በከተሙበት መጋቢት 2005 መጀመሪያ ወር ነው፡፡
መጋቢት 6/2005 ዓ/ም የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር፣ እነ ታዲዮስ ታንቱ የሚመሩት አንድ ተቆርቋሪ ቡድንና ሰማያዊ ፓርቲ የግራዚያኒን መታሰቢያ ተቃውመው ሰልፍ ወጡ፡፡ የጣሊያን ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንኳ ያወገዙትን የጨፍጫፊውን መታሰቢያ የኢትዮጵያ መንግስት ቀድሞ መቃወም ሲኖርበት ሰላማዊ ሰልፍ የወጡትንም ለቃቅሞ እስር ቤት ከተታቸው፡፡ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ለአንድ ቀን ያህል ቢታሰሩም ባለፉት አስር አመታት አይኬ ተደርጎ ይቆጠር የነበረውን የፍርሃት ግንብ ግን በመጠኑም ቢሆን ሰርስረውት ተመልሰዋል፡፡ ይህ የሰላማዊ ሰልፍ ሙከራ ሰላማዊ ሰልፍን እንደ መብት ለህዝብ ለማስመለስ ካደረገው ተጽዕኖ በተጨማሪም የአገሪቱን መንግስት ነኝ ያለውን አካል ለብሄራዊ ጥቅሙ እንደማይጨነቅ  በግልጽ ያሳየ ነበር፡፡

የመጋቢቱ ሰልፍ አንድ አካል የነበረው ሰማያዊ ፓርቲ የአፍሪካ ህብረትን 50ኛ አመት የሚከበርበት እለት ላይ ሌላ ሰላማዊ ሰልፍ ቢጠራም ‹‹መንግስት›› ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ በአንጻሩ ሰልፉ ስብሰባው ካበቃ በኋላ ግንቦት 25 ቀን እንዲሆን ‹‹ተፈቀደ››፡፡ በእርግጥ በዚህ ሰልፍ ላይም ኢህአዴጎች ተስማምተውበታል ለማለት አያስደፍርምል፡፡ ይሁንና ባህርዳር በነበሩበት ወቅት የግራዚያኒን መታሰቢያ ተቃውመው በመውጣታቸው የታሰሩት 43 ሰዎች መሆናቸውን አዲስ አበባ ከነበሩት አሳሪዎች የሰሙት የኢህአዴግ አመራሮች ሰማያዊ ፓርቲ ብቻውን የሚጠራው ሰልፍ ይህ ነው የሚባል ህዝብ ሊገኝበት እንደማይችል የገመቱ ይመስላል፡፡
ከዚህም ባሻገር ሰማያዊ ግንቦት 17 ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ ባይሳካለትም ስርዓቱ ያች ቀን ትንሽም ድምጽ ኮሽ ከሚል የግዱን ሌላ ተለዋጭ ቀን እንዲሰጥ ቅርቃር ውስጥ የከተተ ነበር፡፡ እነዚህና ሌሎችም ምክንያቶች ተዳምረው ሰማያዊ የጠራው ሰልፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንደ መብት እንደገና ለህዝብ የተመለሰበት ወቅት ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ከሰማያዊ ፓርቲ ይህን ያህል እውቅና ባይሰጠውም ዞን ዘጠኝ ያደረጋቸው ተደጋጋሚ የበይነመረብ ዘመቻዎች ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
ከሰልፉ በኋላ የመንግስት ባለስልጣናትም ሆኖ ሚዲያው ፓርቲውን ለመክሰስ አልቦዘኑም፡፡ አንድነት ፓርቲ እስካሁን ድረስ እያደረጋቸው የሚገኙት ሰልፎች ላይ ኢህአዴግ ህዝቡ እንዳይቀላቀል ከመከልከልና ከማስፈራራት ጀምሮ ውንጀላዎችን ቀጥሏል፡፡ ይህም የሚያሳየው ጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲ፣ ሲቪክ ማህበረሰብና ሚዲያ በሌለበት አገር ህዝብ በነጻነት ሮሮውን ሊያሰማበት የሚችለው ሰላማዊ ሰልፍ አብዮታዊ ፓርቲው በስልጣን የሚቆይባቸውን ጊዜያት ያሳጥራል ተብሎ በመፈራቱ ነው፡፡
ኢህአዴግ ለዚህ ጸረ ሰላማዊ ሰልፍ ፕሮጀክቱ ሌላ ስልትም አስፈልጎታል፡፡ የድጋፍ ሰልፍ! የድጋፍ ሰልፉም ሆነ የሰላማዊ ሰልፍን ክልከላው በዚህ ከቀጠለ ለስምንት አመት ከህዝብ እርቆ ከቆየው በተመሳሳይ አይነኬ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ በተቃራኒው ተቃዋሚዎችንና ሌሎች መብታቸውን ለማስከበር መለስተኛ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላትን የሚያወግዙ፣ ፓርቲና መንግስት፣ መሪን የሚያወድሱ የድጋፍ ሰልፎች ህዝብ የራሱን ሮሮ ሳይሆን የልሂቃንን  ጥቅም እንዲያስተጋባ ማድረጋቸው የግድ ነው፡፡ እናም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚጠሩትን ሰልፍ ከምቀላቀልበት የመጀመሪያው ምክንያት ሰላማዊ ሰልፍ እንደ መብት ይቀጥል ዘንድ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት ግዴታ ስላለብኝ ነው፡፡
ሰላማዊ ሰልፍ እንደ መብት መመለሱ ዋናው ነገር ቢሆንም የመጨረሻ ግብ ግን አይደለም፡፡ ስለሆነም ይህን መብት ተጠቅሜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ኢ-ፍትሃዊነቶች በግልጽ እቃወምበታለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው መፈናቀላቸውን፣ ግለሰቦች በፖለቲካ አመለካከቶቻቸው ከመስሪያ ቤት ያለ አግባብ መባረራቸውን፣ ሙስናን፣ አምባገነንነትን፣ አፋኝነትን እንደ አንድ ወጣት በግልጽ እቃወምበታለሁ፡፡ ውጤቱ አወንታዊም ይሁን አሉታዊ ያለፈው ትውልድ መብቱን ለማስመለስ ተራራ ገደሉን ወጥቷል፡፡ መክፈል ካለበትም በላይ መስዕዋትነት ከፍሏል፡፡ እናም እነዚህ ከጠላት አገራት ሳይቀር ትኩስ ትጥቅ እየተቋጠረላቸው የወቅቱን መንግስታት በነፍጥ ተዋግተው ያሸነፉት አካላት በራሴና በአገሪቱ ላይ የፈጠሩትን ችግር በሰላማዊ መንገድ መቃወም እጅግ ትንሽ ግዴታየ ቢሆን እንጅ ያን ያህል የምኩራራበት፣ የሚያስፈራም፣ የሚያስወግዝም አይደለም፡፡ የትውልድ አደራዬም ነው፡፡
መንግስት ሰላማዊ ሰልፍን ለመቀልበስ በጀመረው ዘመቻ ኢትዮጵያውያንን አስፈራርቶም ሆነ ደልሎ የድጋፍ ሰልፍ እያስወጣ ነው፡፡ ባለፈው ‹‹የድጋፍ ሰልፍ›› በሰልፉ የተገኙት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተቃዋሚዎች በሚጠሩት ሰልፍ እንደሚደረገው በራሳቸው ወጭ አሊያም በእግራቸው ተጉዘው ሳይሆን ‹‹በመንግስት›› ንብረት መስቀል አደባባይ ድረስ ደርሰዋል፡፡
በደህንነትም በኩል ቢሆን ምንም አይነት ችግር አልነበረባቸውም፡፡ በእምነት ተቋማት ስም በተጠራው ሰልፍ ሰልፈኞቹ አውግዙ የተባሉትን በማውገዛቸው የሚመጣባቸው ምንም አይነት ጫና አልነበረም፡፡ መከላከያውም ሆነ ፖሊሱ እነሱን ለመጉዳት ሳይሆን እነሱን በመጠበቅ ከጎናቸው ውሏል፡፡ አብዛኛዎቹ ተሰላፊዎች የውሎ አበል የሚከፈላቸው ካድሬዎች፣ አመራሮች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ቀሪው ህዝብ ደግሞ ኮንዶሚኒየም አታገኝም፣ ካልወጣህ ጽንፈኛን ደግፈሃልና …እና በመሳሰሉት ማስፈራሪያዎች ሰልፉን ተቀላቅሏል፡፡ በአጠቃላይ ሰልፉ ወጣት አዛውንቱ ከእውነትና ከእምነቱ ይልቅ ፈርቶ አሊያም ለሆዱ አድሮ የወጣበት ነው፡፡ እኔም በተቃዋሚዎች ሰልፍ ተቃውሜ ማሳየት የምፈልገው ይህንኑ ፍርሃት፣ ሆድ አደርነትና ውሸት ነው፡፡
ተቃዋሚዎች በሚጠሩት ሰልፍ መከላከያና ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለመጠበቅ ሳይሆን እነሱን ለመጉዳት ተዘጋጅቶ እንደሚመጣ አውቃለሁ፡፡ ተቃዋሚዎቹ የትራንስፖርት መኪና፣ የውሎ አበል፣ ሰርተፊኬትና ሌሎች ጥቅሞችን እንደማይሰጡ እገነዘባለሁ፡፡ በተቃራኒው ኢህአዴግ በሰልፉ የተገኙትን ከስራ እስከማባረር፣ እስከማሰርና ሌሎች ጉዳቶችን እስከማድረስ አሊያም ለማድረስ እንደሚያስፈራራም የተደበቀ አይደለም፡፡ ሆኖም ይህ የነጻነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት ከምንም በላይ ማንነትን የማስከበርና አሳልፎ የመስጠት ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ክብሮች እንዲሁ የሚገኙ አይደሉም፡፡ በእርግጥ ሰላማዊ ሰልፍ ብቻም የሚያስከብራቸው መብቶችም አይደሉም፡፡ ግን አንድ መድረክ ነውና እጠቀምበታለሁ፡፡
ስለሆነም ሰላማዊ ሰልፉ ለነጻነቴ፣ ለፍትህ፣ ለማንነት፣ ለአገር ጥቅም እንጅ ለሆዴ ለፍርሃትም ሆነ ተደልዬ እንደማልኖር በግልጽ ጮህ ብዬ የማሳይበት መድረክ ነው፡፡ የድሮው ትውልድ ለአገሩም ሆነ ለራሱ ሲል የፈጸመውን ተጋድሎ ከማድነቅ አሊያም ከመኮነን ባሻገር እኔ ራሴ በትውልድ ቅብብሎሹ የራሴን ሚና ተወጥቼ የማልፍ እንጅ የገዥዎችም ሆነ የሌሎች መገልገያ አለመሆኔንም ህገ መንግስታዊ በሆነው የሰላማዊ ሰልፉ ላይ በመገኘት አረጋግጣለሁ፡፡
ሰልፈኞቹ አስርም፣ መቶም፣ አንድ ሺህም ይሁኑ ዋናው መብቴን መጠቀምና ይህን መብት ተጠቅሜም የሚጠበቅብኝም ማድረግ ነው፡፡ በወጣትነቴ ቢያንስ ለራሴ መብት ካልቆምኩ ለማን ልሆን እችላለሁ? ማንም እንደፈለገ የሚነዳኝ፣ ሲፈልግ የሚከለክለኝ፣ የሚያስረኝ ከሆነ አሊያም እነዚህ በደሎች ሲፈጸሙብት ካልተቃወምኩ፣ በግልጽ ካልተናገርኩ ወጣትነቴ፣ ኢትዮጵያውነቴ፣ ትውልድ ተረካቢነቴ ብቻ ሳይሆን ሰውነቴስ የት ላይ ነው? ስለሆነም ከድሮው ትውልድ፣ ከአሁኑ መሪዎችም ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ ፍጡር መሆኔን ተቃውሞውን  ተቀላቅየ አሳያለሁ፡፡
ይህን ሳደርግ ሰማያዊ ወይንም አንድነት በግድ ቀስቅሶኝ፣ አስፈራርቶኝ አሊያም ደልሎኝ አይደለም፡፡ የማንም ፓርቲ አባል ባልሆንም የጋራ የሚያደርግ ጥያቄ ሰልፉን እቀላቀላለሁ፡፡ አንድነት ወይንም ሰማያዊ የጣላቴ ጠላትም ስለሆኑም አይደለም፡፡ ይህ የመርህ፣ የህገ መንግስታዊነት፣ የነጻነት፣ የብሄራዊ ጥቅም፣ የሰብአዊነት ጉዳይ ነው፡፡ አንድነትም ሆነ ሰማያዊ እኔን የሚያስገድዱበት ጡንቻም፣ ሆነ የሚደልሉበት ኢኮኖሚያዊ አቅም የሌላቸው መሆኑ ከሰልፉ አያስቀረኝም፡፡ እንዲያውም ወጣት ማለት ተደልሎ ሳይሆን በነጻነት፣ በፖሊስ እየተጠበቀ ሳይሆን ፖሊስ እያስፈራራው፣ በፕሮፖጋንዳ ሳይሆን ስለ እውነት፣ ለመሪና ለካድሬ ሳይሆን ለአገርና ለህዝብ የሚቆም መሆኑን የማሳይበት በመሆኑ ነው፡፡
ከስምንት አመት በላይ ከህዝብ ርቆ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በቤተ መንግስት ጥግ ድምጼን ከፍ አድርጌ ማሰማት ልዩ ስሜት ይሰጠኛል፡፡ ይሰማም አይሰማም ገዥዎች፣ ካድሬዎች ብቻ ሳይሆኑ ዜጋም በነጻነት ቤተ መንግስት አካባቢም ቢሆን ጥያቄውን እንደሚያሰማ ማሳየት ቀላል መብት አይደለም፡፡
ኑ እንደ ወጣት፣ እንደ ኢትዮጵያዊ፣ እንደ ትውልድ ተረካቢ ድምጻችንን እናሰማ፡፡ በእርግጥ ከተቃዋሚዎች ይልቅ ህዝብ በራሱ ነጻ ወኪል ሰልፍ ቢጠራ መልካም ነበር፡፡ በተስፈኝነት ያንን መድረክ ከመጠበቅ የተገኘውን መጠቀም ብልህነት ነው፡፡ ኢህአዴግ ያዘጋጀው ላይም ቢሆን ተቃውሞን ለማሰማት መገኘት ትልቅ ስልት ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፉን በሚጠሩት ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞች ልንከፋም ሆነ ልዩነት ሊኖረን ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ ልዩነት ድምጽ ከሚሰማበት ሰልፍ ጋር የሚያገናኘው ነገር አይኖርም፡፡
ደግሞም የነገዎቹን ገዥዎች ቀርበን ካላስተካከልናቸው ደደቢት ድረስ ርቀው ከነበሩት ባልተናነሰ ከህዝብ ጥቅም ያፈነገጡ መኖናቸው የማይቀር ነው፡፡ እንዲያውም  ህዝብ ቀስ እያለ ሰላማዊ ሰልፉን ከፓርቲዎች መንጠቅ እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ ለአሁኑ ግን በትብብር አብሮ ድምጽን ማሰማት አማራጭ ያለው አይመስለኝም፡፡

No comments:

Post a Comment