Monday, September 9, 2013

በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ብልጣብልጥነትን ታግሰን እስከመቼ???

አሁን ባለንበት ብልጣብልጥነት እውቀት ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ማንነት ላይ በተለይ ስስ ናቸው ተብለው የሚታወቁትን የብሔር የሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ብልጣብልጥነትን የሚያቀነቅኑ በርካታ ናቸው፡፡ እራሳቸውን እንደልሂቅ የሚቆጥሩ ሆን ብለው ህዝብን የሚያሳስቱ በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህን ልሂቃኖች በሁለቱም ውስጥ ማለትም ስልጣን ላይ ባለው አንባገነን ስርአት በኩል እና በተቃዋሚውም ጎራ መሰለፋቸው የኢትዮጵያን የወደፊት ሁኔታ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ በጣም የሚገርመው የየብሔሩ ልሂቃን ነን የሚሉ እነዚህ ግለሰቦች ተጨቁኗል እያሉ ሲያራግቡ ቆይተው ዛሬ ስልጣን ላይ ሲወጡ በመጀመሪያ ያደላደሉት እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ነው፡፡ እንጂ ተጨቁኗል ያሉትን ብሄር ዛሬም ስጋውን ከመጋጥና ከመዝረፍ አልተመለሱም፡፡ አንባገነንነት እንዲህ ነው፡፡ ሰፈርተኝነትም እንዲህ ነው፡፡
የሰፈርተኝነቱ ያይላል፡፡ እንወክላለን ከሚሉት ብሔር ይነሱና ማረፊያቸው እራሳቸውን ጋር ይሆናል፡፡ ይህ በዘመናችንም የምናየው እንዲሁም እያየን ያለነው ነው፡፡ ሟቹን / ጨምሮ የኢህአዴግ አመራሮች ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄር ጭቆና እንደነበር ደጋግመው ገልፀዋል፡፡ ገልፀዋል ብቻ ሳይሆን ለእኩይ አላማቸው ሲሉ እንደፈለጉ ተጠቅመውበታል፡፡ በየመድረኩ ሲወጡ ባለፉት ስርዐቶች ደርሶብናል የሚሉትን የብሔር ጭቆና በዚህ ስርዐት እንደተቀረፈ መብቶቻቸው እንደተከበሩላቸው ሲደሰኩሩ ቆይተዋል፡፡ አሁንም በመደስኮር ላይ ናቸው፡፡ መቼም የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በማክበር ከጭቆና ወጥተናል እንደማይሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በደርግ ጊዜም የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ተብሎ አያክብሩ እንጂ ቋንቋቸውን ሳይጠቀሙ ዝም ብለው የተጫነባቸውን ቋንቋ ነው ሲናገሩ የቆዩት እንደማይሉን እናውቃልን፡፡ እውቁ አቀንቃኝም ለዚህ ይመስላል ‹‹ የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ›› ሲል የገለፀው፡፡ ለሆዳቸው ያደሩና እንወክለዋለን የሚሉትን ብሄር እንኳ የመወከል አቅም የሌላቸው ግብዞች ናቸው እቺን አገር እያተራመሷት ያሉት፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ አንድ የገጠር ቀበሌን እንኳ በስርዐት ማስተዳደር የማይችሉ ግለሰቦች ከፍተኛ ስልጣን ላይ ተቆናጠው ያሉት በዚሁ በብልጥነታቸው ነው በሌላ አይደለም፡፡ ለዚህም የቀድሞው መሪ እንዳሉት የፖለቲካ ታማኝነቱ እንጂ በኢህአዴግ ቤት ውስጥ ሌላ መስፈርት እንደሌለ በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ እንዲህ የሚሆነው ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ይመስለኛል፡፡ እራሳቸው ጠግበው ካደሩ ሌላው ትዝ የማይላቸው እነዚህ ስግብግብ ግለሰቦች ዋናው አቅጣጫቸው እራሳቸውን ማበልፀግ እንጂ ተጨቁኗል የሚሉትን ብሔር እንዳልሆነ በዚህ 20 አመት ውስጥ አሳይተውናል፡፡ ፎቅ ሲገነቡ ልጆቻቸውን አውሮፓና አሜሪካ እየላኩ ሲያስተምሩ ተጨቁኗል የሚሉትን ክፍል ግን ዘወር ብለው እንኳ ማየት አልቻሉም፡፡ ዛሬም ህዝቡ በከፋ ችግር ላይ ይገኛል፡፡ ማን ያዳምጠው የሚናገሩት ሆድ አደሮቹ ናቸው፡፡ ህዝቡ ምን እያለ ነው? ካድሬው የሚለውን ሳይሆን ህዝቡ እራሱ የሚለውን ለሰማ ምን ያህል መቀለጃ እንዳደረጉን ያሳያል፡፡ ለብልጣብልጥነቱ ደግሞ ቋንቋን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም አንቀሳቃሽ ሞተር ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ ለስሙ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር የሚካሄደው እራስ ወዳድነት እና ጎጠኝነት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ እኔም ሆንኩ መሰሎቼ ይህንን የሚሸከም ትከሻ የለንም፡፡ ማንም በብልጣብልጥነት የሚቀጥልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ለእኩይ አላማቸው ታሪክ ላይ ባላቸው የተንሸዋረረ አተያይ የሚነሱት እነዚህ ሆድ አደር ግለሰቦች በዚህ ግዜ እንዲህ ሆኖ በዚህ ግዜ እንዲ ተደርገን እያሉ ልዩነትን በመስበክ የነሱን የምቾት ኑሮ የሌላውን የስቃይ ህይወት ያረዝማሉ፡፡ ይህ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ስለዚህ በግዜ መፍትሄ ልንሰጥበት የሚገባን ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የቀራቸው የኛ ስለሆኑ ብንበድል ማን ምን ያገባዋል ማለት ነው፡፡ ሰፈርተኞች እና አምባገነኖች እንዲህ ናቸውና አይግረመን፡፡ በተቃዋሚውም ውስጥ እንደዚህ አይነት ግለሰቦች አሉ፡፡ በሃገርም ከሃገር ውጪም ይገኛሉ፡፡ እኔ እንደማስበው ‹‹መገንጠል እንፈልጋለን፡፡ ይህን ብሄር ነፃ አወጣለሁ›› ብለው የሚታገሉትን ለመታገል የሚከብደን አይደለም፡፡ ምክንያቱም እቅጩን ተናግረው ስለጀመሩት፡፡ አሁን ያስቸገሩት እና እኩይ አላማ ያነገቡት ሳናውቅ በየአዳራሹ ያጨበጨብንላቸው አሁንም ሳናውቅ እያጨበጨብን የምንገኝላቸውን ግለሰቦች ነው መታገል ያለብን፡፡ትንሽ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በቅርቡ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ የሆነና እውነተኛ ማንነቱን ያላወቅነው ነበረ ግለሰብ ‹‹ በቅድሚያ እኔ ኦሮሞ ነኝ ኢትዮጵያዊነት በጉልበት የተጫነብኝ ነው፡፡›› ሲል ገልፆ ብዙም ሳይቆይ ‹‹ ሙስሊም ኦሮሞ ፈርስት›› ማለቱ የቅርብ ግዜ ትውስታችን ነው፡፡ አገር ውስጥ የሚገኙ አንድ ግለሰብ በመፅሄት ይሁን በጋዜጣ ላይ ስለመገንጠል እንዲህ ብለው ነበር‹‹ እኔ በርካታ ቦታዎች ላይ ተዘዋውሬ ህዝቡን ጠይቄያለሁ፡፡ ሁሉም መገንጠልን አይፈልግም ›› ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ ይቺ እውነት ሆኖ ሳለ ልሂቃን ነን የሚሉት ሰዎች ከየት አምጥተው ነው ስለመገንጠል የሚደሰኩሩት፡፡ እንዲህ ያሉትን ግለሰብ ታድያ ስለምን ባንድነት ትግሉን አትመሩም ቢባሉ መልስ አይኖራቸውም፡፡ ምክንያቱ ለእንደዚህ አይነቱ ግለሰብ በተለይ ብሄሩን መጠቀሚያ ላደረገ ግለሰብ አንድነት የሚዋጥ አይሆንም፡፡ በእውነተኛ ማንነት ውስጥ ብልጣብልጥነት ቦታ የላትም፡፡ እኚሁ ግለሰብ መድረክ በተባለ የፖቲካ ስብስብ ውስጥ ሆነው ‹‹ፌደራሊዝሙን የሚጠሉት የአዲስ አበባ ልሂቃኖች (አንድነቶች) ናቸው ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ ፌደራሊዚሙን የሚወዱት እነማን እንደሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ብልጣብልጥ ልሂቃን ተብዬዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ አካሄዳችንን መመርመር አለብን፡፡ በፍፁም ከዚህ ወዲህ እዚህን አይነት ግለሰቦች በየአዳራሹ የምናጅብበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ይህን ስል ግልፅ ማድረግ የምፈልገው ነገር በፓርቲ ደረጃ ህብረ ብሔራዊ ከሆኑ ፓርቲዎች ውጪ ሌሎች አይኑሩ ማለቴ አይደለም፡፡ ይህ ፌደራሊዝም እስካለ መኖራቸው አይቀሬ ቢሆንም እኔ ግን እያልኩ ያለሁት ብልጣብልጥነቱ ይቁም ነው፡፡ በግሌ እነሱን አለመደገፍ መብቴ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ተጨቁነናል ስለሚሉት ነገር እኔ እከገባኝ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ አንባገነን እና ጨቋኝ አገዛዞች አልነበሩም አላልኩም እያልኩ ያለሁት አገዛዙንና ህዝቡን ለዩ ነው፡፡ ባደባባይ በድፍረት ያለፈው የብሄር ጭቆና ደርሶብናል የሚሉት ግለሰቦች እራሱ በዚህ ዘመን ጭቆና እንዳለ ሲተነፍሱ አይሰማም ለምን? ብልጣብልጥነት ስለተመቻቸው ነው፡፡ አሁን እስካለው ኢህአዴግ ድረስ ጭቆና አለ፡፡ ያለው ግን የብሄር ጭቆና ሰይሆን ማንንም ሳይመርጥ የሚያጠቃው የአገዛዙ ጭቆና ነው፡፡ ብልጣብልጦቹ እንደሚነዙት ሳይሆን ባንድነት መሆን ማለት ሰው በቋንቋው አይጠቀምም፤ ባህሉን አያሳድግም ማለት አይደለም፡፡ ይህ የብልጣብልጦቹ ቅዠት ነው፡፡ በአንድነት መኖር/አንድነትን መምረጥ ማለት ለጋራ አላማና ስኬት ያለንን የሰው ሃይል በአንድነት በማስተባበር ከአለም ተፅኖ ፈጣሪ አገር መሆን እንችላለን፡፡ በመከፋፈልና በመለያየት ግን የትም አንደርስም፡፡ ለብልጣብልጦቹ ይበልጥ የተመቸን ሆነን የኛን ምጥ እናረዝማለን፡፡
ግሬስ አባተ


No comments:

Post a Comment