የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
ኢሕአፓ አንድና አንድ ብቻ ነው
የኢሕአፓ ሕገ ፓርቲና መተዳደሪያ ደንብ በውልደቱ ከድርጅቱ ልደት ጋር ነበር አብሮ የተፈጠረው። አባላት በእነዚህ ሰነዶች የውዴታ ግዴታ ራሳቸውን ሲያስገዙ ኖረዋል። አባል ለመሆንም ይሁን ከአባልነት ለመወገድ ሰነዶቹ ለድርጅቱ አንድም እንደ መመዘኛ ሁለትም እንደ መዳኛ ህግጋት ሲያገለግሉ ኖረዋል። ስለሆነም አባላት በሰነዶቹ ላይ ብዥታ ኖሯቸው አያውቅም። ብዥታው ከድሮም ከአመራሩ እንጂ ከአባላት አልነበረም። ዳሩ የሰሞኑ አደናጋሪ መግለጫ ግን “መበደል መበደል ወታደር በድሏል ግን ባላገር ይካስ” እንዲሉ ይመስላል። አባላትን ህግ የተላለፉ ለማስመሰል ተሞክሯል። ሰነዶቹ ውይይትን፤ ሂስና ግለሂስን፤ ብሎም መተራረምን የሚያበረታቱ ሲሆኑ ቅጣትን እንደ መጨረሻ አማራጭ አድርገው ይወስዳሉ።
ይህንን በሚመለከት በፍኖተ ሕብረት የኢሕአፓ ሬዲዮ ነሐሴ vw አሁድ በተሰጠው ቃለ መጠይቅ ሁለት የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ጓዶች አትኩሮት ሰጥተው አስረድተዋል። ሕግና ደንብን በሚመለከት ሁለቱ አመራሮች በሰጡት ቃለ መጠይቅ ውስጥ ገብተን ለመተቸት አንሞክርም። ዳሩ በአሁኑ ወቅት የተፈጠሩት ችግሮች ግን ከሰነዶቹ አፈጻፀም ጋር በእጅጉ የተቆራኙ መሆናቸውን አስረግጠን ማለፍ እንወዳለን።
የኢሕአፓን ሕገ ፓርቲ አና ውስጠ ደንብ መጣስ የተጀመረው ዛሬ በየቦታው እንደሚናፈሰው በእርማት እንቅስቀሴው አባላት ሳይሆን የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላት በነበሩት በአቶ ኢያሱና በአቶ ፋሲካ ነበር። ጠቅለል ባለ መልኩ ይህን ይመስላል፦
፩ኛ. የድርጅቱን መዋቅር በመከተል ድርጅቱን በሚመለከት ገንቢ የሆነ ሕጋዊ ጥያቄ ያቀረቡትን ቻፕተሮች ማፈን። በደርጅቱ ጉባኤ አካሄድ ላይ ያልተስማሙትን አንጋፋ አባላት፣ ለጥያቄያቸው መልስ ከመንፈግ አልፎ ከድርጅቱ ማግለል። መብታቸውን ነፍጎ ግን ግዴታቸውን እንዲወጡ ማስገደድ፣
፪ኛ. የድርጅቱ አባለት በማያውቁት ሁኔታ የድርጅቱ አቋም በማስመሰል መግለጫዎችን በመስጠት ህግ መጣስ፣
፫ኛ. እጅግ ጸያፍ የሆኑ ስነ ምግባሮችን ጨምሮ የዲሲፕሊን ጉድለቶችን በጽሕፈት ቤቱ ውስጥ መፈጸም፣
፬ኛ. አባለትን ወያኔያዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል። በድርጅቱ ውስጥ የበኩርና የእንጀራ ልጅ መፍጠር። በጎጥና በዘር መከፋፋል፣ ከሌሎች የሕግና የደንብ ጥሰቶች በተጨማሪ ይህም ሙሉ በሙሉ ጸረ ኢሕአፓ አካሄድ ስለሆነ ግለሰቦቹ ኢሕአፓን አንደማይወክሉ ለማስታወቅ ተገደናል::
፭ኛ. የድርጅቱን ደንብ በሚጻረር መልኩ ድርጀቱን የሚጎዳ ጽሁፍ፣ ቃለ መጠይቅ፣ ወዘተ. በተደጋጋሚ ማድረግ፣
፮ኛ . ሂስና ግለሂስን ወደ ጎን ገፍቶ አሉባልታን በድርጅቱ ውስጥ ማስፋፋት፣
፯ኛ . የድርጅቱን ምስጢር አደባባይ ማውጣት፣
፰ኛ. የወጣቱን ክንፍ ለመበተን ተከታታይነት ያላቸው የከፉ አርምጃዎችን መውሰድ፣
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የደንብ ጥሰቶች ከበቂ መረጃ ጋር ግልጽ ቢደረጉም እስካሁን እልባት አላገኙም።
ዛሬ እነዚህ ሁለት አመራር የነበሩ ግለሰቦች የአንጋፋ አባላትን “ወንጀል”©ወራሃዊ መዋጮ አለመክፈል እንዲመስል ጥረዋል። ይህ “መብታችሁን አትጠይቁን ገንዘቡን ግን አታቋርጡ” የሚለው የዕበላ ባይነት ፍርደ ገምድል ዳኝነት የድርጅቱን ህገ ደንብ ይጻረራል። በመሆኑም የተፈጠረው አለመግባባት የወያኔን እድሜ ለማራዘም አጋዥ ሆኗል። የድርጅቱን ዴሞክራሲያዊ አሰራር ጥሷል። ስለሆነም ለእርምት የተነሳውን ጥያቄ ከማድበስበስና ከሃላፊነት ለመራቅ ከመሞከር ተቆጥቦ ችግሩን በውይይት ለመፍታት ጥረት ቢደረግ አሁንም ጊዜው አልመሸም። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን አጀንዳውን አድበስብሶና አቅጣጫ አስቀይሮ በሀሰትና በአሉባልታ ዘመቻ መቀጠል በታሪክና በሕዝብ ተጠያቂ ያደርጋል::
የእርማት እንቅስቃሴው አንኳር ነጥቦች፦
፩ኛ. የድርጅቱ መርህ የሆነው የጋራ አመራር ተጥሶና ኮሚቴዎች ፈርሰው ወደ ግለሰባዊ አሰራር በመኬዱ የድርጅቱ ምስሶ የሆነው ዴሞክራሲያዊ አሰራር ተጥሷል።
፪ኛ. የድርጅቱ ንብረት ያለምንም ተጠያቂነት በሁለቱ ግለሰቦች እጅ በመውደቁ የንብረት መባከን አና የአጠቃቀም ጉድለት ደርሷልና በኦዲት ተመርምሮ ቼክና ባላንስ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል።
፫ኛ. ግልጽነት በሌለበት ሁኔታ የድርጀቱ አባላት ስለድርጅቱም ሆነ አሁን ሰለሚካሄደው የእርምት እንቅስቃሴ እንዳያውቁና እንዳየይወያዩ ታፍነዋል።
እነዚህ ከፍ ብለው የተጠቀሱት አብይ የድርጅቱ መርሆዎች በተጨባጭ ተመርምረው በጉባኤ እርምት ሊደረግባቸው ሲገባ በሕግና በደንብ ትንተና ሽፋን በማውገርገር የሕዝብን አስተያየት ለመቀየር የተደረገው ሙከራ ፍሬ ቢስ ነው። በተለይ የአሁኑን የእርምት እንቅስቃሴ ወያኔ ኢሕፓን ለማጥፋት ከሚያደረገው ጥረት ጋር ለማያያዝ የሚደረገውም ሙከራ የሚያስቅና ራስን የሚያስገምት ይመስለናል።
በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በግለሰባዊ ተፈጥሮዋዊ በሆነ ግንፍልተኝነት ለመፍታት መሞከር የእራስን ማንነትና የአመራር ብቃትን መጏደል ከማሳየት አያልፍም። የአርባ አመት የአመራር ተመክሮ ይህንን ካላስተማረ፣ ጠባይ ወደ ተፈጥሮነት ተቀይሯልና ለሌሎች ረጋ ብለው ችግሮችን የመፍታት ባህል ላላቸው አመራሮች ቦታውን መልቀቅ፣ ለድርጅቱም ለሃገርም አሳቢነትን አጉልቶ ስለሚያሳይ፣ ይህንን አማራጭ መጠቀም ብልህነት ነው ብለን እናሳስባለን። በዚህ አጋጣሚ በተደጋጋሚ የቅራኔዎች አፈታት ችግርና የብዙ ሰዎች ምስክርነት ምክንያት “የፖለቲካ ሕይወቴ ሞቷል” በማለት አጥፊ ተግባራትን መፈጸም በታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል።
ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ የበሰለ አመራር የሚፈልገበት ወቅት ነው። በድርጅት ውስጥ የሚነሳን አነስተኛ ቅራኔ መፍታት ተቸግረው፣ ወደ አምባገነንነት ለመጓዝ ጥረት ያደረጉ ሁሉ ድርጅታቸውን ሰው አልባ፣ ተሰሚነታቸውን ባዶ አድርገው መቀመጣቸውን ለማስረዳት ብዙ ምሳሌዎች መስጠት ይቻለል። ከዛም መማር አስፈላጊ ነው። አሁን የአባላት ቁጥር በሚያሽቆለቁልበት ወቅት ለዚህ መፍትሄ አለመሻትና የትግሉ ተረካቢ የሆኑትን ወጣቶችን ለመበተን መሞከር፣ ድርጅቱ ቀጣይ እንዳይሆን መጣር መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
የእርማት እንቅስቃሴው ድርጅቱን በተለያየ ምክንያት የተለዩትን አባላት ለማሰባሰብ መጣር እንዳለበት እሙን ነው። ይህ ደግሞ ኢሕአፓን መልሶ አንድ ማድረግንም ማካተት አለበት። ማንም ግለሰብ፣ ማንም አመረር፣ በኢሕአፓ አንድነት ላይ የመጨረሻ ቃል (ቬቶ) ሊኖረው አይገባም። የድርጅቱ አንድነት ከግለሰቦች የግል ሃውልት ጠረባ ወይም የግል ጥቅም በላይ ነው። ስለሆነም የእርማት እንቅስቃሴው ለዚህ ክቡር ዓላማ መሳካት ቀድመው ከፓርቲው ለተለዩ አባላት በሙሉ ጥሪ ያቀርባል። ስፊ ውይይት ተደርጎ፣ ስህተታችንንም ተማምነን፣ ድርጅታችንን አጠናክረን ለሃገራችን ታላቅ አስተዋጽዖ እንድናደርግ ያሳስባል። ይህ ተግባር የኢሕአፓነታችን ገናናነት፣ የወደቁ ጓዶቻችን ወቅታዊ የአደራ ጥሪ ስለሆነ በየአካባቢው፣ በየቻፕተሩ፣ በተቻለው ሁሉ ውይይቱ መካሄድ አለበት።
ዛሬ ሃገራቸን ከገባችበት የወያኔ የግፍ አገዛዝ ለመውጣት ክፍፍሉ ቆሞ መፍትሄ መፈለጉ ሌላ አማራጭ የሌለው ብቸኛ ጎዳና ነው። ይህ በኢሕአፓ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ድርጅቶች መካሄድ እንዳለበትም እናምናለን። የአንድነት ሃይሎች፣ የክፍፍል አባዜውን አቁመን፣ የእርምት እንቅስቃሴ እያደረግን በበሰለና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ከተጓዝን የምንመኘው የድርጅቶች ሕብረትም ይሳካል። ብሎም የወያኔ ቀን ያጥራል።
የኢሕአፓ ጉባዔ እንጂ ካሁን በኋላ ማንም ግለሰብ በኢሕአፓ አንድነት ላይ የመጨረሻ ቃል(ቬቶ) አይኖረውም !
ኢሕአፓን አንድ ማድረግ የእርምት እንቅስቃሴው የመጨረሻው ራዕይ ነው!
እናቸንፋለን!!
No comments:
Post a Comment