በዘሪሁን ሙሉጌታ
በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙት ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙና እስክንድር ነጋ በዓለም አቀፉ የሳካሮቭ ሽልማት ከሰባት የመጨረሻ ዕጩዎች ውስጥ ተካተቱ።
በአውሮፓ ፓርላማ የውጪ ጉዳይ፣ የልማት ኮሚቴ እና የሰብአዊ መብት ኮሚቴ የሳካሮቭ 2013 ሰባት ተሸላሚ ዕጩዎችን ይፋ አድርጓል። በዚህም መሠረት የ11 ዓመቷ ፓኪስታናዊት ህፃን ማላላ የሱፍ፣ አሜሪካዊው የኮምፒውተር ኤክስፐርት ኤድዋርድ ሶኖውዳን፣ ከኢትዮጵያ ርዮት አለሙና እስክንድር ነጋ፣ ከቤላሩስ አለስ ቢለትስኪ፣ ኤድዋርድ ሎቡ እና ማይኮላ ስታቲቪክ የተባሉ የፖለቲካ እስረኞች፣ እንዲሁም ሩሲያዊው ባለፀጋ ሚካኤል ኮዶሮኮቭስኪ እና የሲ ኤን ኤን ፍሪደም ፕሮጀክት ናቸው።
የአውሮፓ ፓርላማ አባላት በየዓመቱ በሚያዘጋጀው በዚህ ዓለም አቀፍ ሽልማት ላይ እነ ርዕዮት ዓለሙ የተጠቆሙት በምርጫ 97 የኢትዮጵያን ምርጫ ለመታዘብ የመጣውን ልዑክ በመሩት ሚስ አና ጎሜዝና ሌሎች 40 በሚሆኑ የአውሮፓ የፓርላማ አባላት በሰጡት ድምፅ ነው።
በዚህ የሽልማት ዘርፍ ርዕዮትና እስክንድር አሸናፊ የሚሆኑ ከሆነ ሽልማቱን በጣምራ እንደሚቀበሉ የሽልማት ተቋሙ ከለቀቀው የፕሬስ መግለጫ መረዳት ተችሏል።
የሳካሮቭ ሽልማት አንድሬ ሳካሮቭ በተባለ በሶቪየት እውቅ ሳይንቲስት ስም የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ሽልማት ሲሆን ተቋሙ ለኀሳብ ነፃነትና ለሰብአዊ መብት መከበር ለታገሉ ግለሰቦችና ተቋማት የሚሰጥ የሽልማት አይነት ነው። ተቋሙ እ.ኤ.አ በ1988 ዓ.ም ጀምሮ የተቋቋመ ነው። እስካሁን ይህ ዓለም አቀፍ ተቋም ኔልሰን ማንዴላ፣ የበርማዋን እውቅ ሴት ፖለቲከኛ አንግሳሱኪን ጨምሮ 30 ታዋቂ ግለሰቦችንና ተቋማትን ሸልሟል። ሽልማቱ ከሚያስገኘው ዓለም አቀፍ እውቅና ባሻገር የ50 ሺህ ዶላር ሽልማት አለው። የሽልማት አሰጣጥ ስነ-ስርዓቱ በመጪው ታህሳስ ወር የሚካሄድ ይሆናል። ከዚህ ቀደም ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በዚህ የሽልማት ዘርፍ መታጨታቸው አይዘነጋም።
No comments:
Post a Comment