አሁን አብዛኛው አውስትራልያ የገባ ኢትዮጵያዊ በሚገኝባት የሜልበርን ከተማ ውስጥአበሻው ሰብሰብ ብሎ በሚኖርባትና በሚሠራባት ፉትስክሬይ በተባለችው መንደር እንገኛለን፡፡ ይህች የሜልበርን ምዕራባዊ ቀበሌየሆነች መንደር ጥንት የኤስያውያን መናኸርያ ነበረች ይባላል፡፡ ዛሬ ግን ዋናዋ የአፍሪካውያን ስደተኞች መሰባሰቢያ ናት፡፡በዚህች ከ74000 ትንሽ ከፍ የሚል ሕዝብ በሚኖርባት መንደር ውስጥ ከ135 ሀገሮች የመጡ ስደተኞች ይኖሩባታል፤ ከ85 ቋንቋበላይ ይነገርባታል፡፡ እንዴው መርካቶ በሏት፡፡

በአውስትራልያ ታሪክ የመጀመሪያው የእንጀራ መሸጫ ሱቅ የተከፈተው እዚህ ነው፡፡
በነገራችን ላይ እዚህ ሀገር እንጀራ በዋናነት ከስንዴ ወይም ከሩዝ ዱቄት ተቦክቶ የማሽላ ዱቄት ይቀላቀልበታል፡፡ የታደሉትደግሞ ከሀገር ቤት የመጣ የጤፍ ዱቄት ለአመል ይጨምሩበታል፡፡ ስፋቱ የአገር ቤት እንጎቻ የሚያህል ሲሆን ውፍረቱ የሰንበት ቂጣታናሽ ወንድም ነው፡፡ ኮከብ የመሰለ ዓይን ባያገኝም፣ ሞጭሟጫ ከመባል ለጥቂት ይተርፋል፡፡ በብዛት የሚጋገረው ከብረት በተሠራምጣድ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ከሀገር ቤት የሸክላ ምጣድ የሚያመጡ አሉ፡፡ ሳይሰበር ከደረሰላቸው፡፡
በፉት ስክሬይ ከደርዘን በላይ የኢትዮጵያውያን ሱቆች፣ ከአምስት በላይ ምግብ ቤቶችእንዳሉ ይነገራል፡፡ በአካባቢው ስትዘዋወሩ ቢያነጥሳችሁ ‹ይማርህ› የሚል አታጡም ይባላል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች ስለሚዘዋወሩበት፡፡ በርግጥ ወጣቶቹና ጎልማሶቹ እንዲህ ያለ ነገር አያውቁም፡፡የሚገርማችሁ እንዲያውም እዚህ አካባቢ አበሻና አበሻ ሲገናኝ ቁጣ እንጂ ሰላምታ አይሰጣጥም፡፡ ሁለቱም ፊታቸውን ኮስተርአድርገው ነው የሚተላለፉት፡፡ እኔ እንዲያውም ‹እዚህ ሀገር የመጣው ያኮረፈው ተመርጦ ነው እንዴ› ብዬ ነበር፡፡
በፉት ስክሬይ የሚጠፋ ቅመማ ቅመም የለም፡፡ በተለይም ሕንድ ሱቅ ውስጥ በሀገራችንየጠፋው ቅመም ሁሉ ይገኛል፡፡ ሞያ በሜልበርን በሽ በሽ ነው፡፡ በርበሬ ከሀገር ቤት ለማስመጣት የአውስትራልያ የምግብ ሕግሲያስቸግር እዚሁ ሌላ በርበሬ ተፈጥሯል፡፡ ከሕንዶች ሱቅ የሚገዛ የሚያቃጥል ቀይ ቃሪያ አለ፡፡ እርሱን በኮረሪማ መፍጫ መፍጨትነው፡፡ ከዚያ ደግሞ ቅመማ ቅመሙን ለብቻ ፈጭቶ መጨመር፡፡ በመጨረሻም አውስትራልያ ሠራሽ ምርጥ ድልህ ይሆንላችኋል፡፡
አንድ ወዳጃችን ‹ሽሮ እኛን ስላሳደገች በክብር ጡረታ ወጥታ ትቀመጥ› ቢልም ከሀገር ሲወጡ አንዱ የሚናፍቀው ግን ሽሮነው፡፡ በአውስትራልያ ልዩ የሆነ የሽሮ አዘገጃጀት ተፈጥሯል፡፡ የባቄላው ዱቄት ከሕንድ ሱቅ ይገዛል፡፡ ከዚያም አመስ አመስ ይደረጋል፡፡ለቅመማው አስፈላጊ የሆነውን ቅመምም ሕንዶቹ ያመጡታል፡፡ እርሱንም በቡና መፍጫ ፈጭቶ በመጠኑ ማመስ ነው፡፡ ከዚያም ሁለቱን በባለሞያእጅ ደባልቆ ምርጥ የውጭ ሀገር ሽሮ ማግኘት፡፡ ችግር ብልሃትን ይፈጥር የለ፡፡
ለኢትዮጵያውያንእዚህ አንዱ ፈተና ከሀገር ቤት ባህላዊ ምግቦችን ማስመጣት ነው፡፡ የሀገሩ ሕግ ጥብቅ ስለሆነ፡፡ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉግን እንደ ካልዲ(የቡናን ፍሬ ያገኘው እረኛ) አዳዲስ ቅጠላ ቅጠሎችን የሚያገኙ ኢትዮጵያውያን እዚህ ሞልተዋል፡፡ አንድ ቀንነው አሉ፡፡ መቼም እኛ ታሪክን በጊዜና በሰዓት የመመዝገብ ችግር አለብን፡፡ (ተረቱም ታሪኩም ከዕለታት በአንድ ቀን ብሎ ነውየሚጀምረው) አንዲት የሀገሬ ሰው በግቢዋ ውስጥ ስትዘዋወር አንድ የምታውቀውን ቅጠል የሚመስል ነገር ታያለች፡፡ ጠጋ ብላቆረጠችውና መዳፏ ላይ አሸችው፡፡ ልክ ነው፤ እርሱ ነው፡፡ ወስዳ ለጓደኛዋ አሳየቻት፡፡ ሁለቱም ርግጠኞች ሆኑ፡፡ ጉዳዩን ወደልጅቱ እናት ‹ሪፈር› አደረጉት፡፡ እርሳቸውም እየተገረሙ ‹እርሱ ነው› አሉ፡፡ ለካስ ጌሾ ኖሯል፡፡ ጠላ ለመጥመቅ ችግርየነበረው ጌሾ በአውስትራልያ ምድር በቅሎ ተገኘ፡፡ ዛሬ በብዙ ኢትዮጵያውያን ግቢ ውስጥ ጌሾ በቅሎ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡
በዚህች ምድር በቅሎ የተገኘው ግን ጌሾ ብቻ አይደለም፡፡ መቼም አገር ደግ ነገር ብቻአታበቅል፡፡ አንድ ወዳጃችን ሁል ጊዜ አንድ ቦታ እየሄደ ቅጠል ሸምጥጦ ሲወጣ ይታያል አሉ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ማንም ከቁምነገር አልወሰደውም ነበር፡፡ በኋላ ግን ሸምጣጩ በዛ፡፡ የአካባቢው ሰዎችም ግራ ገባቸው፡፡ በከተማዋ ውስጥም ወሬው ተባዛ፡፡የሚሸመጠጥበት ቦታም በአንዳንድ ሰዎች መዘውተር ጀመረ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከሥሩ እየነቀሉ ወስደው በጓሯቸው ተከሉት፡፡ ከጥቂት ጊዜበኋላ የአውስትራልያ ፖሊሶች ጉዳዩን ሰሙትና ክትትል አደረጉ፡፡ ለካስ ያ በወፍ ዘራሽ በቅሎ አገር እየተራኮተ የሚሸመጥጠው ጫትኖሯል፡፡ ፖሊሶቹ እዚያ ቦታ የነበረውን መድምደው አጠፉት፡፡ ችግሩ ግን እነርሱ ሳይደርሱ በፊት በየግቢው ተዛምቷል፡፡ አንዳንድቤት ስትሄዱ ጫት በኩራት በቅሎ ታዩታላችሁ፡፡
ፉት ስክሬይ በአበሾች ዘንድ ከምትታወቅበት ሀብቷ አንዱ ምርጥ የሆነ ቁርጥ ሥጋ መሸጫስለሆነች ነው፡፡ መቼም ቁርጥ እየበላን ቁርጥ ነገር አለመቻላችን የሚገርም ቢሆንም የሀገሬ ሰው የትም ቦታ ቢሄድ፣ ምንምዓይነት ትምህርት ቢማር ሊያጣው የማይፈልገው ነገር ቢኖር ቁርጥ ሥጋ ነው፡፡ ከነአባባሉም ‹የተማረ ሰውና የተሳለ ቢላዋ ሥጋአያጣም› አይደል የሚባለው፡፡ እዚህ ከተማ በጥሬ ሥጋ ሻጭነታቸው የታወቁ ቤቶች አሉ፡፡ ነጭ፣ ቀይ፣ ጎድን፣ ዳቢት፣ ሻኛ፣ለቁርጥ፣ ለወጥ እያሉ የሚያስተናግዱ፡፡ እነርሱ ጋ ገብቶ አለበለዚያም ደግሞ ሰፈር ይዞ መጥቶ ቁርጥ በኅብረት መብላት እዚህየተለመደ ነው፡፡ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ወደ አውስትራልያ ዘመድ ለመጠየቅም ሆነ ለመዝናናት የሚመጡ ኢትዮጵያውያን በአውስትራልያቁርጥ ፍቅር ተነድፈው ነው የሚመለሱት፡፡ አንዳንድ የአውሮፓና የአሜሪካ ወዳጆቼ ጋር ስንጻጻፍ እንዲያውም ‹የአውስትራልያን ቁርጥ ሳትበላ እንዳትመጣ› ይሉኛል፡፡ እስቲ ቀምሼ እመሰክርለታለሁ፡፡
‹አይ እኔ ማን እንደነካው የማይታወቅ ሥጋ አልበላም› ለሚሉ አለያም ደግሞ ‹የተሸረፈ ጥርስ፣ ደልደል ያለም ላትአይቶ መርጦ ተከራክሮ መግዛት› ለሚያምራቸው ወደ ገጠሩ ክፍል ወጣ ማለት ነው፡፡ ከበግ አርቢ ገበሬዎች ጋር ምን የመሰለ የደብረብርሃን በግ ይገኛል፡፡ ማረዱን ባይፈቅዱላችሁም መባረኩን ይፈቅዱላችኋል፡፡ እነርሱ ደግሞ ገፍፈውና ቆራርጠው ይሰጧችኋል፡፡ ከዚያበኋላማ ‹አቤት ባለፈው ለፋሲካ የገዛሁት ምን የመሰለ በግ› እያላችሁ ሾላ ገበያ የሄዳችሁ ማስመሰል ነው፡፡
ሜልበርን አውስትራልያ፡፡
No comments:
Post a Comment