በመጀመሪያም ከዚህ ቀደም ባብዛኛው ስንጠቀምበት የነበረውን ተቃዋሚ የሚል መጠሪ ተቀናቃኝ በሚለው ለመጠቀም የፈለኩት በገዢው ፓርቲ ፕሮፓጋንዳ ብዛት ተቃዋሚ የሚለው ተለጥጦ ሁሉን ነገር የሚቃወም ተደርጎ እየተወሰደ ስለመሰለኝ ይህም በራሱ አንድ ብዥታ መፍጠር ስለሆነ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች የሚለውን ብንጠቀም የተሸለ ይሆናል፡፡ ባለፈው አመት ፕሮፌስር መሳይ ከበደ ስለ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ሲናገሩ ‹‹ትልቁ ችግራቸው ፍርሃት ነው›› ሲሉ መናገራቸውን አስታውሳለሁ፡፡ እንዴ ምን ማለት ነው የሚል ጥያቄ አቃጭሎብኝ ነበር፡፡ ፕሮፈሰሩ ግን ትክክል መሆናቸው የገባኝ ዘግይቶ ነው፡፡ ብዙ ግዜ መፍረድ አልወድም፡፡ ብችል የመፍትሄው አካል መሆን ስለምመርጥ ያ ካልሆነ ዝምታ ጥሩ ነው ብዬ ስለማስብ ሊሆን ይችላል፡፡
እንደሚታወቀው ከምርጫ 97 ወዲህ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት የሚያስቀስፍ እስከሚመስል ድረስ ስለዛ የሚያወራ አልነበረም፡፡ ያ ማለት ግን ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ሰልፍ ለመውጣት ጥያቄ አላቀረቡም ማለት አይደለም፡፡ አንድነት ብርቲካን መታሰሯን አስመልክቶ አባላቱና አመራሮች ብቻም ቢሆኑ ሰልፍ ወጥቷል፡፡ በርካታ ቁጥር ያለው ሰልፍ ግን አልታየም ነበር፡፡ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች በአዳራሽ እና በፅህፈት ቤታቸው ተወስነው ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ አሁን ግን ያ እየተለወጠ መጥቷል፡፡ ሰላማዊ ትግል ሲባል ምርጫ ሲመጣ ብቻ መወዳደር የሚመስላቸው ፓርቲዎች ያሉ ይመስለኛል፡፡ አሁን በተለይም ሰማያዊ ፓርቲና አንድነት ፓርቲ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለነሱም መነቃቃትን መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 2005 ዓ.ም ከፅህፈት ቤቱ እስከ ድላችን ሃውልት ድረሰ ያደረገው የተቃውሞ ሰልፍ መልካም ጅማሮ ነው፡፡ ከዚህ ሰልፍ ወዲህ ፕሮፌሰር በየነ ያሉትን አስታውሳለሁ‹‹ ለኛ አዳራሽ ተከልክሎ ለነሱ ሰልፍ ሲፈቀድ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል›› አይነት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሆይ ምንም እንቆቅልሽ የለውም፡፡ የራስን እውነተኛ ችግር ያለመመልከት ነገር ነው ሚመስለኝ፡፡ እሱም ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ትግሉን ሙሉ ለሙሉ መሬት አላወረዱትም ነበር ማለት ነው፡፡ የመርህ ፖለቲካ ነበር የሚመስለው፡፡ ሁሌም እራስን መፈተሽን የመሰለ ነገር የለም፡፡ የሰከነ ፖለቲካ እናራምድ ካልን እውቅና መሰጣጠቷንም መለማመድ አለብን፡፡አዳራሽ ከፍለው ሲከለከሉ የከፈሉትን ተቀብለው መመለስ ሳይሆን ለምን ብሎ መጋፈጥ ነው፡፡ እንጂ ነፃነት እንዲሁ በልመና አይገኝምና፡፡የሆነው ሆኖ ጅማሯችን መልካም ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት በሚል እያካሄደ ያለው ዘመቻም ይቀጥሉበት የሚያስብል ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ በርካታ ሰልፎችን ማድረጉ ለመነቃቃቱ አስተዋፆው ቀላል አይደለም፡፡ ዜጎች ከፍርሃት አረንቋ እንዲወጡም ይህ አይነቱ ሰልፍ የሚደገፍ ነው፡፡ ስለ ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቅ የሚለው ስርዐቱ አዙሮ ማስፈቀድ ነው በሚል ብዥታን መፍጠሩ አይዘነጋም፡፡ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ይህንን በመጋፈጥ ስርዐቱን ወደ ድርድር ማምጣታቸው ትልቅ ድል ነው፡፡ በቅርቡ ሰማያዊ ፓርቲ ሊያካሂድ ያቀደውን ሰልፍ የስርዐቱ ወታደሮች በሃይል ፅህፈት ቤታቸውን ተቆጣጥረው የውንብድና ተግባር መፈፀማቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ለኔ መልካም ጅማሮ የምለው ሰማያዊ ፓርቲ እስከዛች ሰአት ድረስ በአቋም ፀንተው መቆየታቸውን ነው፡፡ ከዛ ወዲህ የሆነው ህገ አራዊትነት ነው፡፡ ሰላማዊ ትግል ሰላማዊ ነውና፡፡
አንድነት ፓርቲም ከ 33ቱ ፓርቲዎች ጋር በመሆን መስከረም 05 ለማድረግ ያቀደው ሰለፍ በመንግስት እውቅና አግኝቶ ለመስከረም 19 መተላለፉ የመለካም ጅማሮው አካል ነው፡፡ አንድቶች በአቋማቸው መፅናታቸው የሰላማዊ ትግል መስመር እስከተከተሉ ድረስ ወደኋላ አለማለታቸው ትግሉ መሬት እየወረደ እንደመጣ ማሳያ ነው፡፡ ከኛም የሚጠበቀው ነገር ከጎናቸው መሰለፍ ነው፡፡ ነፃነት እንዲሁ አይገኝም፡፡ የሚከፈለው መከፈል አለበት፡፡ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችም የአንዱን ስራ ሌላው እያጣጣለ ሳይሆን እውቅና እየሰጡ መቀጠል አለባቸው፡፡ ከምንም በላይ ከልብ አብሮ ስለመስራት ሊያስቡ ይገባል፡፡ይህ ሲባል ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ ሳይሆን በርዕዮተ አለም ከሚመሳሰሏቸው ጋር በጋራ ቢሰሩ የህዝብንም ድጋፍ ለማግኘት ይችላሉ፡፡ የሚያስፈልገው እንዲሁ መሸነጋገል ሳይሆን ከልብ አብሮ መስራት ነውና ያ ቢጠናከር መልካም ነው፡፡
No comments:
Post a Comment