‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም የምንለው ነገር የለም›› የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሕገ መንግሥቱና በምርጫ አዋጅ የተፈቀደን ሰላማዊ ሠልፍና ቅስቀሳን የሚከለክል ደንብ በድብቅ በማፅደቅና በማውጣት፣ ከነሐሴ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ማድረጉን አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አስታወቀ፡፡
አንድነት ፓርቲ አስተዳደሩ አዲስ ደንብ አውጥቶ በሥራ ላይ ማዋሉን አረጋግጫለሁ ያለው፣ ‹‹የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት›› በሚል መሪ ቃል ለሚያካሂደው ሰላማዊ ሠልፍ ቅስቀሳ ሲያደርግ አባላቶቹ ‹‹ፈቃድ የላችሁም›› እየተባሉ ስለሚታሰሩበት፣ ‹‹ለምን ይታሰራሉ?›› በማለት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ሲጠይቅ መሆኑን የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ አስራት ጣሴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የፓርቲው አመራሮች የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊዎችን ሲያነጋግሯቸው፣ አስተዳደሩ ነሐሴ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. በሸኝ ደብዳቤ የላከላቸው በግምት 15 ገጽ የሚሆን ደንብ ቅስቀሳ ለማድረግና የተለያዩ ወረቀቶች ለመበተን ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ስለሚገልጽ፣ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ሌላ አካል ይኼንን ለማድረግ ሲነሳ ፈቃድ መያዝ እንዳለበት እንዳስረዷቸው አቶ አስራት ተናግረዋል፡፡
በምርጫ አዋጅ ሕግ 573/2000 አንቀጽ 46 ላይ እንደተደነገገው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝቡን የፖለቲካ ግንዛቤ ማዳበር፣ የፓርቲውን የፖለቲካ ዓላማ ለሕዝቡ ማስረዳት፣ ዜጐች በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማንቀሳቀስ የዕለት ተዕለት ሥራዎች እንጂ፣ ፈቃድ የሚፈልጉ አለመሆናቸውን አቶ አስራት ጠቁመዋል፡፡ እነዚህን ሥራዎች የሚያከናውኑት ደግሞ በበራሪ ወረቀት፣ በመኪና ላይ ቅስቀሳና አዳራሽ ውስጥ ስብሰባ መሆኑን አክለዋል፡፡
‹‹እየታሰርንና የቅስቀሳ መሣሪያዎቻችንን ስንቀማ የከረምነው በማናውቀው ደንብ ኖሯል?›› ያሉት አቶ አስራት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በካቢኔ ፀድቆ በመውጣት ተግባራዊ ተደርጓል የተባለውን ደንብ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ስላልሰጣቸው ወደ አስተዳደሩ ማምራታቸውን አውስተዋል፡፡
ወደ ከተማ አስተዳደሩ ሄደው ከንቲባ ድሪባ ኩማን ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ባይሳካላቸውም፣ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅነታቸው ተነስተው የከንቲባው ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው የተሾሙትን አቶ አሰግድ ጌታቸውን አግኝተው ማነጋገራቸውን አቶ አስራት አስረድተዋል፡፡
ደንቡ በካቢኔ ፀድቆ በሥራ ላይ መዋሉን፣ ለሕትመት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በመላኩ ሊሰጧቸው እንደማይችሉ አቶ አሰግድ እንዳረጋገጡላቸው የተናገሩት አቶ አስራት፣ በሕገ መንግሥቱና በምርጫ ሕግ የተሰጠን መብት በምን ዓይነት የሕግ ትርጉም ሊከለከል እንደተቻለ ባይገባቸውም፣ የአስተዳደሩ አካሄድ ግን ትክክል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ለአስተዳደሩ በደብዳቤ በማሳወቃቸው በዚህና በቅርቡ ወጥቷል ስለተባለው አዲስ ደንብ ከንቲባውን ለማነጋገር ቢመላለሱም ነገ ከነገ ወዲያ እየተባለ ሊያገኟቸው እንዳልቻሉም አቶ አስራት ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ከአራት ወር በላይ ሲዘጋጁበት የነበረን ሰላማዊ ሠልፍ መስከረም 5 ቀን ፓርቲያቸው እንደሚያካሂድ ለአቶ አሰግድ ሲገልጹላቸው፣ ሰላማዊ ሠልፉን ከመስቀል በኋላ እንዲያደርጉት እንደጠየቋቸው ጠቁመዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ በተፈቀደው መሠረት ፓርቲያቸው ካሳወቀ ከ48 ሰዓታት በኋላ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ እንደሚችል የገለጹት አቶ አስራት፣ መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ሠልፉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
አስተዳደሩ ያወጣው ደንብ ይከለክላል ከተባለ በሕዝቡ ላይ ችግር ቢፈጠር ኃላፊነቱ ማን እንደሚወስድ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ አስራት፣ ሰላማዊ ሠልፍ በሚወጡ ዜጐችና ቅስቀሳ በሚያደርጉት ላይ ለሚከሰቱ ጉዳቶች ኃላፊነቱን የሚወስዱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና መንግሥት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቦታ ባይሰጣቸውም ሕዝብ ለማገልገል በሕዝብ ተመርጫለሁ የሚል አስተዳደር አዲስ ደንብ ሲያወጣ ሕዝቡ እንዲጠነቀቅ ወይም የተፈቀደለትን መብት እንዲለማመድ ለምን ይፋ አይደረግለትም? በማለት የሚጠይቁት አቶ አስራት፣ ሰላማዊ ሠልፉን ፓርቲያቸው በሕገ መንግሥቱና በሕጉ መሠረት እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል፡፡
‹‹እኛ እያሳሰበን ያለው የሰላማዊ ሠልፉ ጉዳይ ሳይሆን በሕግና በሥርዓት መመራታችን ነው፡፡ አገርን ያህል ትልቅ ነገር ይዘው እንደዚህ ነው የሚሠሩት? ይኼ አደጋ ነው፤›› ያሉት አቶ አስራት፣ ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ተልዕኮ ያለው ፖሊስ በሕገወጥ መመርያ አባሎቻቸውን ከማሰርና ከማዋከብ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል፡፡ አንድነት ፓርቲ መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ለሚያካሂደው ሰላማዊ ሠልፍ የፀጥታ ማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በድብቅ አፅድቆ በተግባር ላይ እንዲውል አድርጐታል ስለተባለው ደንብ ማብራሪያ እንዲሰጡን የአስተዳደሩን የኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች አነጋግረናቸው፣ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም የምንለው ነገር የለም፤›› ከማለት ውጭ ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡
ከሪፖርተር ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment