Wednesday, September 18, 2013

ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ከዘለፋና ስድብ ይለያል ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ይህችን አነስተኛ ግን ግልጽነት በጣም የተንጸባረቀባትን ፈታኝ ወረቀት ለመጻፍ ያነሳሳኝ ሰሞኑን ያነበብኩት የአንድ መረንና አሳዳጊ የበደለው ወጣት ‹ጋዜጠኛ› ጽሑፍ ነው፡፡ የዚያ ዋልጌ ሰው ጽሑፍ ዋና ዓላማ ዶክተር ብርሃኑ ነጋን በተቃውሞው ጎራና በወያኔ ፊት ማሽሟጠጥና በነጻነት ታጋዩ ማኅበረሰብ ዘንድም ሣቅና ሥላቅ እንዲጎርፍበት ሙከራ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ሰው በአንድ ሰው ላይ ሊኖረው የሚገባው የማጥላላትና ጥላሸት የመቀባት መጠን ገደብ ሊበጅለት እንደሚገባ ስለማምን ይህን በሳይጋገር ተቦካ የምዕራብ ልቅ ዴሞክራሲና የ911 የሕጻናት ወደፖሊስ መደወያ ስልክ ዓይነት ሞልቃቃነት የተበከለ ስድ አደግ ወጣት ‹ጋዜጠኛ› ልኩን እንዲያውቅ ለማድረግ ፈለግሁና ብዕሬን እያነሳሁ በ‹ይቅርብኝ›ና በ‹ጽፌው ይውጣልኝ› መንታ ሃሳብ መካከል ስባዝን ቆይቼ በመጨረሻው ተሳካልኝ መሰለኝ ይሄውና ጀመርኩ፡፡
እንደነዚህ ዓይነቶችን ሰለጠነች ሲሏት የባሏን መጽሐፍ ያጠበችዋን ሴትዮ የመሳሰሉ አሻቃባጮችንና ቅቤ ጠባሾን በጊዜ ሃይ ካላልናቸው ነገ እላያችን ላይ ሊያቀረሹ ቢነሱ የሚከለክላቸው እንደማይኖር መገመት አይቸግርም – ሞት በእንቅልፍ እንደሚለመድ አምባገነንነትና ነፍራቃነትም እንዲሁ ከልጅነትና ከልጓምየለሽነት ይጀምራል – መሰልጠንና መማር ጥሩ ነው፤ ግን ልክንና ገደብን ማወቅ መልካም ነው፡፡ በፈረንጅ ፍርፋሪ ሆድን ቀብትቶ አለልክ በመጥገብ ባህልንና ሀገራዊ ጨዋነትን መርሳትና መደፍጠጥ ዋልጌነት እንጂ ሥልጣኔ ሊባል አይችልም፡፡ የመናገር ነጻነት አለን ብለው በፈረንጅ ሀገር የፈረንጅ በርገር በቆመጠ አፋቻው ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ጭራሽ ባፈነገጠ መንገድ ክቡርና ንዑድ ዜጎቻችንን እንዲህ ሲዘልፉ ዝም ማለት በትንሹ ነውር ነው – ከፍ ሲልም የመተባበር ያህል ነው፡፡

No comments:

Post a Comment