አዲሱ ዓለምሰገድ በአዲስ አበባ ከተማ በንግድ የሚተዳደር ወጣት ነው፡፡ የማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች አባል ሆኖ በካድሬነት ተንቀሳቅሶ አያውቅም፤ ለወደፊቱም ፍላጎት የለውም፡፡
በአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ግን አያገባኝም የሚል አይደለም፡፡ የመሰለውን ይጽፋል፣ ይሳተፋል፣ ይመርጣል፣ ይደግፋል፣ ይቃወማል፡፡ ከአንድ ዜጋ የሚጠበቅ የፖለቲካ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ የክርስትና ወይም የእስልምና እምነት ተከታይ አይደለም፡፡ በ1997 ዓ.ም. የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ደጋፊ ነበር፡፡ ሃይማኖትን በተመለከተ በወቅቱ ሁለት ነገሮችን ያስታውሳል፡፡ አንዳንድ ለነፍሳቸው ያደሩ መነኮሳት ሳይቀሩ በየቤተ ክርስቲያኑ ፀረ ኢሕአዴግ ቅስቀሳ ሲያደርጉ አስተውሏል፡፡ ይህ አንዳንድ ጊዜ ከሃይማኖት አስተምህሮዎች ጋር እየቀላቀሉ አንዳንድ ጊዜም በቀጥታ ይካሄድ እንደነበር ልብ ብሏል፡፡ በተቃራኒው አዲሱ ወደ መስጊድ ባይሄድም ኢሕእዴግ በአንዳንድ አካባቢዎች የእስልምና እምነት ተከታዮች ኢሕአዴግን እንዲመርጡ የተለየ ቅስቀሳ ሲያደርግ ታዝቧል፡፡
ይኼንንም ሙስሊም ጓደኞቹ በወቅቱ አረጋግጠውለታል፡፡ ይህ ቅስቀሳ በህቡዕ የሚደረግ እንጂ በግልጽ ወጥቶ በአደባባይ የተሠራ አልነበረም፡፡ በመሆኑም፣ ‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ አይገባም፤›› የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መርህ ጠንቅቆ የሚገነዘብ ቢሆንም፣ አዲሱ በአሁኑ ወቅት በተግባር በፖለቲካና በሃይማኖት መካከል ያለው ርቀትና ቅርበት ውዥንብር ፈጥሮበታል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሙስሊሙን ማኅበረሰብ የሚመለከቱ ጥያቄዎች እየተበራከቱ ናቸው፡፡ መንግሥት በአወልያ ቀደም ሲል ይሰጥ በነበረው እስላማዊ አስተምህሮ ምክንያት የእምነት ተከታዮቹ ‹‹እስላማዊ መንግሥት››ን የማቋቋም አስተምህሮን ተፅዕኖ ለማስወገድ መንቀሳቀሱን ይገልጻል፡፡ ይህም ሕገ መንግሥታዊ ግዴታው እንደሆነ በመግለጽ ነው፡፡ መንግሥት በመረጃ መዋቅሩ ደረስኩባቸው የሚላቸው ጉዳዮችን ለሕዝብ ሲያቀርብ የአክራሪነት አስተምህሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መዳረሱን እየጠቀሰ ለሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ምክንያት ሲያቀርብ ይስተዋላል፡፡ ለዘብተኛ የሚለውን የአህባሽ ትምህርት አስተማሪዎች ከሊባኖስ መጥተው እዚሁ እንዲያስተምሩ ሁኔታዎችን አመቻችቷል ተብሎም ይተቻል፡፡
የተለያዩ የእስልምና እምነት ጥያቄዎችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ወገኖችም፣ ባለፈው ዓመት ምርጫ እስከተካሄደ ድረስ የቆየው መጅሊስ ሕገወጥ መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ መንግሥት ‹‹አክራሪዎች›› የሚላቸው እነዚህ ጥያቄ አቅራቢዎች መጅሊሱን እንዳይቆጣጠሩ ሥጋት አድሮበት እንደነበር፣ ምናልባትም ይኼው ሥጋት ይሆናል ምርጫው ባልተለመደ መንገድ በቀበሌዎች እንዲካሄድ ሁኔታዎችን ያመቻቸው ይባላል፡፡
ሃይማኖት እንደ ሽፋን – የኢሕአዴግ ዕይታ
ጉዳዩ ወደ መንግሥት ከመዞሩ በፊት በአንዳንድ አካባቢዎች በእስልምናና በክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል በተነሱ ግጭቶች የሰዎች ሕይወት አልፏል፣ ንብረት ወድሟል፣ ቤተ ክርስቲያናትና መስጊዶችም ተቃጥለዋል፡፡ የኢሕአዴግ የፖለቲካ ፍልስፍና ንድፈ ሐሳብ የሚተነተንበት አዲስ ራዕይ መጽሔት ከጥር እስከ የካቲት 2001 ዓ.ም. ሕትመት፣ በፖለቲካ አምዱ ‹‹ሃይማኖትን እንደ ሽፋን የከሠሩ ፖለቲከኞች የወቅቱ ስልት›› በሚል ርዕስ በወቅቱ የተከሰቱ ግጭቶች በዚያው ዓመት በጥምቀት ወር የተስተዋለውን የአክራሪነት አዝማሚያ መሠረት አድርጎ ይተነትናል፡፡ ጽሑፉ ሲጀምር እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች አክራሪና የከሰሩ ፖለቲከኞች፣ ሃይማኖትን እንደ ሽፋን ለመጠቀም የቆረጡት እነዚህ ወገኖች በአገራችን ለሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት የተፈጠረውን አመቺ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ በመጠቀምና የመንግሥትን ቻይነት እንደ ድክመት በመቁጠር በአደባባይ ሕግን ተላልፈው እስከመንቀሳቀስ ደርሰዋል፡፡ ቀላል የማይባል ብዥታና መደናገርን እየፈጠሩ ኅብረተሰቡን በሃይማኖት ሳቢያ ወደሚቀሰቀስ ግጭት ለማምራት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፤›› ብሎ ነበር፡፡
ጉዳዩ በቸልታ ከታለፈ ሊያስከትለው የሚችለው አደጋ ከባድ በመሆኑ የጠራ አቋም መያዝ አስፈላጊ መሆኑን ጽሑፉ ያትታል፡፡ ለትንታኔው መነሻ የሆነውን ሲያስረዳ ጽሑፉ በጥምቀት በዓል ‹‹ኢትዮጵያ የክርስትና አገር ነች›› የሚለውን መፈክር ያስፍር እንጂ፣ በአጠቃላይ በሁለቱም እምነቶች መካከል በሲዲና በጽሑፍ የሚወጡ ግጭቶችን የሚቀሰቅሱ ሐሳቦች ከማስተጋባት አልፈው ግጭቶች በተጨባጭ መከሰታቸውን ያብራራል፡፡
መጽሔቱ እንደሚያትተው፣ ሃይማኖቶች በምን መልኩ የትም ቦታ ቢሆን በራሳቸው የግጭት ምንጭ አይደሉም፡፡ የሁሉም ሃይማኖቶች መልካም አስተምህሮ፣ ሕገ መንግሥቱ ለእምነት ነፃነት መቆሙ፣ በተጨባጭ ያለፉት 17 ዓመታት በተግባር ሥልጣን ላይ ያለው አካል በኢትዮጵያ ባልተለመደ ሁኔታ ከየትኛውም ሃይማኖት ያልወገነ መሆኑ ይተነትናል፡፡ ይህ ትልቅ ግምት የሚሰጠው የኢሕአዴግ ትንታኔ፣ ሁለት መሠረታዊ የግጭቶች መንስዔዎችን አስቀምጧል፡፡ አንደኛው በተለይ በ1997 ዓ.ም. ‹‹ከተቻለ በምርጫ ካልተቻለ በኃይል›› የሚል አቋም ያላቸው ኃይሎች የመጨረሻ መደበቂያ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው የምዕራቡ ዓለምና የመካከለኛው ምሥራቅ አክራሪ ኃይሎች ለሚያካሂዱት ዓለም አቀፍ ፍልሚያ አውድማ አድርገው ለመጠቀም መሞከራቸው ነው፡፡ ይኼውም ኢሕአዴግ አክራሪ ኃይሎች የሚላቸውን የሁለቱም ዓለም ወገኖች፣ ኢትዮጵያን እንደ ‹‹ክርስቲያን ደሴት›› የመመልከት የጋራ አቋም እንዳላቸው አመላካች ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ በሃይማኖት ስም ሊነሳ የሚችል ግጭት ሁለተኛው መንስዔ ሲሆን፣ ለዚህም የምዕራብ አክራሪዎች ‹‹እስልምና ወደ ደቡባዊ አፍሪካ እንዳይስፋፋ የሚከላከሉበት አውድማ›› (ገጽ 11) አድርገው በመቁጠር ‹‹ዘመናዊ የመስቀል ጦርነት›› አካል ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በተፃራሪ እስልምና የአፍሪካዊያን መመርያ መሆን አለበት ብለው የሚያምኑ የመካከለኛ ምሥራቅ አክራሪ ኃይሎች፣ ባላቸው የገንዘብ አቅም ተማምነው ሰፊና ያልተቆጠበ ዘመቻ ያካሂዳሉ የሚል ነው፡፡
የመካከለኛው ምሥራቅ አክራሪ ኃይሎች ሌላው ቀርቶ ሶማሊያን እንደ መነሻ በመቀጠም አፍሪካን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ በእስልምና ሃይማኖት ለማጥመቅ ማሰባቸውን ይተነትናል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የውጭ ተፅዕኖ ለመከላከል በሰብዓዊ ዕርዳታም ሆነ በሃይማኖት ስም የሚመጡ ማናቸውም ጣልቃ ገብነቶች ይህንን ዓላማ ለማራመድ ዋነኛ መንገዶች መሆናቸውን ይተነትናል፡፡ ከዚህ ውጪ ኢሕአዴግ በዚህ ትንታኔው እንደ መንስዔ በሦስተኛ ደረጃ ያነሳው ‹‹በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች በግላዊ እምነታቸውና በመንግሥት ኃላፊነታቸው መካከል ልዩነት ማድረግ ሲሳናቸው›› (ገጽ 11) መሆኑን ያስረዳል፡፡ እንደ ማሳያ የቀረበውም ሃይማኖታዊ አምልኳቸው በመንግሥታዊ አገልግሎት አሰጣጣታቸው ላይ ጣልቃ የሚገባባቸው ጊዜ መኖሩን ነው፡፡
‹‹የኦርቶዶክስ አማኝ ከንቲባ ሲሆን ለኦርቶዶክስ መሬት እንደ ልብ የሚሰጥ፣ የፕሮቴስታንት አማኝ ለፕሮቴስታንት፣ የእስልምና እምነት ተከታዩ ደግሞ ለሙስሊም ሃይማኖት መሬት ቅድሚያ የሚሰጥባቸው አካሄዶች የታዩበት ሁኔታ በግልጽ አጋጥሟል፤›› ይላል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸው ሃይማኖታዊ ወገናዊነትን ታሳቢ ማድረጋቸውን ያስገነዝባል፡፡
እዚሁ ላይ ኢሕአዴግ በሃይማኖት ሽፋን የሚራመደውን የፖለቲካ ግጭት ስልት ለማምከን መወሰድ ካሰባቸው ዕርምጃዎች መካከል፣ የድርጅቱ አባላት በጉዳዩ ላይ የጠራ አቋም እንዲኖራቸው ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው መላውን ሕዝብ ለሰላም በፅናት እንዲታገል ማድረግ በሚለው ላይ አንድ አመላካች ጉዳይ ሰፍረዋል፡፡ ‹‹በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሰርገው የገቡ አሳዊ መሲሂዎች ቤተ ክርስቲያኖችና መስጊዶችን የፖለቲካ መድረክ ለማድረግ የሚያካሂዱትን ጥረት ማምከን የሚቻለው፣ ሰፊው ምዕመን ከሃይማኖቱ ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን የፖለቲካ ስብከቶች ለማስወገድ ሲችል ብቻ ነው፤›› ይላል፡፡ በመሆኑም፣ ‹‹የሃይማኖትን ጭምብል አጥልቀው›› የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ለማምከን፣ ‹‹ሃይማኖትን ከፖለቲካ ለመነጠል ሰፊ ውይይት›› (ገጽ 17) ሲካሄድ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡
ከትንታኔው በስተጀርባ
በኢሕአዴግ ትንተና ሃይማኖት ውስጥ ምንም ዓይነት ለግጭት ምክንያት የሚሆን የተመቻቸ ሁኔታ የለም፡፡ ነገር ግን ሃይማኖትን እንደ ሽፋን የሚጠቀሙ አክራሪ የፖለቲካ ኃይሎች መደበቂያ ጉድጓድ ሆኖ ማገልገሉን ነው፡፡ ይህ የኢሕአዴግ እምነት በቅርቡ በታተመው በዚሁ የንድፈ ሐሳብ መጽሔቱም (ከሐምሌ እስከ ነሐሴ 2005) ተመሳሳይ ትንታኔ ሰጥቶበታል፡፡ በቀደመው የትንታኔ መገለጫ በሚመስለው ትንተና ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ሃይማኖት ያራምዳሉ ያላቸውን የመንግሥት ኃላፊዎቹ ሲያጋልጥ ተስተውሏል፡፡ በሌላ በኩል ሕዝቡን በእምነቱ ውስጥ ተሸሽገው አመለካከቱን እየበረዙት ነው ያላቸውን ለመነጠል በሁለቱም ሃይማኖቶች ውስጥ ግልጽ ያልሆነ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡ በኦርቶዶክስ እምነት አመራሮች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ውዝግብ አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች እንደ አስታራቂዎች ሆነው በሃይማኖቱ ዙርያ ሲንቀሳቀሱ ይታዩ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአቡነ ጳውሎስ ሕልፈት በኋላ ውዝግቡ እየቀዘቀዘ የመጣው የክርስትና እምነት አመራሮች ሽኩቻ ወደ እስልምና እምነት የተሸጋገረ ይመስላል፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በምንም ሁኔታ ጣልቃ መግባቱን የማይቀበል ቢሆንም፣ ምናልባት አክራሪዎች የሚላቸውን ለመነጠል በተዘዋዋሪ ሊሰኝ በሚችል ጣልቃ መግቱ አንዳንድ የሃይማኖት ግጭት አጥኚዎች ያምናሉ፡፡
አክራሪዎችን ለመነጠል በእስልምና እምነት ውስጥም፣ ውጭም የታሰበው ሕዝባዊ ውይይት መንግሥት እንደ ተገቢ ዕርምጃ የወሰደው ሲሆን፣ በአንዳንድ የእምነቱ ተሟጋቾች ዘንድ እንደ ጣልቃ ገብነት እየታየ ነው፡፡ ከውጭ ኃይሎች በሚገኝ ገንዘብ አመለካከታቸውን ለመጫን እየሞከሩ ነው ያላቸው ሰዎች ከአወልያ ትምህርት ቤት እንዲወገዱ በመጅሊሱ በኩል ጥረት መደረጉ ይነገራል፡፡ የሙስሊም ማኅበረሰቡ አስተሳሰብ እንዳይበረዝ በሚል የአህባሽ ትምህርት በየመስጊዱ እንዲሰጥ የተደረገውም በመጅሊሱ አማካይነት ቢሆንም የመንግሥት እጅ አለበት የሚል ክስ ይቀርባል፡፡
በተለይ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚና ምን እንደነበር በግልጽ ባይታወቅም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በናዝሬትና በአዲስ አበባ በተደረጉ የጋዜጠኞች ውይይቶች ላይ መገንዘብ እንደተቻለው ግን፣ የሙስሊም ማኅበረሰቡ በተለያዩ መንገዶች የአክራሪነት አመለካከቶች በኃይል እየተጫኑዋቸው ነው በሚል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ እንደተገደደ ነበር፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሙስሊም ማኅበረሰቡና በመንግሥት መካከል የተስተዋለው ይኼው ከፍተኛ ውዝግብ ጣራ ነክቶ፣ በተለይ በዕምነት ተከታዮቹ የሚደረጉ አመፆች አስተባባሪ የሚላቸውን በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡ በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን በአንድ ላይ ለማውገዝ ብሔራዊ ኮንፈረንስ ተጠርቶ ነበር፡፡ ቀጥሎም ይህንን አክራሪነት የሚቃወም ሰላማዊ ሠልፍ በመስቀል አደባባይ ተጠርቷል፡፡
መንግሥት ይህንን ዕርምጃ እየወሰደ ያለው በ2001 ዓ.ም. በሰጠው ድርጅታዊ ትንታኔ፣ ሃይማኖት በምርጫ የከሰሩ አክራሪ የፖለቲካ ኃይሎች መደበቂያ እየሆነ ነው ለሚለው አቋሙ ማረጋገጫ የሚመስል በመመልከቱ ነው፡፡
ሃይማኖትና ፖለቲካ በተቃዋሚዎች ዕይታ
በቅርቡ የተመሠረተው ሰማያዊ ፓርቲና አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ፀረ ሽብር አዋጁ እንዲቀየር በሚያደርጉዋቸው ሰላማዊ ሠልፎች ይኼው የሙስሊሞች ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ ታይቷል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ‹‹ፖለቲካና ሃይማኖት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው፤ አይገናኙም ብሎ ነገር የለም፤›› ይላሉ፡፡ ፓርቲያቸው የእስልምና እምነት ተከታዮችን ጥያቄዎች አጀንዳ አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ በማመን፡፡ ፓርቲያቸው መንግሥት በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ገብቷል ብሎ ያምናል፡፡ ኢሕአዴግ ራሱ ታገልኩላቸው ከሚላቸው መካከል አንዱ ጥያቄ የሃይማኖት ነፃነት በመሆኑ፣ የዜጎች የእምነት ነፃነታቸው ሲገፈፍ የመቃወም ኃላፊነት አለብን ይላሉ ኢንጂነር ይልቃል፡፡ ይህንን ሲያደርጉ በእምነቱ ተከታዮችና በፓርቲያቸው መካከል በጋራ የሚሠሩት ነገር እንደሌለ ግን ያስረዳሉ፡፡
በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ እየታየ ያለው ችግር ኢሕአዴግ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ እንደሚያደርገው ሁሉ እሱ የሚፈልጋቸውን መሪዎች ለማስቀመጥ ዜጎችን የመቆጣጠር የግራ ዘመም አባዜው ውጤት ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ በእስልምና እምነት ውስጥ በመንግሥት ጣልቃ ገብቷል ሊያሰኝ የሚችል ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው፣ ነገር ግን ያንን ሲያውቁ እንደሚቃወሙ ይናገራሉ፡፡
የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ከኢንጂነሩ ሐሳብ ጋር በአብዛኛው ይስማማሉ፡፡ ፓርቲያቸው አንድነት የእስልምናን ጉዳይ ግን አጀንዳ አድርጎ አይንቀሳቀስም ይላሉ፡፡ ‹‹ዜጎች የእምነት ነፃነታቸው እንዲከበርላቸው እንታገላለን፤›› ብለው፣ በጉዳዩ ላይ ጎልቶ እየታየ ያለው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንጂ ሽብርተኝነትም፣ እስላማዊ መንግሥት የመመሥረም ጥያቄ አለ ብለው እንደማያምኑ ያስረዳሉ፡፡ ሽብርተኝነት ተብለው ስለተፈረጁትም መንግሥት ያቀረበው መረጃ አሳማኝ አይደለም ብለዋል፡፡
ቀጭኑ ገመድ
አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲ በቅርቡ በጠሩዋቸው ሰላማዊ ሠልፎች እንደታየው፣ ሙስሊሞች በብዛት ታይተዋል፡፡ በተለያዩ መፈክሮቻቸውም የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱና መንግሥት ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም ይጠይቃሉ፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች በሚያቀርበው ትንታኔ ከሁለቱም ጽንፍ ወጥቶ ‹‹ሦስተኛ መንገድ›› አራማጅ መሆኑን የሚያምነው ኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ‹‹ፖለቲካ ፓርቲዎችና ሃይማኖትን አገናኝ ቀጭን ገመድ አለ›› ይላሉ፤ በጥንቃቄ መታየት እንደለበት በማስቀመጥ፡፡ በእሳቸው እምነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማና ግብ ሥልጣን ነው፤ የሃይማኖት ጥያቄ ግን ይኼ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድ የሃይማኖት አማኞችን ጥያቄ እንደ አጀንዳ አድርገው ሲንቀሳቀሱ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ከመፍጠር አልፎ፣ የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ ጥቅም ላይ ከዋለ ገመዱ ተበጠሰ ማለት ነው ይላሉ፡፡
ማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዜጎች በየትኛውም መንገድ የእምነት ነፃነታቸው ሲጣስ መቃወም ቢኖርባቸውም፣ እንደ አጀንዳ አድርገው ከተንቀሳቀሱ ግን የሃይማኖት ተከታዮቹ በዚሁ የፖለቲካ ፓርቲ ይወከላል ማለት ነው፤ ይኼ ደግሞ በሌሎች ሃይማኖት አማኞች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው በማለት ያስረዳሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ሃይማኖት መሠረት በማድረግ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይመሠረት የከለከለውም ለዚሁ ይመስላል፤›› ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ሙሼ እምነት በፖለቲካ ፓርቲዎችና በሃይማኖት ተከታዮች መካከል የሚኖረው ግንኙነት በመጨረሻ የጠረጴዛ ዙርያ ውይይት ለማምጣት ተፅዕኖ ለመፍጠር ብቻ ነው፡፡ ‹‹ከዚያ ከዘለለ ውዥንብር ውስጥ ይገባል፡፡ ይኼ ፓርቲ ቢያሸንፍ ምን ዓይነት መንግሥት ያቋቁማል የሚል ከባድ ጥያቄ ያስከትላል፤›› ይላሉ፡፡
‹‹በሌላ በኩል የእስልምና አማኞች ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው፤ መንግሥት ሰከን ብሎ ተብሎ ጥያቄዎችን መመልከት አለበት፡፡ መንግሥት የሚያቀርባቸው ዶክመንተሪ ፊልሞችና መረጃዎች ተዓማኒነት የላቸውም ወይ? ለሚለው ጥያቄ የዘጋቢ ፊልሞች መረጃዎች አሰባሰባቸው ግልጽ ባለመሆኑ፣ አቀራረባቸውም ሚዛናቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸው የፕሮፓጋንዳ ሥራ ይመስላሉ፤›› ብለዋል፡፡ ሰዎች በሃይማኖት ሽፋን ከሕገ መንግሥቱ ሲቃረኑ ሁሉም የሚቃወመው ቢሆንም፣ መንግሥት የሚያቀርበው መረጃ አሳማኝ አይደለም በማለት ያክላሉ፡፡
Source: Reporter
No comments:
Post a Comment