ጊዜያዊ መረጋጋቶች አዘናግተውን ማዕከላችንን ማስቀማት እንዳይመጣ ጥያቄያችንን አጥብቀን መያዝ እና ተቃውሟችንን ማደስ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ማለት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄዎቹ ምን ያህል ቦታ ያላቸው መሆኑን ተረድቶ ለተጨማሪ መስዋእትነት ዝግጁ መሆን አለበት ማለት ነው፡፡እኛ እየጠየቅን ያለነው በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሃይማኖታዊ ድንበሩን ጠብቆ ከመንግስት እና ከመላው ህዝብ በሰላም የሚሰራ መጅሊስን ነው፡፡ ሙስሊሞች እንደአገሪቱ ዜጋነታችን ያነሳናቸው ጥያቄዎች ከህልውናችን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ በትክክል ቢመለሱ ራሳችንን ቀና አድርገን የምንሄድበት ተጨባጭ እውን ሆነ ማለት ነው፡፡
ሹመትን መጠየፍ መቻል!
ሹመትን መጠየፍ መቻል!
ድምፃችን ይሰማ
መንግስት ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ውጪ በመሆን በራሱ መንገድ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ የራሱን የቀበሌ ሹመት አካሄዷል፡፡ ይህ ሹመት የተካሄደው በሕዝብ የተመረጡ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና በርካታ ሙስሊም ምሁራን ወደ እስር ቤት ከተወረወሩ በኋላና ሙስሊሙ ምርጫውን ከተነጠቀ በኋላም ነው፡፡ ይህ ገና ሳይካሄድ ጭንግፍ የመታው የመንግስት ሹመት በመንግስት ሚዲያ እብጠት ታጅቦ ያለ ሕዝብ ተሳትፎና ይሁንታ ተካሄዷል፡፡ ይህ በወቅቱ ቅርጫ ተብሎ በስፋት ሲገለጥ የነበረው የሹመት ስነ-ስርአት ሕግንም የሐዝብንም ይሁንታ ሆነ ሞራል ያልጠበቀ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡ ለዚህም ነው ተሿሚዎቹ ከህብረተሰቡ ተቃባይነት ያላገኙትና አንዳችም ከቢሮዋቸው ፈቀቅ ማለት ያልቻሉት፡፡ ባለፉት ታላላቅ የሶስት ኢድ ትእይንቶች የታየው ሐዝብዊ ተቃውሞ ተሿሚዎቹ በመንግስት ሚዲያና በመንግስት ጋዜጠኛ ተከቦ ከመናገር በዘለለ በአደባባይ ለሙስሊሙ መልእክት እንኳ ለማስተላለፍ እንደማይቻላቸውና ሙስሊሙም ሳያላምጥ አንቅሮ የተፋቸው መሆኑ በግልጽ ታይቷል፡፡
አንዳንዶች ‹‹ድጋሚ ምርጫ ለማድረግ መንግስት ፍቃደኛ አይሆንም›› ይላሉ፡፡ ይህ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ መብት የሚጠየቀው የመስጠት ፍቃደኝነት ስላለ አይደለም፡፡ ቀድሞ ነገር መብት የሚጠየቀው መብት ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ መብትን ያለትግል ማስከበር ከቶስ እንዴት ይቻላል? መንግስት ይህን ሹመት ስነ ስርአት ያካሄደውና የተገደደውም ቢሆን በዚሁ ትግል እንጂ በፍቃደኛነት አልነበረም፡፡ የመንግስት አላማ የነበረው መንግስታዊውን እምነት (አህባሽ) ለማሰራጨት ሐላፊነቱንና ስልጠናውን ወስዶ የመጣው የአሕመዲን አብዱላሂ ጨሎ የጀመረውን ሂደት እንዲያስቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው፡፡ ያ ግን በተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊሳካ ባለመቻሉ አዲስ የድራማ ሹመት በቀበሌ አዳራሾች ውስጥ አካሄዶ ሌላ ፊት ይዞ መጥቷል፡፡ ይህ የመንግስት የመቀባባት ምላሽ የመጣው ከሕዝቡ ተቃውሞና እምቢተኝትመሆኑን ማወቅና መረዳት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በቀጣይ ይህን የተቀባባ ምላሽ እና ሹመት ወደ ተገቢው የሕዝብ ይሁንታ እንዲለውጥ የመጠየቅና ጫና የማድረግ ሐላፊነት የሕዝቡ ነው፡፡ ይህ መረጋገጥ የሚችለው ቀጣይነት ባለው ትግል ነው፡፡
ሕዝቡ የሚያደርገው ትግልና ደጋግሞ ጠያቂነት ብቻ ነው ተጊው ምላሽ እንዲገኝ በሩን የሚከፍተው፡፡ በዚህ መልኩ አሁንም ትክክለኛና ከመንግስት ተጽእኖ የጸዳ ፍትሐዊ ምርጫ እንዲደረግ ተጽእኖ ማሳደር ይቻላል፤ ይገባልም! ሕብረተሰቡ በተገቢው መልኩ የአሁኑ ተሿሚዎች የመጡበትን ሂደት በተምሳሌታዊ የቀብር ስነ-ስርአት ከመሬት ውስጥ ከቶታል፡፡ ይህን ያደረግነው ያለ ፈቃዳችን በመንግስት ኋይሎች የተጫነብንን ሹመት ስለምንጠየፍም ጭምር ነው፡፡ የመርህ ጥያቄም መዘንጋት የለበትም፡፡ በመንግስት የተቀነባበረ ድራማ የተደረገውን ሹመት እውቅና መስጠት ማለት ለኢፍትሐዊ አስተዳደርና ሂደት እውቅና መስጠት፤ ይህን ተከትሎ ለሚከሰተው ምስቅልቅልና ውጣ ውረድም ራስን ተጠያቂ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከባድ ስህተት ነው፤ ያውም የመርህ ስህተት! የፍትህና የነፃነት ጥያቄ ለጊዜያዊ ጥቅም ወይም ለሌላ ምክንያት የሚሸራረፍ ከሆነ የቆምንበትን መሰረት መናድ አይሆንምን? ለዚያም ነው ትክክለኛ መጅሊስ እንዲኖረን ከፈለግን በቆራጥ አቋም ተቃውሟችንን መቀጠል ይኖርብናል የምንለው፡፡
የአወሊያ ትምህርት ቤት ጉዳይም ቢሆን ሌላው አጽንኦት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ የአወሊያ ጉዳይ የመጅሊስ ጥያቄ በአግባቡ ሲመለስ አብሮ የሚመለስ ነው፡፡ አወሊያ በጥያቄነት የተነሳው የአህባሽ አይዶሎጂ ማጥመቂያ ማእከል ለማድረግ የተደረገውን ሙከራ ለመቃወምና ለማስቀረት ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ለጊዜው የአህባሽ መጠቀሚያነቱ መቅረቱ ‹‹ችግሩ ተፈታ›› አያስብልም፡፡ መጅሊስ የአህባሽን አጀንዳ ለማስፈፀም መንቀሳቀሱን እስካላቆመ በፈለገው ግዜ እጁ ላይ ያለውን ተቋም ለዚሁ ዓላማ መጠቀሙ የማይቀር ነው፡፡
እርግጥ አወሊያ መጅሊስ በትክክለኛ ምርጫ የምንፈልገውን ህዝባዊ አቋም ከያዘ በመጅሊስ ስር መሆኑ ለድርድር ሊቀርብ ይችላል፤ አወሊያን እንዲያስተዳድረው የምንፈልገው የተለየ አካል የለንምና! አወሊያ የተቋቋመበትን ዓላማ በተሻለ መልኩ ለማስፈጸም የሚችል ማንኛውም ተቋም ሊያስተዳድረው ይችላል፡፡ ሃይማኖታዊ ዓላማውን ማደናቀፍና ለሌላ ተቃራኒ ዓላማ እንዲውል ማድረግ ግን አሁንም የማንቀበለው እና ተቃውሟችንን የምንቀጥልበት ጥያቄ ነው፡፡
አወሊያን ለባእድ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆን ለማድረግ ከተፈለገ ወይ ለብቻው ገንጥሎ በምናምነው ተቋም ወይም ቦርድ ስር እንዲሆን፣ አሊያም መጅሊስን ሙሉ ለሙሉ አስተካክሎ በመጅሊስ ስር እንዲተዳደር ማድረግ ይገባል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ጊዜያዊ መረጋጋቶች አዘናግተውን ማዕከላችንን ማስቀማት እንዳይመጣ ጥያቄያችንን አጥብቀን መያዝ እና ተቃውሟችንን ማደስ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ማለት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄዎቹ ምን ያህል ቦታ ያላቸው መሆኑን ተረድቶ ለተጨማሪ መስዋእትነት ዝግጁ መሆን አለበት ማለት ነው፡፡
እኛ እየጠየቅን ያለነው በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሃይማኖታዊ ድንበሩን ጠብቆ ከመንግስት እና ከመላው ህዝብ በሰላም የሚሰራ መጅሊስን ነው፡፡ ሙስሊሞች እንደአገሪቱ ዜጋነታችን ያነሳናቸው ጥያቄዎች ከህልውናችን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ በትክክል ቢመለሱ ራሳችንን ቀና አድርገን የምንሄድበት ተጨባጭ እውን ሆነ ማለት ነው፡፡ መጅሊስን በነፃነት እንደእምነታችን ብንጠቀም፣ ህዝባችንንም ተጠቃሚ ብናደርግ ከቶ የትኛው አካል ይጎዳል? ተቋም ሳይኖረውና ሳይደራጅ ይህንን ያህል ሰላማዊና ጨዋ ብሎም ለሃገር ተቆርቋሪ የሆነ ህዝብ እንዴትስ ለአገር ስጋት ሊሆን ይችላል?
አዎን! ጥያቄዎቻችን ግልጽ ናቸው! እስኪመለሱልን ድረስም በቁርጠኝነት እንታገላለን! ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!
አላሁ አክበር!
No comments:
Post a Comment