Wednesday, April 10, 2013

መንግስት በመለስ ፋውንዴሽን ውስጥ ጣልቃ መግባቱን የአቶ መለስ ልጅ ተቃወመች የአቶ መለስ ዜናዊን ምስል ያለፈቃድ መጠቀም ሊከለከል ነው


በዘሪሁን ሙሉጌታ

የቀድሞ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የበኩር ልጅ ወጣት ሰምሀል መለስ ባለፈው ቅዳሜ በተቋቋመው “የመለስ ፋውንዴሽን” ውስጥ መንግስት ጣልቃ መግባቱን ተቃወመች።
ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2005 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው የፋውንዴሽኑ የማቋቋሚያ መስራች ጉባኤ ላይ ወጣት ሰምሀል ፋውንዴሽኑ የመለስ አስተሳሰብ ምንጭ መሆን ሲገባው መንግስት በፋውንዴሽኑ ላይ ሚናው መጉላቱ ተገቢ አለመሆኑን ተናግራለች።
ወጣት ሰምሀል በፋውንዴሽኑ ምስረታ ወቅት “አሰራሩ እኔ አልገባኝም። ከዚህ በፊትም ቤተሰብ አንስቶ ነበር። በአዋጁ ላይ የመንግስት ሚና መጉላቱ ስህተት ነው ብለናል” ስትል ተቃውሞዋን አሰምታለች።
ሰምሀል የመንግስትን በፋውንዴሽኑ ጣልቃ መግባትን ብትቃወም ከፋውንዴሽኑ 13 የቦርድ አባላት አራቱ ከቤተሰባቸው ዘጠኝ ደግሞ የመንግስት አካላት ሆነው የተመረጡ ሲሆን ወደፊት አዋጁን በማሻሻል ሌሎች አካላትን ለማሳተፍ ከመታሰቡ ባለፈ በዕለቱ የሰማህል ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
በተያያዘ ዜና የቀድሞ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ምስል ያለቤተሰቦቻቸውም ወይም በስማቸው ከተቋቋመው ፋውንዴሽን ፈቃድ ውጪ በማንኛውም ቦታ መለጠፍም ሆነ ምስላቸውን ቀርፆ መጠቀም ሊከለከል ነው።
የአቶ መለስን ምስል ያለፈቃድ መጠቀምን የሚከለክለው ረቂቅ መመሪያ የተዘጋጀው በአዋጅ ቁጥር 781/2005 አንቀፅ ዘጠኝ ንዑስ አንቀፅ 2(ሰ) መሰረት ነው።
ረቂቅ መመሪያው ባለፈው ቅዳሜ የመለስ ፋውንዴሽን ይፋ በተደረገበት ወቅት ለውይይት ተበትኗል። በረቂቅ መመሪያው ስለ ምስላቸው አጠቃቀም በሚያወሳው አንቀፅ 8 ንዑስ አንቀፅ (1) ላይ ማንኛውም ሰው ለክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ያለውን ፍቅርና ክብር ለመግለፅ ምስሉን በመኖሪያ ቤቱ ግድግዳ ላይ ሊሰቅል፣ በአልበም ውስጥ፣ በቦርሳው፣ በኪሱ፣ በተሽከርካሪው ወይም በሌላ የግል መጠቀሚያው ሊይዘው ከሚችለው በስተቀር ምስላቸውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ፣ ለሽያጭ፣ ለባዛር፣ ለጨረታ ወይም ለማንኛውም የንግድ ድርጅት ወይም ሌላ ተቋም ማስታወቂያ፣ የንግድ ምልክት፣ ለመታሰቢያነት ወይም ለማንኛውም ጥቅም ማስገኛነት ሊሰቅል ወይም ሊቀርፅ ወይም በማንኛውም ሁኔታ ሊያስቀምጥ እንደማይችል አስቀምጧል።
ከዚህ በተጨማሪ የአቶ መለስን ምስል በተለየ ሁኔታ ለህዝባዊ አላማና ጥቅም ለመጠቀም የፈለገ አካል ከቤተሰባቸው ወይም ከፋውንዴሽኑ ቦርድ ፈቃድ ማግኘት እንዳለበት መመሪያው ያስገድዳል።
በተያያዘም ከፋውንዴሽኑ ፈቃድ ውጪ በአቶ መለስ ዜናዊ ስም ማንኛውንም አይነት ግንባታ ለመገንባት በማሰብ የእሳቸውን ስም፣ ምስል ወይም ስራዎች በመጠቀም ገንዘብ ወይም ቁሳቁስ መሰብሰብን ረቂቅ መመሪያው ከልክሏል።¾

No comments:

Post a Comment