Friday, April 12, 2013

ጀግንነት ባህሪው የሆነ ሰው ፣ብሔር ሳይለይ ድንበር ሳያበጅ ጀግናን ያከብራል!

ጀግንነት ባህሪው የሆነ ሰው ፣ብሔር ሳይለይ ድንበር ሳያበጅ ጀግናን ያከብራል!
በወረዳው አንድ ለእናቱ በነበረው አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ትምህርት ቤት የተወሰኑ መምህራን ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ሁለት ሰዓት አካባቢ ጥሪ ተላለፈ፡፡ ስብሰባው የሚጀመረው ሦስት ሰዓት ላይ መሆኑም አብሮ ተነግሯል፡፡ የትምህርት ቤቱን ፀጥታ የሚቆጣጠሩ አንድ የፈረቃ መሪ መምህር ብቻ እንዲቀሩ ተደረገና ዋና እና ምክትል ርዕሰ መምህሮቹን ጨምሮ፣ የትምህርት ክፍል ሃላፊዎች፣ የፈረቃ መሪዎች ወዘተ. ወደ መሰብሰቢያው አዳራሽ ተመምን፡፡ እርግጥ ነው፣ ሁለት መምህራን በስም ተለይተው ስብሰባው ላይ እንዲገኙ ለርዕሰ መምህሩ ቀጭን ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል፡፡ በአዳራሹ በግምት ወደ መቶ የሚጠጉ ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል፡፡ እንደተለመደው ሦስት ሰዓት የተባለው ስብሰባ አራት ሰዓት አካባቢ ተጀመረ፡፡
ሰብሳቢዎቹ የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊ፤ የወረዳው የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊና ምክትል አስተዳዳሪው ነበሩ፡፡ ሁለቱ አጃቢና የሚነሱ ጥያቄዎች መላሺ ሲሆኑ፣ የመወያያውን አጀንዳ የሚያቀርቡ ወይም የተዘጋጀውን ጽሑፍ የሚያነቡ ምክትል አስተዳዳሪው ናቸው፡፡ የመወያያ ጽሑፍ አንባቢው ሰው፣ “የዛሬ ስብሰባ አጭር ነው…ከምሣ ሰዓት በፊት ነው የሚያልቀው የዛሬው የመወያያ አጃንዳ ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ምን እንደሆነ እና የአማራ ብሔርተኝነት እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል…” እያሉ ሲያነቡ፣ በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን ማልጐምጐም ጀመሩ፡፡

በርግጥ አስተዳዳሪው በተለይ አብዛኞቹ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን ወደተቀመጡበት አካባቢ እያፈጠጡና እየተገላመጡ ነበር - ወረቀቱን የሚያነቡት፡፡ በርግጥ ይህ የማወያያ ወረቀት ከፌደራል መንግሥቱ ጀምሮ ደረጃውን ጠብቆ፣ ወረዳ ላይ የደረሰ እንጂ ምክትል አስተዳዳሪው ያዘጋጁት እንደነበረ ይገመታል፡፡ በነገራችን ላይ እኚህ አወያዩ ምክትል አስተዳዳሪ፣ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቱ የ11ኛ ክፍል የማታ ተማሪ ነበሩ፡፡ ተማሪው አስተዳዳሪ ወረቀቱ በታላቅ ስሜት ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፤ ግልምጫቸውም በርትቷል፡፡ መካከል ላይ፣ “አፄ ቴዎድሮስ ለአማራ ብሔርተኝነት የታገለ ጀግናችን ነው…” ሲሉ ጉምጉምታው ወደድንገተኛ ጩኸት ተቀየረ፡፡ አወያዩ ብዙም አልተደናገጡም፤ ይልቅ አይናቸውን እያጉረዘረዙ፣ “ይኼ የነፍጠኝነት፣ የትምክተኝነት ስሜት ነው…አዳምጡ” ብለው ሃይል በተቀላቀለበት ንግግር አስጠነቀቁ፡፡ አዳራሹ በፀጥታ ተዋጠ፤ አወያዩ ጮክ እያሉ ማንበባቸውን ቀጠሉ፤ “በመሳፍንቱ ዘን ቴዎድሮስ ተቀናቃኞቹን በጦር እያንበረከከ የቀጣቸው የተጠናከረ የአማራ ብሔርተኝነት ለመመሥረት ነው…” አይነት ስሜታዊ ንባባቸውን አጠናቀቁና እዚህ ላይ ውሳኔያቸው አሰሙና ቢባል የሚሻል ይመስለኛል) በተነሱት ጉዳዮች ላይ የሞቀ ውይይት እንዲደረግ ጋበዙ፡፡

በመርህ ደረጃ ውይይቱ ጀመረ፡፡ ግን፣ አንድም ተሰብሳቢ ትንፍሽ አላለም፡፡ አዳራሹ እንኳን ከመቶ በላይ ሰው ያለበት፣ ዝንብም ባሉት ንብም ያረፈበት አይመስልም፡፡ ምክትል አስተዳዳሪው ዝምታ ፀረዲሞክራሲነት ነው” በማለት ሂሳቸው እያስፈራሩ፣ ሳይላቸው እየተማፀኑ፣ ተሰብሳቢው አስተያየት እንዲሰጥ ለማድረግ ተፍጨረጨሩ፡፡ አንድም የሚናገር ጠፋ፡፡ የትምህርት ጽ/ቤት የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊዎቹም የቻሉት ማስፈራሪያም፣ መማፀኛም ንግግር ለማድረግ ሞከሩ፡፡ አሁንም አስተያየት ጠፋ፡፡ በድርጅታዊ አሠራር ይመስላል፣ ከተሰብሳቢው መካከል ያሉ የወረዳው ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ እጃቸውን አውጥተው ንግግር ማድረግ ጀመሩ፡፡ ንግግራቸው የተጠና ቃለ ተውኔት ስለሚመስል፣ አስተያየት ሰጪው ቀሽም ተዋናይ እንደሆኑ ታወቀባቸው፡፡ “…ቴዎድሮስ እንደምታውቁት የታወቀ ጀግና ነው…የአማራ ብሔርተኝነትን ለመመሥረት ሲፋለም ጀግንነቱን አለም ነው ያወቀው…” አይነት የሥራ አስፈፃሚው ቃለ ተውኔት፣ ተሰብሳቢውን እንደገና ለጉርምርምታ ዳረገው፡፡ ሰውዬው ተናግረው ቁጭ ሲሉ፣ አዳራሹ እንደገና ወደ ዝምታ ቀፎነቱ ተቀየረ፡፡ ሌላ ሰው አስተያየት አለመስጠቱ ሰብሳቢዎቹን ከሚጠበቀው በላይ እያበሳጫቸው መጣ፡፡

በኋላ፣ ተራ ስድብ ሁሉ ጀመሩ፤ “…አንዳንዶቹ ሙሁራዊ ትምክተኝነት ይወጥረናል…ይኼ ባህሪያችን መተንፈስ አለበት…ምክንያቱም ፀረ - ዲሞክራሲያዊ፣ ፀረ ልማት አስተሳሰብ ስለሆነ ማለት ነው…” የሚሉ ስሜታዊ አስተያየቶችና ማስፈራሪያዎች መነሻቸው ከመድረኩ ሆኖ መድረሻቸው አብዛኞቹ የ”ሀይስኩል” መምህራን የተቀመጡበት አካባቢ እንደሆነ በአዳራሹ ውስጥ ባሉ ሰዎች ሁሉ የታወቀ ይመስላል፡፡ ዝምታ በተንጠላሠበት አዳራሽ ውስጥ፣ ወደ አንድ ስምምነት የመጣ፣ ዝምታዊ መግባቢያ ተፈጥሯል… ከተሰብሳቢው መካከል አንድ እጅ በድንገት ወጣ፡፡ እጅ ያወጣው ሰው የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቱ የታሪክ መምህር ነው፡፡ መድረኩን የሚመሩት የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪው የመምህሩን ስም ጠርተው፣ “ቀጥል አስተያየትን አጠር አርገህ!” ሲሉ አሁንም ተሰብሳቢው በተለይ ተናጋሪው መምህር ባለበት ረድፍ አካባቢ የተቃውሞ ጉምጉምታ ተሰማ፡፡ ተቃውሞው ለሰብሳቢው ስሜታዊ አነጋገርና ድምፀት ነበር፤ ተግሳፁ የራሱ የሆነ ቅኔ ነበረው፡፡ አብዛኛው ተሰብሳቢ የቅኔውን ሰም ይገምታል፡፡

ወርቁን ግን በጣም ጥቂቶች ነበር ቀድመው ሊያውቁት የሚችሉት፡፡ እጅ ያወጣውና አጠር ያለ አስተያየት እንዲሰጥ የተፈቀደለት ወጣቱ የታሪክ መምህር፣ “…እኔ መቼም አፄ ቴዎድሮስ ለአማራ ብሔርተኝነት ተወግተዋል የሚል በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ፀሐፊ የተፃፈ ታሪክ አላነበብኩም፤ አፄ ቴዎድሮስ ከዘመናቸው ቀድመው ያስቡ የነበሩ፣ ለሃገራቸው አንድነት የተፋለሙ ብሎም፣ እየሩሳሌም ድረስ ተሻግረው ለሰው ልጆች ነፃነት ሊዋደቁ ያሉ ባለርዕይ መሆናቸውን ነው የተማርኩት፡፡ እኔም አፄ ቴዎድሮስ ለአማራ ብሔርተኝነት ተዋድቀዋል ብዬ አላስተማርኩም” ሲሉ ከፍተኛ የሆነ ሣቅና ጭብጨባ ተሰማ፡፡ የጭብጨባውም ሆነ የሣቁ መሪዎች ወይም ጀማሪዎች፣ የቅኔው ወርቅ የገባቸው በጣት የሚቆጠሩ የ”ሀይስኩል” መምህራን ነበሩ፡፡ በኋላ እነሱን ተከትሎ አዳራሹ ሁሉ በጭብጨባ ተናጋ፡፡ የቅኔው ወርቅ፣ በአዳራሹ መንሾካሾኪያ ነበር፡፡

ውድ አንባቢያን የቅኔውን ወርቅ እናንተም የገመታችሁት መሰለኝ፡፡ የመወያያ ወረቀቱን ያቀረቡትና የታሪክ መምህሩን ስም ጠርተው “አጠር አርገህ” አስተያየትህን ስጥ ያሉት የወረዳችን ምክትል አስተዳዳሪ፣ የተናጋሪው የታሪክ መምህር የማታ ተማሪ ነበሩ፡፡ “…እኔም አፄ ቴዎድሮስ ለአማራ ብሔርተኝነት ተዋድቀዋል ብዬ አላስተማርኩም” የሚለው የመምህሩ አስተያየት፣ ለአወያዩ “ከወዴት የዘረፍከውን ታሪክ ነው የምታነበንበው!?” አይነት የአንድምታ ፍካሬ ወይም ትርጓሜ ነበረው፡፡ የቅኔ ታሪኩ ወርቅም ይኸው ነው፡፡ አወያዩ አስተዳዳሪ በጣም መናደዳቸው አስታወቀባቸው፡፡ የአዳራሹንም ፀጥታ መቆጣጠር አልቻሉም፡፡ የሰማ ላልሰማ፣ “የታሪክ ተማሪው ለታሪክ መምህሩ ያልተፃፈ ታሪክ እያስተማረ ሳይሆን እየሰበከ” መሆኑ አስተጋባ።

No comments:

Post a Comment