በብሔሮች እኩልነት አምናለሁ፡፡ የአፍ መፍቻ ቋንቋን ማዳበርንም እንዲሁ! በአራቱም የአገሪቱ ማዕዘናት እያንዳንዱ ሰው ባህሉንና ወጉን ማስተዋወቁንም እደግፋለሁ፡፡
ግን………
የገነገነ ብሔርተኝነትና ጎጠኝነት መንገሱ፡ የኔ ብሔር ብቻ - የኔ ቋንቋ ብቻ - የኔ ባህል ብቻ- የኔ------የኔ------ የኔ ብቻ የሚል አስተሳሰብ እየገነነ መምጣቱ ግን ያሳስበኛል፡፡
በምሳሌ “ያሳሰበኝን ” አሳሳቢነት ላስረዳ፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች መላውን አማራና ደቡብ ክልልን ዞሬያለሁ፤ ሰፊውን ኦሮሚያንም ጎብኝቻለሁ፤ አፋርና ትግራይንም የማየት ዕድሉ ነበረኝ፤ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝም ሆነ ሐረር ድሬዳዋን ወዲያ ወዲህ ብየባቸዋለሁ - ዕድሜ ለጋዜጠኝነት!
ታዲያ አብዛኞቹ የደቡብ ብሔሮች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ጉዳይ ተጠምደዋል፤ ኦሮምኛንና ኦሮሞነትን ከፍ ለማድረግ ኦሮሚያ ክልል ስራ በዝቶበታል፤ ዋግኸምራዎች ኽምጣኛን፡ አዊዎች አዊኛን ለልጆቻው ለማውረስ እንደተጉት ሁሉ በትግራይም፡ በጋምቤላም፡ በአፋርና በቤንሻንጉልም ይኸው ነገር ተጠናክሯል፡፡
ታዲያ አብዛኞቹ የደቡብ ብሔሮች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ጉዳይ ተጠምደዋል፤ ኦሮምኛንና ኦሮሞነትን ከፍ ለማድረግ ኦሮሚያ ክልል ስራ በዝቶበታል፤ ዋግኸምራዎች ኽምጣኛን፡ አዊዎች አዊኛን ለልጆቻው ለማውረስ እንደተጉት ሁሉ በትግራይም፡ በጋምቤላም፡ በአፋርና በቤንሻንጉልም ይኸው ነገር ተጠናክሯል፡፡
ዛሬ ዛሬ
አማርኛ የማይናገሩ ኢትዮጵያዊያን ከተሜዎች በርክተዋል፡፡ አፀደ ህፃናትን አልፈው ሃይስኩል የገቡም የትየለሌ ናቸው፡፡ ዛሬ ዛሬ የኔ ብሔርና የኔ ቋንቋ ወይም የኔ ባል ብቻ የሚሊ አጥባቂ ብሔርኞች በየቦታው ሞልተዋል፡፡ ይህ ስር እየሰደደ፤ እየገነነ መሄዱ ያሳስበኛል፡፡
ዛሬ ዛሬ
አማርኛን የአማራ ብቻ አድርጎ ማሰብ የተጋድሎ ያክል መቆጠር ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ክፋቱ ደግሞ የአማራ ክልልም አማርኛን “ የኔ ነው ” ብሎ በማሰብ “እንደሌሎቹ” ለማሳደግ የባለቤትነት ስሜት ያለው አለመምሰሉ ነው፡፡
ህገ መንግስቱ አማርኛን ብሔራዊ ቋንቋ ብሎ ቢገልፀውም መንግስት እንደ ብሔራዊ ቋንቋነቱ ለአገሪቱ ህዝቦች የጋራ መግባቢያ እንዲሆን ወይም ለብሔራዊ መግባባት ሲጠቀምበት አላየንም - ያሰበም አይመስልም ወይም ችላ ብሎታል፡፡
አሁንም እደግመዋለሁ፡፡
በብሔሮች እኩልነት አምናለሁ፤ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ማሳደጋቸውንም እደግፋለሁ!!
ግን ሁሉም የራሱን ብቻ ካጠበቀ ነገሩ እንደሲር ይከርና እንዳይበጣጠስ እሰጋለሁ - እፈራለሁም፡፡ 80ዎቹም ብሔሮች ልጆቻውን በእናት ቋንቋቸው ብቻ የሚናገሩ ፡ እናት ብሔራቸውን ብቻ የሚያፈቅሩ አድርገው ካሳደጉ የነገዋን ኢትዮጵያ ዕጣፋንታ መገመቱ ቀላል ነው፡፡ ይህ ያሳስበኛል - እንደ ባቢሎን ዘመን የምንግባባበት አጥተን እንዳንፈረካከስም እፈራለሁ፡፡
አማርኛን በአማራ ክልል ብቻ ፡ ኦሮሚኛም በኦሮሚያ ብቻ ፡ ትግርኛም በትግራይ ብቻ ፡ ወላይትኛም በወላይታ ብቻ- - - ምናለፋችሁ ቋንቋዎች በየብሔሮቻው ብቻ እየታጠሩ ነው፡፡ በዚህም ብሔራዊ መግባባት እንዳይሳነን እሰጋለሁ - እፈራለሁ - ያሳስበኛልም!!
አማርኛን መናገር እንደነውር የሚቆጥሩ ዜጎች እየበዙ መምጣታቸው ያሳስበኛል፡፡ /እዚህ ላይ ሁሉም አማርኛ መናገር ይቻል የምል ጠባብ አይደለሁም፡፡/ ነገ አንድ የኦሮሞ ሰው ትግራይ ቢሄድ ወይም አንድ የአፋር ሶታ ደቡብ እግር ቢጥለው ወዘተ በምን ሊግባቡ እንደሚችሉ እኔንጃ፡፡ ለዚያም ነው ይህ ያሳስበኛል የምለው፡፡
አማርኛም ሆነ ኦሮምኛ፡ ትግርኛም ይሁን ጉራጊኛ፡ አፋርኛም ይባል ከምባትኛ ወይም ሌላ ብቻ የሚያግባባን የዛሬ ፡ የነገና የወደፊት መግባቢያ ያስፈልገናል፡፡ ለዚያም ነው ቋንቋዎች ይደጉ፤ይበልፅጉ ግን ያግባቡን እንጅ እንዳንግባባ አያድርጉን የምለው!!
ደመቀ ከበደ
No comments:
Post a Comment