Thursday, April 25, 2013

የምርጫ ቅስቀሳ !


ሟች ነፍሱ ሰማይ ቤት እንደደረሰ የሰማይ ቤት ዳኞች ገሃነም ወይም ገነት ለመግባት ሁለቱንም ስፍራዎች ጎብኝቶ መምረጥ እንዳለበት ይነግሩታል፡፡ በመርሐ-ግብሩ መሰረትም በመጀመሪያ ገሃነምን እንዲጎበኝ ይጋበዝና ገና ከበሩ ላይ በመልካም አለባበስ የተሸቆጠቆጠው ሳጥናኤል በሞቀ ሰላምታ ተቀብሎት ወደ ውስጥ ይዞት ይገባል፡፡ ገሃነም ውስጥ የሟች የድሮ ወዳጆች ሁሉ ተሰብስበው እየጠጡ፣ ከረንቦላ እየተጫወቱ፣ በሙዚቃ እየጨፈሩ አስደሳች ጊዜ ሲያሳልፉ ተመለከተ፡፡

ከዚያም ወደ ገነት ተወሰደ፡፡ ገነት እንደገባ አንድም የድሮ ጓደኛውን ሊያገኝ አልቻለም:: ከዚያም በላይ ሲያስበው ያስመረረው ግን በገነት ያሉ ሰዎች ስራቸው ሁሉ ነጫጭ ለብሰው ሸብሸብ፣ መጸለይና መስገድ ብቻ መሆኑ ነው ፡፡ ሟች ሁለቱንም ሁኔታዎች አመዛዝኖ ሲያበቃ ገሃነም ከወዳጆቹ ጋር ለመቀላቀል ወስኖ ፊርማውን አኖረ፡፡

በማግስቱ ወደገሃነም ሲወሰድ ግን የጠበቀው ነገር ሌላ ነበር፡፡ ሳጥናኤል በአስፈሪ ዕርቃኑ ቆሞ እህል-ውሃ የማያሰኝ ጅራፍ ይዞ እየዠለጠ ወደ ውስጥ አስገባው፡፡ ውስጥ የነበሩት ጓደኞቹም ግማሽ ሰውነታቸው በእሳት ተዘፍቆ ሲሰቃዩ ተመለከተ፡፡ ወዳንድ ጓደኛው ጠጋ አለና ‹‹ትላንትና ያየሁት ሕይወት የት ሄደ?›› ብሎ ቢጠይቀው፡፡ ‹‹አይ እሱማ የምርጫ ቅስቀሳ ነው›› ብሎት እርፍ አለ፡፡
ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment