ስለምርጫው ተጠይቀው ኢንጂነር ኃይሉ እንዲህ አሉ “ይሄ ምርጫ ሳይሆን ንጥቂያ ነው!” እንዴት ቢማረሩ ነው ባካችሁ! ከምርጫው ራሱን ያገለለው የ33ቱ ፓርቲዎች ቡድን (ስም አልወጣለትም አይደል?) ምን ነበር ያለው? “ኢህአዴግን ለማጀብ ወደምርጫው አንገባም!” ብለው ነበር (ምን ያድርጉ? ምህዳር የለማ!) ባለፈው ሳምንት ከምርጫው በኋላ የምርጫ ቦርድ ሃላፊው ምን አሉ መሰላችሁ? (እኚህ እንኳን ፓርቲዎችን ሁሉ እንደልጆቼ ነው የማየው ያሉት) “እንዳሁኑ ምርጫ ፓርቲዎች ሳይወዛገቡ በሰላም የተጠናቀቀበት ጊዜ የለም” ይሄን የሰማ የቀድሞ የኢህአዴግ ደጋፊ ወዳጄ (አሁን ሃይማኖተኛ ሆኗል) “እውነታቸውን እኮ ነው … በምርጫው አልተሳተፉማ!” ብሎ እርፍ አለ! (ሰው ሁሉ በቀጥታ መናገር ተወ ማለት ነው?) እኔ ደግሞ ያስገረመኝ የአንዳንድ መራጮችና ተመራጮች አስተያየት ነው፡፡
ባለፈው እሁድ አንዱ መራጭ ድምጽ ሰጥቶ ሲወጣ የኢቴቪ ጋዜጠኛ ያገኘውና “ምርጫው እንዴት ነበር?” ይለዋል፡፡ (ኢንተርቪው በጥቆማ ነው የሚባለው ውሸት ነው አይደል?) መራጩም - “የመብራት ችግር አለ፣ የውሃ ችግር አለ፣ የመሰረተ ልማት ችግር አለ፣ በአጠቃላይ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች የሚፈታልኝን መርጫለሁ” (ማንን ይሆን?) ኢቴቪ ያነጋገራቸውን አስተያየት ሰጪዎች እንደኔ በቅጡ ሰምታችኋቸው እንደሆነ አላውቅም፡፡ “የመረጥኩት ኢህአዴግን ነው” ማለት እኮ ነው የሚቀራቸው፡፡ (ነግረውን ቢለይላቸው ይሻል ነበር!) ሌላ መራጭ ደግሞ እንዲህ አለ - በፈረደበት አንድ ለእናቱ ኢቴቪያችን፡፡ “ምርጫው ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሁም ልማታዊ ነው ማለት ይቻላል” አይገርምም… ልማታዊ ምርጫ! ኢህአዴግ ራሱ እኮ ሌላ ሌላውን እንጂ ምርጫውን ልማታዊ ሲል ሰምቼው አላውቅም (አሁን ይጀምር ይሆናል!) አንዱ ጐልማሳ መራጭ ደግሞ አስተያየታቸውን የጀመሩት የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስን በማወደስ ነው፡፡ “የባለራዕዩን መሪ አርአያ ተከትለን…” አሉና እሳቸውም “ይሆነኛል…ይጠቅመኛል” ያሉትን መምረጣቸውን ነገሩን፡፡
አንደኛዋ ወይዘሮ ደግሞ ምን ብትል ጥሩ ነው? “ጫንቃችንን ያቃለለልንን ፓርቲ መርጫለሁ” (ኢህአዴግ ብላ ብትገላገልስ?) ከሁሉም ግን የኢራፓ ሊቀመንበር የሰጡትን አስተያየት የሚያህል የለም (ዊርድ እኮ ነው!) “ዝናብ የለም፤ ደመና ነው፤ ሙቀት የለም…ሁሉ ነገር ኖርማል ነው” (ስለምርጫ እንጂ ስለሜትሮሎጂ ማን ጠየቃቸው?) የሆኖ ሆኖ እስካሁን “የምርጫው ሂደት ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ልማታዊ ነው” ተብሏል፡፡ ግን እኮ ድሮም ቢሆን በጥባጩ ህዝብ ሳይሆን ፓርቲዎቹ ናቸው - ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎቹ! የብጥብጣቸውን ሰበብም አሳምረን እናውቀዋለን - የፈረደበት ሥልጣን ነው!! አሁን ግን የምርጫው ውጤት ቀድሞ የሚታወቅ ስለሆነ (መጨረሻው እንደሚታወቅ ፊልም) ፓርቲዎቹ አልተወዛገቡም (የተሳተፉት ማለቴ ነው!) ለነገሩ ብዙዎቹ ገና የኢህአዴግን ሚሊዮን እጩዎች ሲሰሙ እኮ ነው እጅ የሰጡት (የቤት ሥራቸውን አልሰሩማ!) እነዚህ የጦቢያ ተቃዋሚዎች ግን ሁነኛ መካሪ ሳያስፈልጋቸው አይቀርም (ቢቻል በዲሞክራሲ የዳበረ ልምድ ካላቸው አገራት!) እንዴ…”በምርጫ አንሳተፍም!”፣ “ፓርላማ አንገባም!”፣ “አንደራደርም” ምናምን እየተባለ እስከመቼ ይዘለቃል? እኔ የምጠረጥረው ምን መሰላችሁ? ወይ የፖለቲካ ጨዋታውን አላወቁበትም ወይ ደግሞ ኢህአዴግ አንድ ነገር አስነክቷቸዋል።
ከሰብኣዊ
No comments:
Post a Comment