Monday, April 15, 2013

ተበድለን ይቅርታ አንጠይቅም!


Author, writer from norway
አብዶ ኑር የሱፍ (ኖርዌ)
ፍትህ  እና የሰብዐዊ መብት ጉዳይ ህዝቡ እርሙን ባያወጣም  ከተቀበሩ ከ 21 አመታት በላይ ሆኗቸዋል።  ይህ ያለው መንግስት እነዚህ ለህዝብ የሚስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን በመቅበር ህዝቡ እንዳይተነፍስ በማድረግ  አፍኖ መግዛቱን በማን አለብኝነት ተያይዞታል ። በሃገራችን  ስለ መብት  መጠየቅ ወንጀል ሆኗል ። ስለ መብት ደፍረው በሚጠይቁት  ላይ የአሸባሪነት ታርጋ ይለጠፋል ፤ወደ ወህኒ ይወረወራሉ ፤ ከህግ ውጭ ኢ-ሰብዐዊ ግፎች ይፈጽምባቸዋል ፤ ከዛም  አድርባይ ምሁር ነን ባዮችን  በመጠቀም ተበዳዮች ይቅርታ ጠይቀው እንዲወጡ ይደረጋል  ።ይህ የተለመደ ሰላማዊ ታጋዮችን ከጨዋታ ውጭ ማድረጊያ መንገድ ነው ።

ልብ በሉ ይህ መንግስት የሽምግልና ባህላችንን ጭምር እንኳን ሳይቀር እያዋረደ ያለ ተግባር በመፈጸም ላይ ይገኛል ። ስለ ሽምግልና ካወራን ሽምግልና ማለት  በሁለቱንም ወገን  ግራ እና ቀኝ አይቶ  ጥፋተኛው ጥፋቱን አምኖ ፤ ለተበደለው ወገን  የበደሉን ካሳ ወይም የበደሉን ይቅርታ የሚቸርበት የተከበረ የሃገራችን ማህበራዊ እሴት ነበር ። ነገር ግን በዚህ ጊዜ እየተደረገ ያለው የሽምግልና ሂደት ከባህላችን ወጣ ያለ ፤ግራ እና ቀኙን ያላመዛዘነ ፤ የመብት ጠያቂዎች  የደረሰባቸውን የሰብዐዊ መብት ረገጣ ከግምት ዉስጥ  ያላስገባ ነው ።እነዚህ ሽማግሌዎች የተበደሉ ታሳሪዎችን እራሳቸውን ጥፋተኛ  አድርገው ይቅርታ እንዲጠይቁ በማግባባት ተግባር ላይ በመሰማራታቸው የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርጋቸውን ተግባር እየፈጸሙ ይገኛሉ ።
በነገራችን ላይ በዚህ የሽምግልና አካሄድ ይቅርታ መጠየቅ በራሱ በምናነሳቸው የመብት ጥያቄዎች ላይ እራሱን የቻለ ጉዳት አለው ። እንደ ባህላችን ያጠፋ አካል ካለ ይቅርታ መጠየቅ ትልቅነት ነው ። ነገር ግን ሽማግሌ በሚባሉት ግለሰቦች አማካኝነት ባልሰራኸው ስራ  ይቅርታ ጠይቀህ ከእስር ቤት ስትወጣ ከመታሰርህ በፊት ስትታገልለት የነበረውን የመብት ጥያቄ ደግመህ መጠየቅ እንዳትችል መደረጉን እርግጠኛ መሆን አለብህ ። ምን ይህ ብቻ ያለ ጥፋትህ ይቅርታ መጠየቅ ማለት ድምጽህን ማፈን ለሚፈልገው መንግስት የልብ ልብ መስጠት  እና የሚያስፈራራ ድምጽ ያለው ቃጭል በአንገትህ ላይ ታስሮልህ እንደመንቀሳቀስ ያህል ይቆጠራል ።በዚህም አስፈሪ ድምጽ ምክንያት ደንብረህ  የምታምንበትን የመብት ጥያቄ ከግብ ሳታደርስ እግሬ አውጭኝ ብለህ እንድትፈረጥጥ ወይም ዝምታን እንድትመርጥ ትገደዳለህ ።
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ምክንያት የሆነኝ በሃገራችን የሰላማዊ ትግል ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጅ የሆነውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ለማጠልሸት ብሎም ህዝበ ሙስሊሙ እየተከተለው ያለውን የተቀናጀ ሰላማዊ ትግል ለማስቆም ይህ ተንኮለኛ መንግስት  ራሱን  የሙስሊም ምሁራን በማለት የሚጠራን አንድ ቡድን በመጠቀም የዘረጋው አዲስ ነገር የሚመስል ግን የተነቃበት አካሄድ  ነው ።
መንግስት ይህንን ከአመት በላይ በጽናት በመላ ሃገሪቱ እየተካሄደ ያለውን  ፍጹም ሰላማዊ ትግል ለማጠልሸት እና ለማዳፈን ያልተጠቀመው ነገር የለም ። የሐሰት ዶክመንተሪ ፊልም ማዘጋጀት ፣ሙስሊሙን ከክርስቲያን ወገኑ ጋር ለማጋጨት መሞከር ፣ ኮሚቴዎቹን ለመከፋፈል መሞከር ፣ ሰላማዊ የመብት ጠያቂዎችን ማሰር ፣ ማሰቃየት ብሎም መግደል ፣የሐሰት ምስክሮችን በማሰልጠን  የይስሙላ ፍርድ ቤቱን በመጠቀም የሐሰት ፍርድ መፍረድ ፣  ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ማባረር ፣ ሰራተኞችን ከስራ ገበታ ማባረር ፣ ቤት ለቤት  የጥቁር ሽብር ፍተሻ ማካሄድ እና የመሳሰሉትን ኢ-ሰብዐዊ ድርጊቶችን መፈጸም እና ሌሎችም ይገኙበታል ። ነገር ግን  ህዝበ ሙስሊሙ የገባው ቃል ኪዳን ስላለ ከሰላማዊ ትግሉ ሊገታው አልቻለም ። ወደፊትም አይችልም ።
ይህ ያልተሳካለት የበግ ለምድ የለበሰ ተኩላ ከድሮ ልምዱ በመነሳት የራሱን አድርባይ ተቃዋሚዎች በማዘጋጀት እና የድምጻችን ይሰማ አመራሮችን በመገልበጠ ትግሉን ለማዳከም  በመጣር ላይ ይገኛል።  ይህ አካሄድ በሃገራችን የፖለቲካ ሁኔታ የልደቱን  ወይም የአየለ ጫሚሶን አይነት የተቃዋሚ  ደጋፊ ማዘጋጀት ማለት ነው ። በሌላ በኩል ደግሞ ራሳቸውን የሙስሊም ምሁራን ብለው የሰየሙት በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ሞዴል የተዘጋጁ ለመንግስት የሚያገለግሉ የሽማግሌ ቡድን በማዘጋጀት በእስር የሚገኙትን ኮሚቴዎቻችንን ይቅርታ ጠይቀው ከእስር እንዲፈቱ  ፣ ጥያቄያችን ሳይመለስ  እና እየተደረገ ያለው የሰላማዊ ትግል ያለ ዉጤት መና እንዲቀር የሚያደርጉ ናቸው ።
ኧረ ለመሆኑ ይቅርታ መጠየቅ ያለበት በዳይ ወይስ ተበዳይ ?  ልብ በሉ መንግስትን የሚያስጠይቁት መጠነ ሰፊ ወንጀሎች አሉ ፤ ከነዚህም ዉስጥ ህዝብ የወከላቸውን የመፍትሄ  አፈላላጊ ኮሚቴዎችን  በማን አለብኝነት በማሰሩ እና ኢ-ሰብዐዊ ግፍ መፈጸሙ ፣ ሰላማዊ ታጋይ ህዝብን በማሸበሩ ፣ በማሰሩ ብሎም በአሳሳ ፣ በገርባ ፣ በሐረር ፣ በሻሸመኔ ፣ በናዝሬት ፣ በአዲስ አበባ ፣ በደሴ እና በሌሎች የሃገራችን ክፍሎች የፈጸማቸው ግድያ እና ኢ-ሰብዐዊ ወንጀሎች ፣ በሃገራችን የፍትህ ሂደት ላይ ለሰራው ወንጀል ፣ በኢቲቪ አማካኝነት ላሰራጨው የሃሰት ድራማ ፣  ላካሄደው የቤት ለቤት የጥቁር ሽብር ፍተሻ ፣ ሙስሊሙን ከክርስቲያን ወገኖቻችን ጋር ለማጨት  ለሞከረበት እና ሌሎች ተያያዥነት ላላቸው ወንጀሎች ይቅርታ መጠየቅ ያለበት በመንግስት ስም የተቀመጠው  ሃይል ነው ።
ህዝበ ሙስሊሙም ሆነ በግፍ የታሰሩት የመፍተሄ አፈላላጊ ተወካዮቻችን ተበዳይ ሆነን ሳለ ይቅርታ አንጠይቅም ። ይልቅ ጥያቄያችን እስኪመለስ ብሎም  ግፍ የሰራብን ሃይል ይቅርታ እስኪጠይቀን እና ለፍርድ እስኪቀርብ ድረስ የድምጻችን ይሰማ አሚሮቻችን በሚሰጡን ተልዕኮ አማካኝነት ድምጻችንን ከማሰማት ወደ ኃላ እንደማንል ሊረዱት ይገባል ።
ራሳችሁን የሙስሊም ምሁራን በማለት ሰይማችሁ በሽማግልና ስም በመግባት የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ ሳይመለስ ትግሉን ለማጠልሸት ከመሞከራችሁ በፊት  ህዝበ ሙስሊሙ በየአደባባዩ ሰላማዊ ጥያቄ በጠየቀ በጥይት ሲገደል ፣ ሲገረፍ ፣ በግፍ ወደ ማጎሪያ ሲወረወር ፣ የተከበሩ እና የምንወዳቸው ኡስታዞቻችንን  በአደባባይ ሲቀለድባቸው ለምን አላወገዛችሁም ? ለምን የህዝበ ሙስሊም ጥያቄ ይመለስ አላላችሁም ? ይህ ተግባራችሁ ለወደፊቱ ተጠያቂ እንደሚያደርጋችሁ አውቃችሁ ከዚህ እኩይ ተግባር እንድትታቀቡ እንጠይቃለን ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
ለአስተያዬትዎ = abnuye2001@gmail.com

No comments:

Post a Comment