Wednesday, April 17, 2013

የእስራኤል ኤምባሲ ኢትዮጵያዊያ ጋዜጠኞችን በሽብር ጠርጥሮ ልዩ ፍተሻ አደረገ


በፋኑኤል ክንፉ
 በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ፤ የእስራኤልን 65 የነፃነት ቀን በዓልን ለማክበር በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ሚያዝያ 7 ቀን 2005 .. በጠራው የእራት ግብዣ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞችን በሽብርተኝነት በመጠርጠር ልዩ ፍተሻ አካሄደ።
ሰኞ ዕለት ከምሽቱ አንድ ሰዓት በእስራኤል ኤምባሲ ጋባዥነት በተጠራው የራት ግብዣ ላይ ለመገኘት በርካታ ታዳሚዎች የሒልተን ሆቴል የፍተሻ መሣሪያን ለማለፍ በረድፍ ተሰልፈዋል። ተራ በተራ ፍተሻውን ያለፉ ተጋባዥ እንግዶች ወደ አዳራሹ መግባት ጀምረዋል። ከእነዚህ መካከል የሪፖርተር፣ የሰንደቅ፣ የሰብሰሃራ እና የኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጠኞች ይገኛሉ።

እራት ወደ ተዘጋጀበት አዳራሽ ለመግባት ተሰልፈው የነበሩ ጋዜጠኞች ከእንግዶች መካከል ተወስደው ወደ አንድ የአዳራሹ ጥግ እንዲቆዩ ተደረገ። ለምን ይህን ማድረግ እንደፈለጉ መገመትም አልተቻለም። ቆይታችን ረዘም በማለቱ አንዱን የሴኩሪቲ ሰራተኛ ጠራነው።ለምንድ ነው እዚህ ጋር የቆምነው ስንል ጠየቅነውግራ በመጋባት አተያየት ከተመለከተን በኋላጠብቁኝ መጣሁ አለአማራጭ አልነበረንም ጠበቅነው።
ከትንሽ ደቂቃ በኋላ አንድ ረጅም የሴኩሪቲ ሰራተኛ አንድ ወፈር ያለ መመርመሪያ ይዞ አጠገባችን ደረሰ።የለባሳችሁትን ኮት አውልቁ። በሱሪ ኪሳችሁ የሚገኘውን ማኛውንም ነገር ሶፋው ላይ አኑሩየሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጠን። አደረግን። የአዳራሹን ግርግዳ አስጠግቶ በያዘው ማሽን ሙሉ ሰውነታችን እየተዟዟረ ፈተሸን። ምን እያደረጉ እንደሆነ አልገባንም። ሌሎች እንግዶች በሒልተን በር ላይ ካደረጉት ፍተሻ ውጪ ሲፈተሹም ሲበረበሩም አላየንም። የበለጠ በውስጣችን ጥያቄ ያጭሩብን ይህ ሁኔታ ነበር።
ልብሳችን ለበስን። በሶፋ ላይ ያስቀመጥነውን ዕቃዎቻችን ወደ ቦታቸው አኖርናቸው። ወደ አዳራሹ ለመግባት ተንደረደርን፤ ድንገት አንዴ ቁም ተባልን። በርቀት የቆመ የሴኩሪቲ ሠራተኛበእጃቸው ላይ ለጥፍባቸውየሚል ትዕዛዝ ሰጠ። በሁላችንም እጆች ላይ ከሌላው በተለየ ቀጠን ያለ ወረቀት ቢጤ ለጠፍብን። በአይን ምልክት ሰጥተውን መግባት እንደምንችል ነገሩን። የእስራኤል የነፃነት ቀን ወደ ሚከበርበት አዳራሽ ውስጥ ዘለቅን። በውስጣችን ግን የተለየ ፍተሻ በእኛ ላይ መደረጉ ጥያቄ እንደሆነብን ነው ወደ አዳራሹ የገባነው።
አዳራሹ መግቢያ በር ላይ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር እና የኤምባሲው ከፍተኛ ኃላፊዎች እንኳን ደህና መጣችሁ እያሉ እንግዶችን ይቀበላሉ። እኛ ማንን እንኳን እንደጨበጥን እርግጠኛ ሳንሆን ነው የዘለቅነው።  ለኮክቴል ከተዘጋጁት የቁም ጠረጴዛዎች መካከል አንዱ ላይ ክንዳችን አሳረፍን። ነፃነታችን የነጠቀውን የነፃነት ቢራ አንድ ሁለት ማለት ጀመርን። ጨዋታው ደራ ለምን በተለየ መልክ ፈተሹን የሚለው የእንቆቅልሽ ጥያቄ እንደቀጠለ ነው።
በድንገት የተቀላቀለን አንድ እኛን የሚመስል ግለስብየምትፈተሹት ለራሳችሁ ደህንነት ነው። መናደድ የለባችሁም አለፈርጠም ብሎ። መጀመሪያ ብንተዋወቅ አይሻልም። እኔእንትና እባላለሁየጋዜጣ አዘጋጅ ነኝ። አንተ የትነው የምትሰራውለጊዜው አያስፈልጋችሁም። ተጋባዥ ነኝመልስ ለመስጠት ያህል ነው አለ። አንተ ለምን እንደኛ አልተፈተሸክም ስንል ጠየቅነው። ፈጠን ብሎማወቅ ያለባችሁ የግብዣ ጥሪ ወረቀቱን የተላከላችሁ ከሳምንት በፊት ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ አሸባሪዎች መጠቀሚያ ሊያደርጓቹህ ስለሚችሉ ፍተሻ መደረጉ ተገቢ ነውሲል ሚስጢሩን አረዳን። አንተ በአሸባሪዎች የማትመለመለው ምን ስልሆንክ ነው? የእኛ የፖለቲካ ባሕል በየስብሰባው እንደተቀጣጣይ ፈንጂ እየገባን የሚያስፈነዳን ነገር የለውም። ከምን መነሻ እኛን በዚህ ተግባር ሊመለመሉ ይችላሉ ብላችሁ አሰባችሁ ስንል ጥያቄ አቀረብንለት።እኔ ቢያንስ ከአስራ አምስት ዓመት በላይ እስራኤል ኖሬያለሁ። ስለዚህ በዚህ ተግባር አልሰማራምሲል ስለራሱ ሊያስረዳን ሞከረ። ልብ በሉ ቤተ-እስራኤላዊ መሆኑን እየነገረን ነበር። እሻDህን በእሻDI መሆኑ ነው።
በጣም በመበሳጨትለምን እኛ ብቻ ተመርጠን እጃችን ላይ ይህን መለጠፍ ፈለጋችሁ? በዚህ ደረጃ የምትጠረጥሩን ከሆነስ ለምን ጋበዛችሁን? ይህን ሁሉ የመብት ጥሰት የምትፈጽሙት በእኛው ሀገር ላይ ሆናችሁ መሆኑን አታውቅም? የእኛ ሀገር የፖለቲካ ባሕል እንደመካከለኛው ምስራቅ በማፈንዳትና በመፈንዳት ላይ የተንጠለጠለ መስሏችሁ ይሆን? እኛን ለሽብር ተግባር ልትመለመሉ ትችላላችሁ የምትለው ተመሳሳይ የአዕምሮ ስሪት ያለን መስሎ ይሆን? እና ሌሎችም ጥያቄዎች በጠረጴዛው ላይ መፍሰስ ጀመሩ። ሃይለቃልም መሰነዛዘር ተጀመረ። ነገሮች በጥሩ ሁኔታ አለመሆናቸውን ስንመለከት ከአዳራሹ ለቀን ወጣን።
የተደረገብን ግልፅ የመብት ጥስት ቢሆንም ለእስራኤሎች አድናቆታችን መንፈግ አልቻልንም። ከተጠሩት ተጋባዥ እንግዶች መካከል አብዛኛው ቤተ-እስራኤሎች ናቸው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ለእስራኤል ብሔራዊ ጥቅም ያሳዩት ተቆርቋሪነት አስቀናኝ። ግን ስንቶቻችን ነን ቤተ-እሰራኤሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን ሚና ጠንቅቀን የምንረዳው? የኢትዮጵያ ጥቅሞች እና የእስራኤል ጥቅሞችን ለይተን ከእነሱ ጋር ውይይት የምናደርገው? በስመ ሀገር ሰው የሚነገረውና የማይነገረውን ለይተን እናውቅ ይሆን? የሀገራችን የፀጥታ ሃይሎችስ በሁለታችን መካከል ያለውን የልዩነት ድንበር ይገነዘቡት ይሆን? ለማንኛውም ልዩነታችንን ጠንቅቆ መረዳት ቢያንስ በሽብር ሲጠረጥሩን ከመደናገጥ ያድነናል።

No comments:

Post a Comment