Saturday, April 13, 2013

ምናባዊ ቃለ ምልልስ ከመለስ ዜናዊ’ጋ


በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ የሚቀለዱ ቀልዶች የሚያበሳጫቸው ሰዎች እንዲያነቡት አይመከርም! ካነበቡም ኃላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡
----------------------------------------
ከኑሮ ውድነቱ ውድድሩ ከብዶኛል፡፡ ስለሆነም አንድ ቀን መሞቴ ላይቀር ለምን ብዙ ቀን እቸገራለሁ የሚል ክፉ ሐሳብ ውልብ አለብኝ፡፡ ከዚያም እግዜር እስኪጠራኝ ለመጠበቅ ትግስቱ ስላልነበረኝ ራሴ ወደእርሱ ለመሄድ አሰብኩ፡፡ በአጭሩ ራሴን ለማጥፋት ወሰንኩ ማለቴ ነው፡፡ ከዚያም ቁጭ ራሴን ካጠፋሁ በኋላ ስለሚኖረኝ ሕይወት ሳስብ እንደማልፀድቅ ታወሰኝ፤ ራሱን ያጠፋ ሰው አይፀድቅም፡፡ በቃ ገሃነም መግባቴ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ ከዚያም ገሃነም ከገባሁ በኋላ ብቻዬን ነው የምሆነው ወይስ አብሬው የምደበረው ቀድሞ የማውቀውሰ ሰው አገኝ ይሆን ብዬ ሳስብ፣ ያው መቼም ፖለቲከኛ አይፀድቅምና መለስ ዜናዊን እንደማገኝ ታሰበኝ፡፡ እናም ስንገናኝ ቃለመጠይቅ ላደርግላቸው ወሰንኩ፡፡ ሆኖም ቃለ ምልልሱን ተመልሼ ለናንተ ወዳጆቼ እንዳላስነብባችሁ ሰማይ ቤት ፌስቡክ የለም፡፡ ስለዚህ ቃለምልልሱን በምናቤ አዘጋጅቼ እንደሚከተለው ላስነብባችሁ ወሰንኩ፡-

እኔ፡- ጤና ይስጥልኝ?
መለስ [እያነበቡት ካሉት መጽሐፍ ላይ እንዳቀረቀሩ ላፍታ በግምባራቸው አዩኝና ምንም ሳይሉ ወደንባባቸው ተመለሱ፡፡ የሚያነቡት መጽሐፍ ሰረቅ አድርጌ ሳየውገሃነማዊ ዴሞክራሲይላል፡፡]
እኔ፡- አወቁኝ፣ 
መለስ፡- [በንዴት መጽሐፋቸውን አጥፈው] ማንነህ አንተ?
እኔ፡- በፍቃዱ ኃይሉ ነኝ፤…. ጦማሪው፣አሁንስ አወቁኝ?
መለስ፡- እንኳን ጦማሪ ቆማሪም ብትሆን አላውቅህም፣ የማወቅም ግዴታ የለብኝም፡፡ የመጣህበት ጉዳይ ለቃለ መጠይቅ እስከሆነ ድረስ ግን ጥያቄዎችህን እመልስልሃለሁ 
እኔ፡- ለመንደርደሪያ ያክል እስኪ ስለሚያነቡት መጽሐፍ ምንነት ጥቂት ይንገሩኝ?
መለስ፡- ነሐሴ ወር ላይ (አንዳንዶች ሐምሌ ነው ይላሉ፤) ገሃነም እንደገባሁ በአስተዳደሩ አካላት የአፈፃፀም ችግር በመኖሩ፣ በርካታ በደሎች በሃጥኣን ላይ ሲፈፀም እንደነበር በማስተዋል፣ የገሃነምን አስተዳደር በስር ነቀል ለውጥ ትራንስፎርም ለማድረግ የነደፍኩት አስተዳደራዊ ሥርዓትን የሚያሳይ መጽሐፍ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ገሃነም ውስጥ አንድ ሰው የሚቃጠልበትን እሳት ነዳጅ ሒሳብ እንዲከፍል ይገደድ ነበር፣ አሁን ግን ሁሉም ሰው በነጻ የሚቃጠልበትን መንገድ አመቻችተናል፡፡ በመሆኑም በፊት በጉልበት ይቃጠሉ የነበሩ ሰዎች፣ ዛሬ በገዛ ፈቃዳቸው፣ በመከባበር መቀጣጠል ጀምረዋል፡፡ ቢሆንም ግን ገሃነም ገና ብዙ ሕዳሴ ያስፈልገዋል፣ ሕዳሴ የሚመጣው ደግሞ በገሃነማዊ የዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለማችን ብቻ ነው፤ አራት ነጥብ፡፡ 
እኔ፡- ለዚህ ሥርዓት ግንባታ ከበለፀጉት የገነት ነዋሪዎች ልምድ ለመቅሰም፣ ወይም ድጋፍ ለማግኘት የሞከሩት ነገር አለ?
መለስ፡- እኛ የውስጣዊ አሠራራችን ላይ ጣልቃ ለሚገቡ ማንኛውም አካላት በራችንን አንከፍትም፡፡ የገነት ነዋሪዎች እጃችንን በመጠምዘዝ ለእነርሱ እንድናጎበድድ ይፈልጋሉ፡፡ እኛ ግን መቼም አናደርገውም፤ እኛ ገሃነማውያን ከራሳችን የተሻለ ማንም አያውቀንም፡፡ 
እኔ፡- እስኪ አንዳፍታ ከሞት በፊት ስለነበረው ሕይወታችን እናውራ፡፡ አገራችንን መምራት ምን ይመስላል?
መለስ፡ - የምን አገር?
እኔ፡- የኢትዮጵያ መሪ ነበሩ፣ መቼም አይዘነጋዎትም?
መለስ፡- ብዙዎቻችሁ የእውነተኛ መሪ አድርጋችሁኝ እንደነበር ይሰማኛል፡፡ እኔ እናንተ ስለምታስቡት ነገር ደንታ የለኝም፣ ሐሳባችሁን ይዛችሁ በሊማሊሞ ማቋረጥ ትችላላችሁ፡፡ እኔ በምድር እያለሁ፣ በጠቀስከው ጄኦፖለቲካዊ ክልል ውስጥ ሥልጣን መቆናጠጥ የምችልባቸውን እንደብሔር፣ ሃይማኖት እና ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶችን እያነሳሁ ኃይል ሁሉ ወደኔ እንዲፈስ ለማድረግ፣ ብሎም የግል የበላይነት ሕልሜን ለማሳካት እንጂ እንደሌላው የዓለም መሪ መምራት የሚባለው ነገርበውኔም በሕልሜም አልነበረም፣ እንዲኖርም የሚያስገድደኝ አልነበረም፣ አይኖርምም፡፡
እኔ፡- ይቅርታ አድርጉልኝ አቶ መለስ፣ ግን እኮ አሁን የእርስዎ ራዕይ ምናምን እየተባለ እየተቀወጠ ነው?
መለስ፡- እሱማ የታወቀ ነው፤ ተረኞች በራሳቸው መንገድ ኃይልን እንደሚቆናጠጡ ይታወቃል፡፡ የኔ ራዕይ የሚባለውን ነገር ለሕዝቡ ሰጥተውት፣ ሕዝቡ የመለስ ራዕይ እያለ ሲያወራ እነርሱ በጓዳ ሥልጣናቸው ጉዳይ ላይ ዕጣ ይጣጣላሉ፡፡ አሠራራችንን በፊትም ቢሆን እንዲህ እንደነበር ማወቅ እና መረዳት ያስፈልጋል፡፡ 
እኔ፡- ወይ ጉድ አቶ መለስ፡- እሺ በቅርቡ ደግሞ / አዜብ ደሞዝዎ 4,000 ብር ብቻ እንደነበር ተናግረዋል፤ እውነት ነው እንዴ?
መለስ፡- አራት ሺሕ መሆኑን አላውቅም፤ 1983 ወዲህም ሆነ ወዲያ ደሞዝ ተቀብዬ አላውቅም፡፡
እኔ፡- እንዴ አቶ መለስ፣ እንዴት?
መለስ፡- እንደሚታወቀው ደሞዝ በኔ ቤት ዋጋ አልነበረውም፡፡ በተጨማሪም አዜብ ነች እንጂ እኔ ለገንዘብ ደንታም እንዳልነበረኝ፣ ፓርቲዬ የሰጠኝን ብቻ የምሠራ ሰው እንደነበርኩ በተደጋጋሚ ተናግሬያለሁ፡፡ እኔ ሁሉም ሰው እስከታዘዘልኝ ድረስ.. በቃ ምንም አልፈልግም ነበር፡፡ በዚያ ላይ ገንዘቡን ቢሰጡኝም የማጠፋበት አጋጣሚ አልነበረኝም፡፡ የጦርሜዳም ሆነ የቤተመንግሥት ኑሮ እየተንቀሳቀሱ ገንዘብ ለማጥፋት አይመችም፣ ሁሉም በሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡ መቼም ይሄንን የማያውቅ አይኖርም፡፡ 
እኔ፡- [አላውቅም ማለትን እንደውርደት ስለቆጠርኩት ጭንቅላቴን እንደገባው ሰው ወዘወዝኩ] ወደሌላ ጥያቄ እንለፍ እና አንዳንዶች አሁንም ድረስ አቶ መለስ የሞቱት ደንግጠው ነው የሚል እምነት አላቸው፤ እውነት ነው?
መለስ፡- እስካሁን ድረስበመላው ዓለማችን ደንግጦ የሞተ መሪ የለም፤ በኢትዮጵያም ቢሆን ደንግጦ የሞተ መሪ አልነበረምስለዚህ የኔ ደንግጦ መሞት አለመሞት ለተመሳሳይ አጋጣሚ ተጨማሪ ግብኣት ይሆናል ብዬ ስለማላምንበተጨማሪም በገሃነማዊ ዴሞክራሲ መርሖች ላይ ሰዎች በምን ምክንያት እንደሞቱ መናገር የለባቸውም የሚል ስምምነት ስለአለንይህ እውነት አፈንግጦ ቢወጣ ኒዮ ሊበራሎች
እኔ፡ - [አቋረጥኳቸው] እሺ በቃ አሁንም ወደሌላ ጥያቄ እንለፍ፤ ከኢትዮጵያ እና ከገሃነም የትኛው ለአገዛዝ ይቀላል?
መለስ፡- እንደሚታወቀው እዚያም ሆነ እዚህ አብዛኛው ሰው ለመገዛት ዝግጁ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ቆመህ ሞተህም የሚገዛልህ አታጣም፤ እዚህም ያው ነው፡፡ ልዩነቱ እዚህ ተፎካካሪ አለብኝ፡፡
እኔ፡ - ማነው ተፎካካሪዎ?

መለስ፡- ሳጥናኤል!

No comments:

Post a Comment