Friday, April 26, 2013

ታሪካችንና ተረታችን ድንበሩ የቱጋ ነው?


ታሪክ የሰው ልጅ በዘመናት በትውልዶች ያለፋባቸውን አሻራዎች የሚያሳይ መስታውት ነው። ታሪክ የትውልዶችን ባህሎች፣ አኗኗሮች፣ ሐይማኖታዊ እሴቶች፣ ፍልስፍናዎች፣ የአገዛ ስርዓቶች፣ ትውፊቶችና የህዝቦች መስተጋብሮች ብሎም አጠቃላይ የቅብብሎሽ ሂደቶችን የሚያሳይ የእውቀት ዘርፍ (Discipline) ነው። የሰው ልጅ እስካለ ድረስ ታሪክ አለ። ሰው ከታሪክ የወለዳል ታሪክም ከሰው ይወለዳል። ሰውና ታሪክ ይሄን ያህል እርስ በእርሳቸው የተቆራኙ ናቸው። በመሆኑም ታሪክ የምንቀበለውና የምናቀበለው ነው። ታሪክ በትውልድ ሰንሰለታዊ ቅብብሎሽ እየሰፋና እየዳበረ ይሄዳለ። የዛሬ ክንውን የነገ ታሪክ ነው። ሆኖም ታሪክ የድርጊቱ ክንውን በጊዜ ሂደት እየራቀ በሄደ ቁጥር በፅሁፍ ከትቦ ለራስ ትምህርትን ለመውሰድም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የበዛ ጥንቃቄንና ጥረትን ይጠይቃል። 

ይህም በመሆኑ የታሪክ ፀሐፊያን በጊዜ ርቀት የደበዘዙ የታሪክ ሁነቶችን ለመረዳትም ሆነ ለማስረዳት ብዙ ድካም ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም ታሪክ እንደማንኛም የሳይንስ ዘርፍ የራሱን ተመራማሪና የመረጃ ምንጭ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው። የታሪክ ፀሐፊያን ታሪክን ሲፅፉ የመጀመሪያ ስራቸው መረጃን መሰብሰብ ነው። መረጃው የመጀመሪያ ደረጃ የታሪክ ምንጭን (Primary data source) ወይም የሁለተኛ ደረጃ የታሪክ የመረጃ ምንጭን (secondary data source) ሊሆን ይችላል። ሁለቱንም በአንድ ላይ መጠቀምም የሚቻልበት ሁኔታም አለ። 
የመጀመሪያ ደረጃ የታሪክ የመረጃ ምንጮች የሚባሉት ታሪክ የሆነው ድረጊት በወቅቱ ሲከሰት ወይም ሲከናወን ያዩ፣ የተመለከቱ ወይም በወቅቱ የድርጊቱ አካል የነበሩ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በህያው ምስክርነት ድርጊቱን በታሪክ ፀሐፊው ሊነግሩት ይችላሉ። አለበለዚያም እንደ አይን ምስክር በመፅሐፍ፣ መልክ በዕለት ማስታወሻ፡ በጋዜጣ ወይም በልዩ ልዩ መንገድ ፅፈው ሊያስቀምጡትም ይችላሉ። 
ከዚህ ውጪም ታሪክ ፀሐፊያን የድርጊቱ አካል ከነበሩት ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም ማህበረሰቦች የግል ማህደሮችም (personal documents) እንደመጀመሪያ የታሪክ ምንጭነት በመጠቀም ታሪክን መፃፍ ይችላሉ። እነዚህም የታሪክ ምንጮች፣ ደብዳቤዎች፣ የግል የህይወት ታሪኮች የዕለት ማስታወሻዎችና የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ። የፍርድ ቤት የክስ መዛግብትና ውሳኔዎች ልዩ ልዩ ቃለ ጉባኤዎች (minutes) ህጐችና ደንቦችም ኦፊሴላዊ የታሪክ ማህደሮች (Official history documents) በሚል በመጀመሪያ ደረጃ በመረጃ ምንጭነት ይጠቀሳሉ። የቪዲዮ ምስሎች፣ ፎቶ ግራፎች፣ የድምፅ ውጤቶች ቅሬተ አካላት፣ ቅርሶችና የመሳሰሉትም በመጀመሪያ የታሪክ ምንጭነት የሚጠቃለሉ ናቸው። 
ከዚህ ውጪ በሁለተኛ ደረጃ የታሪክ ምንጭነት የሚጠቀሱት የመጀመሪያ ደረጃ የታሪክ ምንጭ ተብለው ከተጠቀሱት ውጪ ያሉት ምንጮች ናቸው። እነዚህ መረጃዎች ሁነቱ ሊከሰት ባልነበሩ ሰዎች በተለያየ መንገድ በቅብብሎሽ የተገኙ መረጃዎች ናቸው። እነዚህ መረጃዎች በመፅሐፍ መልኩ ሊዘጋጁ ይችላሉ። በትውፊት መልኩም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋሉ። ሁለተኛ ደረጀ የታሪክ ምንጮች ድርጊቱ ሲፈፀም ወይም ሲከሰት ከነበረው ሰው ወይም ህብረተሰብ በቀጥታ የተገኘ መረጃ ስላልሆነ በመረጃ ታዓማኒነቱ ከመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጮች ያነሰ ነው። ታሪክ ፀሐፊዎች ወይም መረጃውን አስተላላፊዎች ከጥሬ እውነታው ይልቅ የራሳቸውን አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ እምነትና የፖለቲካ አቋም እያንፀባረቁበት ሲሄዱ ደግሞ ጊዜው በራቀ ቁጥር የመነሻ እውነታው እየደበዘዘ ከመሄድ ባለፈ አሰሱም ገሰሱም ተደበላልቆ በመጨረሻ ወደተረትነት ይቀየራል። በመሆኑም የታሪክ ፀሐፊያን የሁለተኛ ደረጀ የታሪክ የመረጃ ምንጮችን በመረጃነት ሲጠቀሙ ምርቱን ከግርዱ ለመለየት ሰፊ የማመሳከር ሥራ ይጠበቅባቸዋል። ጥንቃቄው ከመረጃ አሰባሰብ፣ እስከመተንተንና መተርጐም ብሎም እስከ ድምዳሜ (conclusion) የሚደርስ ነው።
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ታሪክ ሲፈተሽ ቀደም ፀሐፊያኑ የፃድቃኑን፣ የሰማዕታቱን፣ የመላዕክቱንና የቅዱሳኑን ታሪክ በየገድሉና ድርሳኑ እያደበላለቁ ሥጋዊውን ከመንፈሳዊው አዋህደው በመፃፋቸው ታሪክ ፀሐፊዎቹ ከሙያው ይልቅ ለወጡበት መደብ የሚወግኑ መንፈሳዊ የትምህርት መሰረትም ብቻ ያላቸው ስለነበሩ ቤተመንግስቱንና የቤተክህነቱን ተግባር እየደበላለቁ የኢትዮጵያን ታሪክ ሲፅፉ ቆይተዋል። 
የሀገሪቱን ታሪክ በዚህ መልኩ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፉ ከመጡት መረጃዎች ጋር የተደበላለቀውን ለመለየት ዘመናዊ የታሪክ ተመራማሪዎች በዙ ጥረዋል። እነ ኢኖሊትማን እና ኮንቲ ሮሲኒ የአክሱም ሀውልቶችን የድንጋይ ላይ ፅሁፍ በማንበብ የተቀበሩ ሳንቲሞችንና የከርሰ ምድር የአርኪዮሎጂ ምርምሮችን በማመሳከር ታሪኩ በጥናት የተደገፈ እንዲሆን ብዙ ጥረዋል። ያም ሆኖ ዛሬም ድረስ የታሪኩን ምርት ከግርድ ለመለየት ብዙ ሥራን ይጠይቃል። በታሪካችን ላይ ያለው ክፍተት የገለባና የምርት ጉዳት መደበላለቅ ብቻም አይደለም የታሪክ አዘጋገብ ፍትሃዊነት ችግርም ይታያል። 
ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ ሲፃፍና ሲነገር የቆየው አጠቃላይ የሀገሪቱን ስዕል ይወክላል ማለት ያስቸግራል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ ሰሜናዊነትና ክርስቲያናዊነት የሚያጠቃው ነው። ውስንነቱ በዚህ ብቻ የሚያበቃ ብቻም አይደለም። ታሪክ ፀሐፊዎቻችን የሀገር ታሪክ ሲፅፉ የመቼታቸው ማጠንጠኛ የሚያደርጉት ነገስታቱን ብቻ መሆኑ በራሱ የኢትዮጵያን ታሪክ በስፋት በንጉስ እገሌ ተወለደ፤ ነገሰና ሞተ በሚለው ላይ ብቻ እንዲንጠለጠል አድርጐታል። 
የነገስታትን ገድሎች በዜና መዋዕል መልኩ የሚተርከው የሚበዛው ታሪካችን በዋነኝነት አንድም በራሳቸው በነገስታቱ አለበለዚያም በፀሐፊ ትዕዛዞቻቸው የተፃፉ ናቸው። ፀሐፌ ትዕዛዝ የሚባሉት የሳራቸው የነገስታቱ የግል ታሪክ ፀሐፊዎች ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች ስማቸው እንደሚያመለክተው በንጉሱ አርታኢነት በትዕዛዝ የሚፅፉ የንጉስ የቅርብ አገልጋዮች ናቸው። ከታሪክ የመረጃ ምንጭነት አንፃር ቀደም ሲል ከጠቀስናቸው ሁለት መሰረታዊ የመረጃ ምንጮች አኳያ የፀሐፌ ትዕዛዛትን የታሪክ መዛብት ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባይቻልም በምንጭነት ለመጠቀም ግን የሚበዛውን ገለባ ማስወገድን ይጠይቃል። በሀገራችን በተለያየ መንገድ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የኢትዮጵያን ታሪክ የፃፉ በርካታ የታሪክ ፀሐፊያን ግን የተቀበሉትን ሁሉ ሳይመረምሩ በማቀበላቸው ታሪኩም ተረቱም ተደበላልቋል። ዘመናዊ የታሪክ ፀሐፊ ምሁራንም ቢሆኑ በምርምር ግኝታቸው መሰረት ታሪክን ከተረት እየለዩ አካፋን አካፋ በማለት ከቆየው ልማድና እድሜ ጠገብ ስርዓት ጋር መላተሙን አልፈለጉም። ይህም በመሆኑ ታሪክ ፀሐፊያኑ ከማህበረሰቡ ጋር እንዳያጋጫቸው የሚፈሩትን እውነት በአብዛኛው እንደነገሩ ነካክተውት ሲያልፉ ቆይተዋል። ይህም የምሁራን ድፍረት ማጣት በሀገራችን የታሪክና የተረት ድንበር እስከዛሬም ድረስ እንዳይለይ አድርጐታል። ዛሬም ቢሆን የጊዜ ጉዳይ እንጂ ተረትን አዘሉትም ተሸከሙትም ያው ተረት በመሆኑ ከታሪክ ጋር መሳ ለመሳ የሚቆምበት እድልና ሞራል አይኖረውም። 
እንደው ለማሳያ ያህል ግን አንድ ታሪክ ቀመስ ተረትን መመልከቱ ነገሩን ግልፅ ያደርገዋል። የእስራኤል ዘር ምንጩ አብርሃም ነው። አብርሃም ይስሀቅን ወለደ ይስሀቅ ያዕቆብን ወለደ ያዕቆብ ደግሞ የአስራሁለቱ የእስራኤል ነገዶች መነሻ የዘር ግንድ የሆኑትን አስራሁለት ልጆች ወለደ። (ዘፍ 35÷23-26 ይመልከቱ) የያዕቆብ ልጆች ስም የእስራኤል ነገዶች ስም መጠሪያ ተደርጓል። ለእስራኤል ነገዶች የሀላፊነትና የሥራ ድርሻ ክፍፍል ሲካሄድ ሌዊ የቤተመቅደስ የክህነት አገልግሎት ሲሰጠው ይሁዳ በአንፃሩ ሁልጊዜም የንግስናውን ዙፋን እንዲይዝ በእግዚአብሔር የተሰጠው መሆኑን (በዘፍጥረት ምዕራፍ 49÷8-12) እናነባለን። በዚህም መሠረት ሁሉም ነገዶች የየራሳቸው ሀላፊነትና ተግባራት ተሰጥቷቸዋል። ይህም በመሆኑ በእስራኤል ቀደምት የንግስና ታሪክ ከይሁዳ ዘር ውጪ ማንም የዙፋኑ ወይም የዘውዱ ህጋዊ ወራሽ መሆን አይችልም። ይህንንም የዘር ሀረግ ተከትሎ ንግስናው የዘር ሰንሰለት እስከ ንጉስ ዳዊት ብሎም እስከ ልጁ ጥበበኛው ንጉስ ሰለሞን ድረስ ሲወርድ እንመለከታለን። 
በዚህ መሀል ደግሞ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሌላ ታሪክ እንመለከታለን። ንግስተ ሰባ (የሰባ ንግስት) የንጉስ ሰለሞንን የጥበብ ዝና ሰምታ በእንቆቅልሽ ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጓዟን (1 ነገስት 101-10) እናነባለን። ንግስተ ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም ከመጓዟ ውጪ በመፅሐፍ ቅዱስ የትኛውም ክፍል ከሰለሞን ልጅ መወለዷን የሚጠቅስ አንዳች ክፍል አናገኘም። 
ታሪኩን ወደ ኢትዮጵያ መለስ ስናደርገው ደግሞ በአብዛኛው በሴማዊ መሰረት ላይ የተመሰረተው የአክሱም ስርወ መንግስት ከፍተኛው የስልጣኔ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ 10ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የኩሽ ዝርያ ባላቸው አገዎች ወይም የዘጉዌ ሥርወ መንግስት ይተካል። ይህም የሥርወ መንግስት ለወጥ የመንግስቱን መቀመጫ ሳይቀር ከአክሱም ወደ ላስታ ያዛወረ ነበር። ይህ የሀይል ሚዛን ከሴማውያኑ አክሱሞች ወደ ኩሽቲኮቹ አገዎች መዛወር ያልጣማቸው የቤተክህነት ሰዎች ዘውዱን ወደ አክሱማውያን ለመመለስ የሚያሰላቸውን ልዩ ልዩ ስልት መቀየስ ጀመሩ። የስልጣን ይገባኛል ፍትጊያው ከሀይል እስከ ፕሮፖጋንዳ በመዝለቅ ከሁለት መቶ ዓመታት ያላነሰ ትንቅንቅን አስከተለ። 
በዚህ መሀል በተለይ የቤተክህነት ሰዎች ውግዘትና ህዝቡን የማስተባበሩ ሥራ እየበረታ በመሄዱ ምክንያት የዘጉዌ ስርወ መንግስት ክፉኛ እየተዳከመ ሄደ። ከዚህ ቀደም ብሎ ግን በዓጼ ላሊበላ ዘመነ መንግስት ወቅት አንድ መፅሐፍ በቤተክህነት ሰዎች ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ተደርጐ ነበር። ይህ መፅሐፍ ክብረ-ነገሥት በመባል ይታወቃል። መፅሐፉ በቀደመው ጥንታዊ የግብፃውያን ቋንቋ ኮፕት የተፃፈ ሲሆን በኋላም ወደ አረብኛ ተተርጉሟል። 
መፅሐፉ ንግስት ሳባ ኢየሩሳሌም የመሄዷን ታሪክ በማስፋፋት ንግስቷ ከንጉስ ሰለሞን ምኒልክ የተባለ ልጅ መወለዷን፣ ልጁም ካደገ በኋላ ወደ አባቱ ተመልሶ መሄዱን፤ ከዚያም በኋላ የታቦትና የንግስትና ሥርዓቱን ከእስራኤል ይዞ መመለሱን በመተረክ፤ ቀደም ሲል በይሁዳ በኩል ለዳዊት ብሎም ለሰለሞን የተሰጠውን የዘር ንግስና ለቀዳማዊ ምኒልክና ዘሮቹ ይሰጣል። በዚህ መፅሐፍ መሰረት አገዎች የምኒልክ ዘር ስላልሆኑ የስርወ መንግስቱ ስልጣን አይገባቸውም። ለህጋዊ ወራሾቹ አክሱማውያኑም መመለስ ይገባቸዋል። 
ሆኖም ይህ መፅሐፍ በአንድ ወቅት ለተከሰተ የስልጣን ግብግብ በረቀቀ መንገድ የተፈጠረ ተረት እንጂ የታሪክ መሠረት የሌለው መሆኑን በርካታ የታሪክ ምሁራን ይስማሙበታል። 
በወቅቱ በነበረው የሥልጣን ግብግብም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ የነበረችው የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ዛግዌዎችን በመቃወም ለአክሱማውያን መወገኗ ይነገራል። የመፅሐፉን ተረትነትና የነበረውን አጠቃላይ ሴራ ያብራሩት ዶክተር አያሌው ሲሳይ ‘‘የአገው ህዝቦችና የዛግዌ ሥርወ መንግስት ታሪክ’’ በሚለው መፅሐፋቸው ገፅ 7 ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል። ‘‘ታሪክ ነገስቱ የኢትዮጵያ ነገስታት ሳባ ከሰለሞን በወለደችው በቀዳማዊ ምኒልክ አማካኝነት የዳዊት ዝርያነት እንዳላቸው የሚነገር የዘልማድ አባባል ሲሆን፣ በእስክንድርያ መንበረ ፓትርያርክ ውስጥ የሰለሞን ዘሮች ነን ይሉ የነበሩትን ወክሎ በኮፕት (ቅብጥ) ቋንቋ መጀመሪያ የፃፈው ማን እንደሆነ የሚያስረዳ ሰነድ ሊገኝ አልቻለም። ምንአልባት ከውጪ በባዕድ አገር ቋንቋ እንደተፃፈ ቢነገር ለጉዳዩ ክብደት ይሰጠዋል፤ እስክንድርያምለኢየሩሳሌም ቅርብ ስለሆነች ታሪኩ ከዚያው በውጪ ልሳን ከተፃፈ እውነት ሆኖ ተቀባይነትን ያገኛል በማለት፤ ዙፋናቸውን በላስታ-ዋግ የአገው ነገስታት የተቀሙት የጥንቱ የአክሱም መንግስት ተሸናፊ መሳፍንት በምድረ ግብፅ ውስጥ ይኖሩ በነበሩ ቅብጪ (copt) የልሳን ተናጋሪዎች መነኮሳት አፅፈው ህጋውያን የዘውድ ወራሽነታቸውን ሊያስመሰክሩ የሞከሩበት አፈ-ታሪክ ይሆናል ግምታዊነት የተላበሰ አነጋገር መሰነዘር ይቻላል’’ ‘‘…ከታሪክ አኳያ አባባሉ ሲመረመር መፅሐፉ እንደተፈለሰፈ ከሚነገርበት ከእስክንድርያም ሆነ የነገስታት የዘር ሀረግ ተመዘዘ ከተባለበት ከኢየሩሳሌም በተመሳሳይ አቀራረብ የሚያወሳ መረጃ ባለመገኘቱ ከተረትነት ያለፈ ከቶ ሊሆን አይችልም።’’ የዘመኑ የታሪክ ምሁራንም ቢሆኑ ክብረ ነገስትን እንደ ዶክተር አያሌው ሁሉ ከተረትነት ያለፈ ስፍራ አይሰጡትም።
በዚህ መፅሐፍ አማካኝነት ከመፅሐፍ ቅዱስ የንግስት ሳባን ታሪክ በማጣቀስ ከእስራኤል በዘሩ የንግስና ሥልጣን ከተሰጠው የንጉስ ዳዊት ልጅ ከሆነው ንጉስ ሰለሞን ምኒልክን ወልዳለች በሚል የዛግዌን ሥርወ መንግስት ህገወጥ በማድረግ የአክሱም መሳፍንትና ቀሳውስቱ ለራሳቸው መንፈሳዊ ተቀባይነትን (Spiritual legitimacy) መስጠት ችለዋል። በመጨረሻም በክብረ ነገስት መፅሐፍ ህጋዊ የዘውድ ወራሽነቱን ያጣው የዛጉዌ ሥርወ መንግስት 1270 ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ካከተመ በኋላ ዘውዱን የተረከቡት የሸዋ ነገስታት ከነመኖሩም ታሪክ ከማያረጋግጥለት የንጉስ ሰለሞን ልጅ ‘‘ቀዳማዊ ምኒልክ (Menelik I)’’ የዘር ግንዳቸውን እያገናኙ ለንግስናቸው መለኮታዊ ሽፋን ሰጡት። 
በአማሮችና በትግሬዎች ትብብር ስልጣናቸው የተነጠቁት የአገዎች ታሪክ አክትሞ በይኮኖ አምላክ አማካኝነት ‘‘የሰለሞን ስርወ መንግስት’’ በሚል የአማራው ዳይነስቲ ንግስናውን ተረክቦ፤ መቀመጫውን ሸዋ፣ የመንግስት ቋንቋውንም ከግዕዝ ወደ አማርኛ ቀየረ። ዝርያውንም በቀዳማዊ ምኒልክ በኩል ዳዊትና ሰለሞን ከተወለዱበትና ከክርስቶስ እናት ማርያም ከተወለደችበት ከነገደ ይሁዳ በመምዘዝ የዙፋኑን መሰረት መለኮት አደረገው። መነሻው ሲመረመር ግን ከሳባ ውጪ የቀዳማዊ ምኒልክ ታሪክ የተፈፀመ ድርጊት ሳይሆን የተፈጠረ ድርሰት ነው። 
ንግስናቸውም ምዳራዊ ተቀናቃኝ እንዳይገጥመው ከመለኮት ጋር በማገናኘት ‘‘ሞዓ አንበሳ ዘአምነገደ ይሁዳ ስዩመ እግዚአብሔር’’ በማለት ዘራቸውን ለንግስና ከተመረጠው ይሁዳና ሰለሞን የስልጣን ምንጫቸውን ደግሞ እግዚአብሔ በማድረግ ስልጣን ያጐናፀፋቸውን ክብረ ነገስት እንደ አይናቸው ብሌን መጠበቅ ጀመሩ። የሀገሪቱም ታሪክ ሲፃፍ ከዚሁ መፅሐፍ እየተጠቀሰ እንዲፃፍ በማድረግ የሀገሪቱ ታሪክ በተረት እንዲበረዝ አደረጉ። ይህ ክብረነገስትን መፅሐፍን መሰረት አድርጐ 1270 ጀምሮ በኢትዮጵያ የነገሰው የሰለሞን ስርወ መንግስት እስከ ዓፄ ኃይለስላሴ የመጨረሻ የዘውድ ዘመን ድረስ ቆይቷል። 
በክብረ ነገስት መፅሐፍ ውስጥ የፈጠሩትንም ምናባዊ ምኒልክ ነገሰ የተባለበት ዘመን ወደ ኋላ በመቁጠር የሀገሪቱን ታሪክ ከራሳቸው ንግስና ጋር በመገናኘት የሀገሪቱን ታሪክ 3ሺና ከሃያ በላይ መሆኑን ሲገልፁ ቆይተዋል። በነገራችን ላይ ንግስናን ከመለኮት ጋር እያገናኙ አጥንትና ደምን ቆጥሮ ስልጣንን በዘር መከለል በኢትዮጵያ ብቻ የነበረ ሳይሆን በዘመነ ፊውዳል በአውሮፓም የነበረ ታሪክ ነው። ሆኖም አውሮፓውያንም ሆኖ የሌች ሀገራት የነገስታት ዘሮች እንደ ኢትዮጵያ ነገስታት የታሪክ ቀዶ ጥገናን በማካሄድ የሀገራቸውን ታሪክ ከተረት ጋር አልሸቀጡም።
በፀጋው መላኩ 

No comments:

Post a Comment