Wednesday, April 17, 2013

ኢንጅነር ዘለቀ ረዲ ከአንድነት ፓርቲ አመራር ለቀቁ *[የአንድነት ፓርቲ አመራሮች] አምባገነኖች ናቸው


*የወጣቱ ፈተና እነዚህን አዛውንቶች ዲሞክራሲ ማስተማር ነው
በዘሪሁን ሙሉጌታ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የስራ አስፈፃሚ አባልና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ በመሆን ለአለፉት ሁለት አመታት ሲያገለግሉ የነበሩት ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ በፈቃዳቸው ከፓርቲ አመራርነታቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ።
የፓርቲው አመራሮች አምባገነኖች መሆናቸውንና እሳቸውን በነፃነት ሊያሰሯቸው ባለመቻላቸው ከሚወዱትና ከሚያከብሩት ትግል እራሳቸውን በፈቃዳቸው ማግለላቸውን በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት ሰፊ ቃለ-ምልልስ ላይ ገልፀዋል።
ኢንጂነር ዘለቀ ለፓርቲው ፕሬዝዳንት በፃፉት ሦስት ገፅ መልቀቂያ ደብዳቤ ላይ እንደገለፁት ፓርቲያቸውን በፍፁም ቅንነትና ታማኝነት በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው እንዲሁም በገንዘባቸው ፊት መሪ በመሆን ሲደግፉ መቆየታቸውን አውስተዋል።

ነገር ግን በፓርቲው ውስጥ ባሉ ጥቂት አምባገነን አመራሮች ጋር መግባባት ባለመቻላቸው የፓርቲ አባልነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከአመራርነታቸው መልቀቃቸውን አረጋግጠዋል።
አሁን ያለው የአንድነት አመራር ‘‘ምጥን’’ ዲሞክራሲ በመከተል ትግሉን ከማፋፋም ይልቅ በማዳከም ላይ መሆኑን ያብራሩት ኢንጂነር ዘለቀ ከሚወዱት ፓርቲ በግዴታ ውዴታ ለመልቀቅ መገደዳቸውን አብራርተዋል።
የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ከሆኑ ጊዜ አንስቶ አዳዲስ አሰራር በማምጣት ኃላፊነቱ ሲረከቡ ሊዘጉ የተቃረቡ ሦስት /ቤቶችን በማሳደግ ወደ 25 /ቤቶች ተከፍተው እንዲሰሩ ማድረጋቸውን፣ አባላት በጥራት የመመልመልና የመከታተል ተግባራቸውን ሲወጡ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ የፓርቲው አባላት ለውጥ እንዲመጣ የሚታገሉና ዓላማ ያላቸው ቢሆንም አመራሩ ግን ለዘብተኛ ነው ያሉት ኢንጂነሩ ‘‘በተለይ ሊቀመንበሩ በእጅጉ ለዘብተኛ ከመሆናቸው ባሻገር ራሱ ኢህአዴግ ቦታውን ለቆ ኑና ተረከቡኝ እስከሚል የመጠበቅ እንጂ ገፍቶ የመሄድና ለውጥ እንዲመጣ የማድረግ ዓላማ እንደሌላቸው ለመገንዘብ ችያለሁ’’ ብለዋል።
‘‘እኔ በማውቀውና ባነበብኩት ትግል በእርቅና በሽምግልና፣ በልመና እንዲሁም እንደራደር በሚል ሳይሆን ሕዝብን አነቃንቆ ጫና በመፍጠር ይመጣል። አሁን አንድነትን የምንመራ ሰዎች አይነት የትግል ስልት ግን ጠንካራ ታጋዮችን ከማስበላት የዘለለ ምንም ጥቅም የለውም’’ በማለት እነ አንዱአለም አራጌን አቶ ናትናኤልን በምሳሌነት አንስተዋል።
የኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ከፓርቲ መሰናበት በማስመልከት የፓርቲው ሊቀመንበር / ነጋሶ ጊዳዳ ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው ለእሳቸው በመደበኛ ሁኔታ ተፅፎ የተሰጣቸው ደብዳቤ አለመኖሩን፤ ኢንጂነር ዘለቀም በስራ ላይ ከመሆናቸው ባለፈ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ፣ ኢንጂነሩ ይልቀቁ እንኳ ቢባል በፕሬዝዳንቱ ሳይሆን በፓርቲው ብሔራዊ /ቤት አማካኝነት ቀርቦ የሚወሰን መሆኑን አመልክተዋል።
በአንፃሩ ጉዳዩን ወደ ሚዲያ በመውሰድ ሕዝቡ በፓርቲው ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚደረገው ጥረት አግባብ አለመሆኑ፣ ፓርቲው ለዲሞክራሲ የቆመ እንደመሆኑ መጠን ችግሮቹን በውስጥ ተነጋግሮ መፍታት ይገባ እንደነበር በመግለፅ የኢንጂነር ዘለቀን ወደ ሚዲያ መውጣት ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም ሚዲያውም የእሳቸውን ኀሳብ ማስተጋባቱ ትክክል አለመሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል። 

No comments:

Post a Comment