Finote nestanet
ላለፉት 5 ወራቶች የመድረክን የስራ አፈፃፀም ሁኔታ በቅርብ ሲገመግም የነበረው የአንድነት ብሔራም/ቤት የመድረክ አባል ድርጅቶች በአስቸኳይ እንዲዋሀዱ ጠየቀ፡፡
ብሔራዊ ም/ቤቱ ቅዳሜ ሚያዝያ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የአራት ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ላለፉት አራት ዓመታት አሳሳቢ በሆኑና በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ የቆየ ቢሆንም ሀገራችንን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር በተደረገው ትግል ውስጥ የተጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ብሔራዊ ም/ቤቱ በሰየመው ገምጋሚ ኮሚቴ አማካኝነት የመድረክ አጠቃላይ ሁኔታ በስድስት ዋና ዋና ክፍሎች ተገምግሞ ሚያዝያ 19/2005 ዓ.ም ለብሔራዊ ም/ቤቱ በግምገማው ሪፖርት ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ ከጠዋቱ 3፡00 – 1፡00 ሰዓት ስብሰባውን ያካሄደው የአንድነት ብሔራዊ ም/ቤት በዚሁ የግምገማ ሪፖርት ላይ ብቻ በመወያየት የመድረክ ጉዞ በውህደት እንዲጠናቀቅ ወስኗል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ሁኔታ እጅግ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ የወደቀችበት ሁኔታ በመኖሩ መድረክ ጉዳዩን በጥልቀት ገምግሞ ራሱን የኢትዮጵያ ህዝብ በሚፈልገው የለውጥ ደረጃ በማጠናከርን አማራጭ የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተገቢውን እንቅስቃሴ በማድረግ ሕዝቡን በዙሪያው የማሰባሰብ ተግባር እንዲያከናውን የላቀ ጥረት እንዲያደርግ ብሔራዊ ም/ቤቱ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
አንድነት ፓርቲ መድረክ ሊወስዳቸው የሚገባቸውን የመፍትሔ ሃሳቦች በጥልቀት የተወያዩት የብሔራዊ ም/ቤቱ አባላት የግንባሩ አባል ፓርቲዎች የፕሮግራምና የስትራቴጂ አንድነት በ 3 ወር ጊዜ ውስጥ በመፍጠር በቀጣዩ ሂደት በአስቸኳይ ወደ ውህደት መምጣት እንዳለባቸው ወስኗል፡፡ መድረክ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውን የፖለቲካ ለውጥ ማሳካት በሚያስችለው ቁመና እራሱን እንዲያዘጋጅ ለአንድነት ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ብ/ም/ቤቱ መመሪያም ሰጥቷል፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የቀረበው የግምገማ ሪፖርትና በውይይቱ ላይ የተነሱት ተጨማሪ ሃሳቦች የም/ቤቱ ሠነድ ሆኖ እንዲመዘገብ በመወሰን ይኸው ሰነድ ለግንባሩ አባል ድርጅቶችና ለህዝብ ይፋ እንዲሆን በመወሰን ብሔራዊ ም/ቤቱ የዕለቱን ስብሰባ አጠናቋል፡፡
No comments:
Post a Comment