Thursday, April 11, 2013

ዜጎችን ከስፍራቸው ማፈናቀል አንዱ የኢህአዲግ ማናለብኝ ህገዎጥ ተግባር ነው።


ከሰሜን አሜሪካ አንድነት ድጋፍ ማህበራት የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት፣ ዜጎች በማንኛውም የኢትዮጵያ ግዛት የመንቀሳቀስ፣ የመኖር ፣ የመነገድ ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳላቸው በግልጽ ያስቀምጣል። ነገር ግን ገዢውANDINET NORTH AMERICA ASSOCIATION OF SUPPORT ORGANIZATIONS (ANAASO) ፓርቲ ይሄን የዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብት በመጣስ በተለያዩ ቦታዎች በዜጎች ላይ የሚያደርሰው ግፍና በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነዉ።
በሰለጠነው አለም፣ ዜጎች ከመኖሪያ ስፍራቸው የሚፈናቀሉት፣ የሚኖሩበት አካባቢ ተፈጥሮ ባስከተለው ቀውስ የተጠቃ ወይም የሚጠቃ ከሆነ ነዉ። በአገራችን ኢትዮጵያ እያየን ያለነዉ ግን ኢትዮጵያውያን የተለየ ቋንቋ በመናገራቸው፣ የዚህ ወይም የዚያኛው ብሄረሰብ አባል በመሆናቸው በአገራቸው እንደ ባእድ ተቆጥረዉ፣ ነፍጥ በጨበጡ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለስልጣናት ና አገልጋዮቻቸው በኃይል ሲፈናቀሉ ነዉ።

ከጥቂት ወራት በፊት ከደቡብ ክልል በግፍ ተባረው አዲስ አበባ፣ ሰሞኑን ደግሞ ከቤነሻንጉል ጉሙዝ ተባረዉ መተከል እና ፍኖተ ሰላም እንዲሰፍሩ የተደረጉ ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጅ ወገኖቻችንን እንደምሳሌ መጥቀሱ ይበቃል። ከቤኔሻንጉል በአስቸኳይ እንዲባረሩ የተደረጉት ወገኖቻችን ፣ በአውቶብስ እንደ እቃ ታጭቀው፣ ክብራቸው ተገፎ የተባረሩ ሲሆን፣ አንዱ አውቶብስ ከአቅም በላይ ሰው በመጫኑ ምክንያት አደጋ ደርሶ፣ ከአምሳ ስድስት በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሞተዋል። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት አሰቃቂ የዘር ማጥራት ወንጀል በኢትዮጵያውያን ላይ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ነው።
ሕወሃት/ኢሕአዴግ ፣ በርካታ የአገራችን ድንግል መሬቶችን ለሕንዶች፣ ለአረቦችና ለቻይናዎች እየሰጠ፤ ከነዚህ አገራት የመጡ ዜጎች በአገራችዉ ያላገኙትን የተደላደለ ኑሮ እንዲኖሩ እያደረገ፣ ለነዚህ ለዉጭ አገር ዜጎች ቀይ ምንጣፍ እያነጠፈ፣ ኢትዮጵያዉያንን ግን ከመኖሪያቸው ማፈናቀሉ፣ ማዋረዱ፣ ማሰሩና መግደሉ፤ የዚህን አገዛዝ ምንነት በግልጽ የሚያሳይ ነዉ።
በቤኔሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች የሚኖረው ሕዝባችን ፣ የተለያዩ ቋንቋዎች ከሚናገሩ፣ ለዘመናት ተፋቅረው፣ ተዋልደው፣ እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው ከኖሩ በርካታ ብሄር ብሔረሰቦች የተውጣጣ ነው። ወላይታው በሲዳማው ላይ፣ ሲዳማው በኦሮሞው ላይ፣ ኦሮሞው በጉሙዙ ላይ፣ ጉሙዙ በአማራው ላይ፣ አማራው በትግሬው ላይ፣ ትግሬው በአፋሩ ላይ፣ አፋሩ በኢሳው ላይ …..ችግር የለውም። ኖሮትም አያውቅም። ገዥዎቻችን ግን እየነጣጠሉ ሲመቱን ኖረዋል፡፡ በመሆኑም በደቡብና በቤነሻንጉል የተከሰተዉ አሳዛኝ የዘር ማጥራት ወንጀል በአገዛዙ የተፈጸመ እንጂ በአካባቢዉ ሕዝብ የተፈጸመ አይደለም። ለዚህም ሕወሃት/ኢሕአዴግ እና አሁን ያሉት አመራሮች ሙሉ ተጠያቂ እንደሆኑ ለማረጋገጥ እንወዳለን።
ከዚህ ዘረኛና እኩይ ተግባራቸው በአስቸኳይ ተቆጥበው፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ወደ ስፍራቸዉ እንዲመለሱ፣ ለደረሰባቸው ግፍም ተመጣጣኝ ካሳ እንዲሰጣቸውና ለዚህም ተጠያቂ የሆኑ የወረዳ፣ የክልል እንዲሁም የፌደራል ባለስልጣናት በአስቸኳይ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ እናሳስባለን።
በሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ማህበራት ይሄን መግለጫ ስናወጣ፣ በርካታ የፖለቲካና የሲቪክ ማህበራት ከኛ በፊት ተመሳሳይ መግለጫ እንዳወጡ ማስታወስ እንፈልጋለን። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ጠንቅቀን መረዳት ያለብን መሰረታዊ ሃቅ አለ። ይህ ዓይነቱ ግፍ፣ መግለጫ በማውጣት ብቻ መፍትሄ እንደማያገኝ መረዳት አለብን። ከመግለጫ ማውጣት ባሻገር፣ ዘለቈታዊ ዉጤት ሊያመጣ የሚችል የተቀነባበረ ትግል መጧጧፍ ይኖርበታል።
በዚህ ረገድ፣ ቀዳሚዉ ሥራ ዲሞክራሲያዊ ትግሉን ማስተባበርና ኢትዮጵያዉያንን በአንድ ቡድን ማሰባሰብ በመሆኑ፣ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምንገኝ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት ያለንን ልዩነቶች አቻችለን፣ የህግ የበላይነት የሰፈነባትና የዜጎች እኩልነት የተረጋገጠባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ቆርጠን በአስቸኳይ መነሳት አለብን እንላለን። የሰሜን አሜሪካ አንድነት ድጋፍ ማህበራት፣ ለዲሞክራሲያዊ ትግሉ የድርሻቸውን ሃላፊነት ለመወጣት፣ ከዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናችንንም በዚህ አጋጣሚ ለማስገንዘብ እንወዳለን።
ነጻነት የትግል ውጤት ነው
የትም ቦታ የተፈጸመ የፍትህ መጓደል በሁሉም ቦታ ፍትህ ላይ የተቃጣ አደጋ ነው! (ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር)
Injustice anywhere is a threat to justice everywhere! (Martin Luther King Jr.)

No comments:

Post a Comment