Wednesday, April 24, 2013

ጨፌ ኦሮምያ የክልሉን አስተዳደር መገምገም ጀመረ ። በክልሉ ቢሮ ተቀምጠው አበል የሚበሉ አካላት አሉ


የኦሮምያ ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮምያ) የክልሉን የስራ አስፈፃሚ መገምገም ጀመረ። ምክር ቤቱ ከትናንት ጀምሮ እስከ ነገ በሚዘልቀው የግምገማ ኮንፈረንስ በተመረጡ ሴክተሮች በተለይም በመንግስት ገቢ፣ የፋይናንስ ግዢና አስተዳደር እንዲሁም ከመሬት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።
በአዳማ ከተማ መካሄድ በጀመረው በዚሁ የግምገማ ኮንፈረንስ ላይ የኦሮምያ ጠቅላይ ኦዲት ጋር በመሆን የተዘጋጀ ሲሆን በክልሉ ገቢ ፋይናንስ ግዢ እንዲሁም የመሬት ዙሪያ እየታየ ያለው ክፍተት አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ በክልሉ የፍትህ አካላት ከአስፈፃሚ ተቀናጅተው በመስራት ፈንታ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሰፍን በማድረጋቸው ለችግሩ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማመላከት እንደሆነ ታውቋል።
የጨፌ ኦሮምያ ምንጮች ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት በዛሬው ዕለትም በክልል ደረጃ ከፋይናንስ፣ ከመንግስት ግዢና ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ የኦሮምያ ጠቅላይ ኦዲት ቢሮ መረጃውን ይፋ እንደሚያደርግም ታውቋል።
በክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች እየታየ ያለው ከፍተኛ ሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት መስፋፋቱ ሕዝቡን እያማረረ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮች በአንዳንድ የፍትህ አካላት ሳይቀር በክልሉ ቢሮ ተቀምጠው አበል የሚበሉ እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል።
ከግምገማ ኮንፈረንሱ በኋላ የሚወሰዱ እርምጃዎች ከዚህ በፊት የነበረውን የመለሳለስ አካሄድ በመቀየር ተገቢውን ቅጣት ለመስጠት የአሰራር ክፍተቶችን መለየታቸውን ምንጮች የጠቀሱ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም አቃቢያነ ህጎች አጥፊዎችን ለማስቀጣት የሚያደርጉት ጥረት በክልሉ ፍርድ ቤቶች የመለሳለስ ሁኔታ መታየቱ ተደርሶበታል ብለዋል። በተለይም ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸው ጉዳይ መለሳለስ ማሳየታቸውን የሚያመለክቱ ጉዳዮች ከእነማስረጃ የቀረበበት ሁኔታ በመፈጠሩ ከግምገማ ኮንፈረንሱ በኋላ የዳኞች ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል።
የግምገማ ኮንፈረንሱ በክልሉ ም/ቤት (ጨፌ ኦሮምያ) አፈጉባኤ አስተባባሪነት የተካሄደ ሲሆን የክልሉ ም/ቤት የበጀት አስተዳደርና ፋይናንስ ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የኦሮምያ ጠቅላይ ኦዲት ቢሮ እንዲሁም የክልሉ የስነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ተዘጋጅቷል። የወረዳ የዞን ፍ/ቤት ፕሬዝዳንቶች፣ ዳኞችና ዐቃቤያነህጎች ከልዩ ልዩ አካላት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
በዘሪሁን ሙሉጌታ

No comments:

Post a Comment