Wednesday, April 24, 2013

"Politics is a dirty game”


"Politics is a dirty game”
እኔና ፖለቲካን የሙጥኝ ያለ ወዳጄ  በአዲስ ዓመት ዋዜማ ስለ ፖለቲካ ስናወጋ ምዕራባውያኑ "Politics is a dirty game” የሚል አባባል እንዳላቸው ተነሳና እንዲህ አለ - ወዳጄ ..እነሱ እኮ መጫወቻው ሜዳ አላቸው... ስለዚህ ቢያንስ ይጫወቱታል.. አንዳችም ሙግት መግጠም አላስፈለገኝም፤ እንዳለ ተቀበልኩት፡፡ እውነት ነዋ! በኋላ ሳስበው ከፈረንጆቹ አባባል እኛ ጋ የቀረው (Politics is dirty” የሚለው ብቻ መሆኑን አጤንኩኝ፡፡ ጌሙ ሲቀነስ የሚቀረው ቆሻሻነቱ ወይም መጥፎነቱ ብቻ ነዋ!
እስቲ ዝም ብላችሁ ከ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ታዘቡልኝ... አንዴም እኮ ጨዋታ ሆኖ አያውቅም፡፡ እኔና እናንተ ወረቀት ላይ ከምንጫወተው በቀር ማለት ነው፡፡ አሁን ስመረምረው ግን ችግሩ እየገባኝ የመጣ ይመስለኛል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፖለቲካ ቅድም እንዳልኩት በተለይ
ለኢትዮጵያ እሳት ነው፤ ዜጐችን የሚቆላ ጥይት፡፡ ለሰለጠኑትና ለበለፀጉት ግን Politics is a dirty game ለምን ይሄ አይነት ግዙፍ ልዩነት ተፈጠረ ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ እነሱን ፖለቲካ እሳት ሆኖ የማይፈጃቸው፤ ጥይት ሆኖ የማይቆላቸው በአይነቱ ለየት ያለ መከላከያ ልብስ ስላሰሩለት ነው፡፡ ዲሞክራሲ ነው ከፖለቲካ ጥይት መከላከያቸው፡፡ ለነገሩ እነሱም ቢሆኑ ፖለቲካን አደገኛው አንጋፋ ሙያ ነው የሚሉት፡፡ እኛ ጋ ግን እንኳንስ ሙያ (Profession) ሊሆን ከጥይትነቱ (እሳትነቱ) ገና አልተላቀቀም፡፡ በየጊዜው ከፈረንጆቹ የምናስመጣው የዲሞክራሲ ጥብቆም የፖለቲካውን እሳት ሊከላከልልን አልቻለም - አንዴ እየጠበበን ሌላ ጊዜ ደግሞ እየሰፋን፡፡ 

እና ምን ይሻለናል? እንደኔ ከሆነ ለምን መከላከያውን እስክናገኝ ፖለቲካው አይቀርብንም፡፡ ለእኛ ለተራ ተርታው ዜጐች ብቻ ሳይሆን ለተቃዋሚ ፓርቲዎችም ማለቴ ነው፡፡ እንግዲህ ተቃዋሚዎችም እንዲህ የሚማስኑት ወያኔ/ ኢህአዴግን ከሥልጣን አስወርደው በተራቸው እንደ ወያኔ በፖለቲካ እሳት ሊፈጁን አይደለም መቼም !እንዲፈጁንም አንሻም ! (ክፉ ስለሆኑ እኮ አይደለም፡፡ እኛ የፖለቲካ እሳቱን መከላከያ ስላለበጀን ነው፡፡) ቢቀርባቸውስ? (ሥልጣኑን ማለቴ ነው!) ሥልጣኑን ለማግኘት በእሳቱ መፈጀት ብቻ ሳይሆን ተለብልቦ መቃጠልም ስላለ ዝም ብለው ቢኖሩስ? ..አይቻልም ወይ መኖር ሥልጣን ላይ ሳይወጡ.. ለማለት ያህል ነው፡፡ ኧረ ይቻላል ... እንኳን ልማት ተኮሩ ወያኔ/ኢህአዴግ ቀርቶ የትኛውም አምባገነን የአፍሪካ መንግሥት ሥልጣኑን ካልነኩበት ብዙም አይተናኮልም እኮ፡፡
ግን እስቲ የ21 ዓመት የፖለቲካ ክንውናችንን ቁጭ ብለን እንገምግመው፡፡ አተረፍን ወይስ ከሰርን? ለመለምን ወይስ ተለበለብን? ይሄን ጥያቄ አንጋፋዎቹ ፖለቲከኞች ወይም ፓርቲዎች ቢመልሱት ይሻላል፡፡ ከዚያ ፖለቲካ ይቅርብን ወይስ እንግፋበት የሚለውን ራሳቸው ይወስኑት፡፡
እኔ በበኩሌ የፖለቲካ ጥይት መከላከያ እስኪሰናዳልን ቢቀርብን እመርጣለሁ፡፡ ማነው የሚያሰናዳው? ሌላ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ የዚህንም መልስ ራሳቸው ፖለቲከኞቹ ቢመልሱት ይሻላል፡፡
እውነቴን ነው የምላችሁ  ... የዲሞክራሲ ጥብቆን ከማሰፋታችን በፊት ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ መቧቸር ራስንና አገርን ለአደጋ ማጋለጥ ነው፡፡ የፖለቲካ እሳት (ጥይት) ሲዘንብብን (ሲወርድብን) መግቢያ ይጠፋናል፡፡ ከዝናቡ መጠለያ ጃንጥላ አላበጀንማ! እናም ፖለቲካ ቢያንስ እንደሰለጠኑት a dirty game እስኪሆን ድረስና የጥይት መከላከያ እስክናበጅ ይቅርብን ብያለሁ
በተለይ ሰላማዊ ተቃዋሚ ነን ብለን በአገር ቤት ውስጥ ያለነው! የፖለቲካውን ሂደት ወይም የዲሞክራሲን ጉዞ ያደናቅፋል የሚለኝ አይጠፋም፡፡ እኔ ግን አስመሳይ ወይም ቀጣፊ እለዋለሁ፡፡ ለምን ብትሉኝ... በፖለቲካ ሰበብ ዜጐች ሲታሰሩ፣ ነፃነታቸው ሲታፈን፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈፀም፤ ድህነት ሲንሰራፋበት፤ የኑሮ ዋስትና ሲያጣ፤ ሥራ አጥ ሲበረክት ወዘተ... እንዲህ አላሉማ!
ብዙ ጊዜ ኢህአዴግን ታግለን እናሸንፈዋለን የሚል ማስፈራሪያ ከተቃዋሚዎች ጎራ ሲስተጋባ እሰማለሁ፡፡ ግን እንዴት? በምን? የሚመልስ የለም ወይም በተፈጥሮው መልስ የሌለው ጥያቄ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አባባሉ ብዙም አይደላኝም፡፡ ይልቅስ ..አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው.. የምትለዋ
ዘፈን  የመሃሙድ አህመድ ዜማ ትዝ ይለኛል፡፡ ቆይ ግን በሞቴ ወያኔ/ኢህአዴግን እንዴት ነው ሊያሸንፉት ያሰቡት? ተቃዋሚዎችን ማለቴ ነው፡፡ የፖለቲካውን ፍልሚያ የሚመክቱበት ጋሻ ሳያዘጋጁ? እንዴት ነው 17 አመት ከደርግ ጋር ተፋልሞ ሥልጣን የያዘን ፓርቲ ታግለን እናሸንፋለን የሚሉት? በአሜሪካ በየ4 አመቱ ዲሞክራቶቹ ሪፐብሊካነን ቢያሸንፉ እኮ አይገርምም! ሁለቱም የመፋለሚያ መሳሪያቸው ተመጣጣኝ ነው - ዲሞክራሲ ይባላል፡፡ በዚያ ላይ ፖለቲካ እሳት ሳይሆን ጌም ነው - ደርቲ ጌም ቢሆንም፡፡
ስለዚህ ከትግሉ በፊት የፖለቲካ እሳት ወይም ጥይት መከላከያውን እናሰናዳ ባይ ነኝ! የዲሞክራሲ ጥብቆ በልካችን ሳናሰፋ ግጥሚያ መግባት አገርንም ዜጐችንም በእሳት ማስለብለብ ያመጣል፡፡ በ97 ምርጫ መንግስት ዜጐችን የገደለው፣ ያሰረው፣ ያዋከበው ወዶ ነው እንዴ? የፖለቲካ ጥይት መከላከያ ስለሌለን ነበር እኮ፡፡ (ምንም እንኩዋን ኢህአዴግ አድማ መበተኛ ስላልነበረኝ ነው ቢልም) እንደ ፈረንጆቹ ዲሞክራሲ የተባለው መከላከያ ቢኖረን ኖሮ ግን እሱም አይተኩስ እኛም አንሞትም ነበር፡፡
እኔ በበኩሌ በፖለቲካ ሰበብ መታሰር፣ መዋከብ፣ መሰደድ፣ መገደል እስካልቀረ ድረስ ለአቅመ ፖለቲካ አልደረስንም ባይ ነኝ፡፡ ለአቅመ ፖለቲካ የሚያበቃንን ቅድመ ዝግጅት እስክናደርግ ደሞ ፖለቲካውም ስልጣኑም ቢቆየንስ?
ወያኔ/ኢህአዴግ እንደ ጋዳፊ 40 ዓመት ሊገዛን ... ብሎ የሚደነፋ አይጠፋም፡፡ መልሱ ግን ቀላል ነው፡፡ የራሳችንን የዲሞክራሲ ጥብቆ ካላሰናዳን ሌላም ነገር አይቀርልንም፡፡ የስልጣኑን ነገር በተመለከተ ግን ኢህአዴግም ቢሆን 40 ዓመት ሥልጣን ላይ ይቀመጣል ብዬ አላስብም - ለምን መሰላችሁ? ሥልጣን ይሰለቸዋላ! በዚያ ላይ እርጅናም አለ እኮ! (ፓርቲ ያረጃል እንዴ?)
ኢህአዴግ 40 ዓመት ገዛም አልገዛም፤ አረጀም አላረጀም ...  አገራችንን ለአቅመ ፖለቲካ እናብቃት፡፡ በአገራችን ፖለቲካ የሚለበልብ እሳት ሳይሆን ጨዋታ እንዲሆን እንትጋ - ቆንጆ ጨዋታ እንኳን ባይሆን Dirty game እናድርገው፡፡ 


No comments:

Post a Comment