Thursday, April 25, 2013

የፌደራል መንግስቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በቤንሻንጉል ተፈናቃዮች ላይ ስህተት መፈጸሙን ተናገሩ


ለሳምንታት የመላውን ኢትዮጵያውያን ትኩረት በመሳብ መነጋገሪያ ሆነ የቆየው በቤንሻንጉል ጉሙዝ በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመው መፈናቀል በተመለከተ የፌደራል መንግስቱ ከረጅም ጊዜ ዝምታ በሁዋላ ትናንት በጠቅላይ ሚኒሰትሩ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ አማካኝነት አቋሙን ግልጽ አድርጓል።
አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰው መፈናቀል በሙስና በተዘፈቁ የአካባቢው ባለስልጣናት መፈጸሙን ገልጸዋል። መንግስታቸው ማጣሪያ በማድረግ እርምጃ እንደሚወስድም ገልጸዋል። በየትኛውም ክልል የሚገኙ ባለስልጣናት ከእንግዲህ በየትኛውም አካባቢ የሚደረጉ መፈናቅሎች አጥፊ፣ ጸረ ህዝብ እና ጸረ ህገመንግስት በመሆናቸው መንግስት በቸልታ አይመለከተውም ብለዋል።

አቶ ሐይለማርያም በክልሎች ለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የክልሎች እንጅ የፌደራል መንግስቱ ጉዳይ አይደለም በማለት በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የኢህአዴግ ባለስልጣናትና ደጋፊዎቻቸው የሚሰጡትንም አስተያየት ውድቅ አድርገውታል። እርሳቸው እንዳሉት የፌደራሉ መንግስት በየትኛውም ክልል የሰብአዊ መብቶች ሲፈጸሙ ጣልቃ የመግባት ግዴታ አለበት።አቶ ሀይለማርያም የሰጡት መግለጫ አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ቀደም ከሰጡት መግለጫም ሆነ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ከሰጡት መግለጫ ጋር የሚጣረስ መሆኑ የፌደራል መንግስት አዲስ አቋም መያዝ መጀመሩ ነው? ወይስ አሁን ለተፈጠረው ውጥረት ማስተንፈሻ ነው? ወይስ በፌደራል መንግስት መካከል መናበብ የለም? የሚል ጥያቄ አስነስቷል።አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ቀደም በቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ደን በመጨፍጨፋቸው መባረራቸውን መናገራቸው ይታወሳው።የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አህመድ ናስር ከአንድ የመወያያ መድረክ ጋር ባደረጉት ውይይት ግለሰቦቹ የተፈናቀሉት የፌደራል መንግስቱ እና ክልሎች የሰፈራ መርሀግብርን በተመለከተ በደረሱበት ስምምነት መሰረት መሆኑን ገልጸው ነበርየኢትዮጵያው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር እና የህወሀት ነባር ታጋይ የሆኑት አምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስ ለጀርመን ድምጽ በሰጡት ቃል ምልልስ ሰዎቹ የተፈናቀሉት በህገወጥ መንገድ መሬት በመያዛቸው መሆኑን መግለጻቸውም ይታወሳል።እንደ አምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስ ሁሉ የሰዎች መፈናቀል ተገቢ ነው በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ከተሟገቱት መካከል የቀድሞዋ የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኛ የአሁኑዋ የኢህአዴግ ቀንደኛ ደጋፊ ተደርጋ የምትታየው የዛሜ ኤፍ ኤም ራዲዮ ባለቤት / ሚሚ ስብሀቱ ተጠቃሽ ናት።አቶ ሀይለማርያም የሰጡት መግለጫ መፈናቀሉን ደግፈው ሲከራከሩ የነበሩትን የኢህአዴግ አባላት ያሳፈረ ሆኗል። ይሁን እንጅ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አቶ ሀይለማርያም ተጠያቂነቱን ወደ ታች ለማውረድ የሚያደርጉትን ሙከራ አልደገፉትም። እነዚህ ወገኖች ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ጀምሮ ሁሉም ሀይላት ተጠያቂ ሲሆኑ፣ መንግስት ከዚህ ቀደም በጉራፈርዳ እና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለተፈናቀሉት ተገቢውን ካሳ ሲከፍል እና ወደ ቦታቸው ሲመልሳቸው እንዲሁም በይፋ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ሲጠይቅ ብቻ ነው የፖሊሲ ለውጥ ማድረጉን አምኖ መቀበል የሚቻለው በማለት አስተያየት ይሰጣሉ።

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ከአቶ ሀይለማርያም ንግግር በሁዋላ ኢሳት በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰውን መፈናቀል በማጋለጥ በኩል ለተጫወተው ሚና አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment