ከየትኛው FM እንደሚሰራጭ አላውቅም ግን ምክር ቢጤ ያስተላልፉትን እንስማቸው ፡፡ ተናጋሪውንም እንዲሁ ብቻ የሃይማኖት
መምህር (አዋቂ) እንደሆኑ ገብቶኛል፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስትያንን ወክለው የቀረቡ መሆናቸውን ተገነዘብኩኝ፡፡
የሰማሁት ጥቂት ነው - ከንግግራቸው፡፡ የቀሰምኩት ቁም ነገር ግን አንዳንድ ሰው ሙሉ ቀን ተናግሮም የማይገኝ ነው፡፡
ገና ማዳመጥ ስጀምር መምህሩ የሃይማኖት
ተቋማትን እየወቀሱ ነበር፡፡ ከምዕመናን ገንዘብ አሰባስቦ እስር ቤት ውስጥ ቤ/ክርስትያን ለማሰራት ተፍ ተፍ የሚሉ የሃይማኖት ሰዎችን
ክፉኛ ይተቻሉ - መምህሩ፡፡ እስር ቤት ውስጥ ቤ/ክርስትያን ከማሳነፅ ወደ ወህኒ የሚወርደውን የወንጀለኛ ቁጥር እንቀንስ የሚሉት
መምህሩ፤ የወንጀለኞች ቁጥር መበርከት የሚያሳየው የሃይማኖት ተቋማት በአግባቡ ሥራቸውን እያከናወኑ አለመሆኑን ነው ብለዋል፡፡ ከሞራልና
ሥነ ምግባር አኳያ ሁሉም ሃይማኖቶች ልዩነት እንደሌላቸው በመጥቀስም አማኞቻቸውን ከወንጀልና ከምግባረ ብልሹነት በመከላከል ወደ
ወህኒ የሚወርዱ ወንጀለኞችን ቁጥር ለመቀነስ መትጋት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ የሃይማኖት ትምህርትን በአግባቡ ስላልሰጡና ምዕመናኑን
ስላላስተማሩ እስር ቤቶች እንዲስፋፉ፣ የእስረኞች ቁጥር እንዲጨምር የራሳቸውን አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው ሲሉ ተቋማቱንና የሃይማኖት
መሪዎችን ተችተዋል፡፡ በእኚህ መምህር አባባል የሃይማኖት ተቋማት የሃይማኖት አባቶች መነታረኪያ ሳይሆኑ የምዕመናን ሥነ ምግባር
ማነፂያ ስፍራዎች ናቸው ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት በርትተው ሃላፊነታቸውን ቢወጡ ለወህኒ ቤቶችና ለፖሊስ ሃይል የሚመደበው ወጪ ይቀንስ ነበር ሲሉም አክለዋል - መምህሩ፡፡
በዓለም ደረጃ ኒውክሌር ለመገንባት የሚውለው ዕውቀትና ሃብት የስንት ሚሊዮን ህፃናትን ቀለብ ወይም የክትባት ወጪ ሊሸፍን እንደሚችልም በቁጭት ተናግረዋል፡፡ ከወዳጄ ቤት ወጥቼ ወደ ቤቴ ሳዘግም የሃይማኖት ሊቁ በኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ የተናገሩትን መሬት ጠብ የማይል ቁምነገርና ጠሊቅ ሃሳብ በአዕምሮዬ እያብሰለሰልኩ ነበር፡፡ እውነት እኮ የሃይማኖት ተቋማት የሥነ ምግባር ትምህርት የሚሰጡበት የተመቻቸ መድረክ ወይም ዝግጁነቱ ቢኖራቸው የወንጀለኞችን ቁጥር መቀነስ ብቻ ሳይሆን ብዙ የአገራችንን ችግሮች ይቀርፉ ነበር ብዬ ማውጠንጠን ጀመርኩ፡፡
ምን አልባትም አንዳንድ ከፍተኛ የመንግስት በጀት የሚመደብላቸው የመንግስት መ/ቤቶች ላያስፈልጉም ይችሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ የሙስና ወንጀል የሚፈፅሙ ዜጐች እንዳይኖሩ ተቋማቱ ታትረው ከሰሩ ሙስና ይገታል፡፡ ይሄ ማለት የሥነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አያስፈልግም ነበር፡፡ መቼም ሙስና ሳይኖር ወንጀሉን የሚመረምርና የሚያጣራ መ/ቤት አያስፈልግም አይደል!
ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ምዕመኑን በሚገባ ካስተማሩ ህዝባቸውን የሚዋሹ ፖለቲከኞች አይፈጠሩም፡፡ ምርጫ ማጭበርበር የሚሉት ነገር አይነሳም፡፡ በሥልጣን አላግባብ መጠቀም፣ ሰብዓዊ መብቶችን መጣስ፣ ሥልጣንን የሙጥኝ ማለት፣ ለፖለቲካ ሥልጣን ሲሉ ሴራ መጠላለፍ ወዘተ አይኖሩም ነበር፡፡
ክፋቱ ግን በተለይ የአንዳንድ ሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እንኳንስ ምዕመኑን በሥነ ምግባር ትምህርት ከጥፋትና ከክፋት ሥራ ሊያድኑ ቀርቶ ራሳቸውም ትምህርትና ምክር የሚሹ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ተግሳፅም ጭምር፡፡
ከሰብኣዊ
No comments:
Post a Comment