Tuesday, April 2, 2013

‹‹ርዕዮት የአቋም ለውጥ ታደርጋለች ብላችሁ ስጋት አይግባችሁ››


‹‹ርዕዮት የአቋም ለውጥ ታደርጋለች ብላችሁ ስጋት አይግባችሁ››
ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመማር የምትገኝበትን የማረሚያ ቤት አስተዳደር በመጠየቅ ይሁንታ በማግኘቷ 16.000 ብር በመክፈል የተመዘገበችው ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት አለሙ ባልተጻፈ ህግ ትምህርቱን እንዳትከታተልና ከትምህርት ቤቱ የተላኩላት የመማሪያ መጻህፍት እንዳይገቡላት ተደርጋለች፡፡ይሁንና ርዕዮትና ቤተሰቦቿ ጉዳዮን ለሚዲያ ሳይገልጹ ቆይተዋል፡፡ርዕዮት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚደርሱባትን ኢሰብአዊ ድርጊቶች ቤተሰቦቿን ጭንቀት ውስጥ ላለመክተት በማሰብ ተቋቁማ አልፋለች፡፡
በያዝነው ሳምንት አንድ ምሽት የደረሰባት ነገር ግን ይህንን ሁኔታ የሚያውቁ ሁሉን ያስገረመ ነበር፡፡ጅራፍ ራሱ ገርፉ ራሱ ይጮሃል እንደሚባለው ርዕዮት ክስ ቀርቦባታል፡፡ክሱ የማረሚያ ቤቱን አስተዳደር የሚመለከት ሲሆን ፈራጆቹም የማረሚያ ቤቱ ሰዎች ናቸው፡፡‹‹ለማረሚያ ቤቱ ሰዎች ክብር አትሰጪም፤የምትሰሩትን ስራ በሚዲያ አጋልጣለሁ እያልሽ ትዝቻለሽ››የሚል ክስ የቀረበባት ርዕዮት ምላሹን የምሰጠው ከጠበቃዬ ተማክሪ ነው ብላለች፡፡ጋዜጠኛዋ ላይ የቀረበው ክስ ጥፋተኛ መሆኗን በመደምደም ውሳኔ የሚያስተላልፍ ከሆነ ቤተሰብና ውስን በሆኑት ጠያቂዎቿ እንዳትጎበኝ በመከልከል ልታገኘው የሚገባትን የአመክሮ ጊዜ የሚያሳጣት ይሆናል፡፡
ርዕዮት ጥፋተኛ ነኝ በማለት ይቅርታ እንድትጠይቅ የቀረበላትን ውትወታ ሳትቀበል መቆየቷና ትጠጣው ዘንድ የተወሰነባትን ጽዋ በፍጹም የሞራል የበላይነት ለመጨለጥ እግረ ሙቅ ውስጥ ራሷን ማስገባቷ በቅናት እንዲለበለቡ ያደረጋቸው ሰዎች በየጊዜው እንዲህ አይነት ድግስ በማዘጋጀት ተስፋ እንድትቆርጥ ለማድረግ የሚታትሩ ቢሆንም ርዕዮት በዓለ ልደቷን ለማክበር ቃሊቲ በተገኘንበት ሰዓት‹‹ርዕዮት የአቋም ለውጥ ታደርጋለች ብላችሁ ስጋት አይግባችሁ ››ብላናለች፡፡

No comments:

Post a Comment